ግብፅ እና ኢትዮጵያ አንዳቸው የሌላኛቸውን ዲፕሎማት ለማስወጣት ወሰኑ

ኢትዮጵያ የግብፅ ዲፕሎማት አሕመድ ሞሐራን አሕመድ ሶሊማን በ48 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ ስትወስን ግብፅ በበኩሏ የአጸፋ እርምጃ መውሰዷን አስታውቃለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት መስከረም 21/2019 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ ዲፕሎማቱ ከአገር እንዲወጡ የተወሰነው "ዲፕሎማሲያዊ ጥሰት" በመፈጸማቸው መሆኑን አመልክቷል።
ዲፕሎማቱ ማሳሰቢያው ከተሰጠበት ሰዓት አንስቶ በ48 ሰዓታት ውስጥ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ መወሰኑ ተገልጿል።
የግብፁ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን መና እንደዘገበው፤ ካይሮ የኢትዮጵያን ውሳኔ "አሳዛኝ" እና "ምክንያታዊ ያልሆነ" ስትል ኮንናለች።
ኢትዮጵያ የግብፁ ዲፕሎማት ከአገር እንዲወጡ ላስተላለፈችው ውሳኔ በምላሹ ግብፅም በካይሮ ያሉት የኢትዮጵያ ዲፕሎማት በ48 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ አሳስባለች።
የመገናኛ ብዙኃኑ የመንግሥት ምንጭ ግብፅ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎችም አገራት ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ ገብታለች መባሉን ውድቅ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ "የውጭ ኃይሎችን ለውስጣዊ ውድቀቶቿ እና ዘላቂ ቀውሶቿ ተጠያቂ ታደርጋለች" ሲሉም ወንጅለዋል።
ኢትዮጵያ በኤርትራ መዲና አሥመራ የሚገኘውን ኤምባሲዋን ለመዝጋት መወሰኗን እና 10 የኤርትራ ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ አገሪቷን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠቷን አስታውቃለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ ይህንን እርምጃ የወሰደው ኤርትራ "ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ" በሆነ መንገድ ለምትፈፅመው "የጠብ ጫሪነት እና የትንኮሳ" ድርጊቶች ምላሽ ለመስጠት እንደሆነ ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የግብፁ ዲፕሎማት እና የኤርትራ ዲፕሎማቶች ከአገር እንዲወጡ ማሳሰቢያ የሰጠው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዳግመኛ ባገረሸበት ወቅት ነው።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሚዋጉ ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ ኤርትራን መክሰሳቸው አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ መከላከያ ኤታማዦር ሹሙ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ "እየተዋጋን ያለነው የውጪ ኃይሎችን ፍላጎት ለማስፈጸም ከተሰባሰቡ እና ከተደራጁ ኃይሎች ጋር ነው" ብለው ነበር።
"ሻዕቢያ [ኤርትራ] እና ቲፒኤልኤፍ [ህወሓት] ያለ ሱዳን፣ ያለ ግብፅ እና ከዚያም ባሻገር ያሉ ኃይሎች ካልደገፏቸው ብቻቸውን ተጣምረውም ቢሆን ዋጋ የላቸውም። ሲነጣጠሉ ደግሞ ትርጉም የላቸውም" ሲሉ ተናግረዋል።
የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ ብዙም ባልተለመደ መልኩ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች የመሠረቱትን ጥምረት በመደገፍ የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጓል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

































