በራየንኤር አውሮፕላን በረራ ላይ አንድ መንገደኛ በመስኮት ተስቦ ሊወድቅ እንደነበር ተሳፋሪዎች ተናገሩ

የራየንኤር አየር መንገድ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ራየንኤር በተባለ የአየርላንድ አየር መንገድ አውሮፕላን ጉዞ ላይ እያለ አንድ መንገደኛ በመስኮት ተስቦ ሊወድቅ እንደነበር መንገደኞች ተናገሩ።

የአውሮፕላን መከታተያ መረጃዎች እንዳሳዩት አውሮፕላኑ አየር ላይ ለ10 ደቂቃ ያህል ከቆየ በኋላ በድንገት ወደ መሬት የወረደ ሲሆን፤ መንገደኞች "ፍንዳታ ነገር" መስማታቸውን ተናግረዋል።

የግሪክ ሆስፒታል ኃላፊ የ61 ዓመቱ የሰርቢያ ዜጋ የቃጠሎ ሕክምና እየተደረገለት ነው ብለዋል። "ተስቦ እንዳይወድቅ ባለቤቱ ለአምስት ደቂቃ ያህል እግሮቹን ይዛ ነበር" ሲሉ ስለ ሁኔታው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ አርብ ጠዋት ከግሪኳ ቴሳሎኒኪ ወደ ጀርመን ሚኒንግን ለመብረር የተነሳው አውሮፕላን "ከተነሳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በረራ ላይ እያለ የመንገደኛ መስኮት ወድቋል" ብሏል።

"አውሮፕላኑ በሰላም አርፏል። መንገደኞችም ወደ ተርሚናሉ ተመልሰዋል። አንድ መንገደኛ በቴሳሎኒኪ የሕክምና እርዳታ ጠይቆ እንዲያገኝ ተደርጓል" ሲል የአየርላንዱ አየር መንገድ ገልጿል።

ከበርካታ ሰዓታት በኋላ "መንገኞችን ወደ ሚኒንግን የሚወስድ ቅያሪ አውሮፕላንድ ተዘጋጅቷል" ሲል አክሏል።

መንገደኞች ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት፤ ሌሎች መንገደኞች ተሰባስበው በመጎተት ወደ ውስጥ እስኪያስገቡት ድረስ መንገደኛው እስከ ትከሻው ድረስ ወጥቶ ነበር።

በአውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩ ሌሎች ሰዎችም በጄቱ ሞተር ምክንያት መስኮቱ መሰባበሩን ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይሁን እንጂ አየር መንገዱ በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠም።

ክርስቲና የተባለች መንገደኛ "አየሩ መቀየሩን ወዲያው ነበር ያወቅነው። ጩኸቶች ነበሩ፤ ለቅፅበት ያህል የሆነ ሰው የድንገተኛ አደጋ በሩን የከፈተው መስሎኝ ነበር" ብላለች።

"የአየር ጭምብሉ ወረደ እና ጠንካራ ሽታ ነበር። የአንደኛው መንገደኛ አንገት እና ትከሻ ከመስኮቱ ውጭ ነበር። እንደ እድል ሆኖ የመቀመጫ ቀበቶውን አላወለቀም ነበር።"

ሶፊያ የተባለች ሌላ መንገደኛ ደግሞ "የኦክስጅን ጭንብሉ ሲወርድ ምን እንደተፈጠረ አላወቅንም ነበር። ምንም ሳንሆን እንደምንመለስ አላወቅንም ነበር። በአውሮፕላኑ መጨረሻ ላይ ነበር የተቀመጥነው። እና የሆነ ፍንዳታ ነገር እንደነበረ አወቅን" ብላለች።

"አውሮፕላኑ ለመውደቅ እየወረደ እንደነበር አስበን ነበር። አየሩ ከባድ ነበር። መተንፈስ እንደማንችል ተሰማን። የተጎዳው ሰው እየደማ ነበር፤ ለበርካታ ጊዜ ራሱን ስቶ ነበር። ይህም ኦክስጅን በማጣት እና በድንጋጤ ይሆናል" ስትልም ገልጻለች።

አውሮፕላኑ 18 ዓመት እድሜ ያለው መሆኑ የታመነ ሲሆን በራየንኤር ስር የሚገኘው ማታል ኤር ንብረት መሆኑ ተነግሯል።

አየር ማረፊያውን የሚያስተዳድረው ፍራፖርት ግሪስ "ክስተቱ በሄልኒክ የአየር እና ባቡር ደኅንነት ምርመራ ባለሥልጣን እየተመረመረ ነው" ብሏል።

የአየርላንድ አቪየሽን ባለሥልጣን ለቢቢሲ ስለ ክስተቱ እንደሚያውቅ እና ለመርማሪዎች እርዳታ እንደሚሰጥ ተናግሯል።

ክሪስ ብሬዲ የተባሉ ጡረታ የወጡ አብራሪ ለቢቢሲ መንገደኛው የመቀመጫ ቀበቶውን ባያስር ኖቶ ከዚህ በላይ የከፋ አደጋ ይደርስ ነበር ብለዋል።

እ.አ.አ በ2018 በአሜሪካ አየር መንገድ ከተጎዳ ሞተር የወጣ ፍርስራስ መስኮቱን በመስበሩ የመንገደኛ ሕይወት አልፏል።