አቶ ኢሳያስ ጅራ እንዴት ለእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት ብቸኛ ተወዳዳሪ ሆነው ቀረቡ?

አቶ ኢሳያስ ጅራ ላለፉት ስምንት ዓመታት ፌዴሬሽኑን በፕሬዝዳንት የመሩ ሲሆን፣ ለቀጣይ አራት ዓመታት በአመራርነት ለመቀጠል እየተወዳደሩ ይገኛሉ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Football Federation

የምስሉ መግለጫ, አቶ ኢሳያስ ጅራ ላለፉት ስምንት ዓመታት ፌዴሬሽኑን በፕሬዝዳንት የመሩ ሲሆን፣ ለቀጣይ አራት ዓመታት በአመራርነት ለመቀጠል እየተወዳደሩ ይገኛሉ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

አቶ ኢሳያስ ጅራ ፌዴሬሽኑን ለሦስተኛ ዙር ለመምራት በብቸኝነት ተወዳዳሪ ሆነው መቅረባቸው ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ለቀጣይ ፕሬዝዳንታዊ ተወዳዳሪነት በዕጩነት የቀረቡት ብቸኛ ተወዳዳሪ አቶ ኢሳያስ ጅራ ቦሾ መሆናቸውን ረቡዕ ነሐሴ 13/2018 ዓ.ም አሳውቋል።

የፌዴሬሽኑ የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም ለፌዴሬሽኑ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት በላከው ደብዳቤ፣ እስከ ነሐሴ 4 ባሉት 12 ቀናት ውስጥ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ እና በፕሬዝዳንቱ አቅራቢነት የሚመረጡ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን ከእነተጠባባቂያቸው ለፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት እንዲልኩ ማሳወቁን ገልጿል።

ኮሚቴው ነሐሴ 5፣ 11 እና 13 ባደረጋቸው ስብሰባዎቹ ስለቀረቡት ዕጩዎች ማጣራቱን እና በዚህም መሠረት ለዕጩ ፕሬዝዳንታዊ ተወዳዳሪነት የቀረቡት አቶ ኢሳያስ ጅራ ብቻ መሆናቸውን ፌዴሬሽኑ አሳውቋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ ሞላ፣ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ከአቶ ኢሳያስ ጋር ለመፎካከር ሌላ አንድ ዕጩ ቀርበው እንደነበረ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሆኖም፣ ለፕሬዝዳንትነት የቀረቡት ሌላኛው ዕጩ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ ላይ የተዘረዘሩትን መመዘኛዎች ባለማሟላታቸው ኮሚቴው ውድቅ እንዳደረጋቸው ገልፀዋል።

ኦቶ ኢሳያስ ጅራ፣ ለአራት ዓመታት የሚቆየውን ሁለተኛ የሥልጣን ጊዜያቸውን ዘንድሮ ያጠናቅቃሉ። አንድ ግለሰብ ፌዴሬሽኑን ለሁለት የስልጣን ዘመን ብቻ እንዲያስተዳድር ይደነግግ የነበረው መተዳደሪያ ደንብ በዚህ ዓመት ተሻሽሎ ነው ፕሬዝዳንቱ ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን የሚወዳደሩት።

በተሻሻለው የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት፣ አንድ ዕጩ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳዳር አንድ መቶ ከሚሆኑ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ውስጥ ቢያንስ የአራቱን ድጋፍ ማግኘት ይጠበቅበታል። በተጨማሪም ሁለት የከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ በአገሪቱ ካሉት 14 የክልል ፌዴሬሽኖች ደግሞ የአንዱን ይሁንታ ማግኘት ይጠበቅበታል።

ከዚህ ቀደም ክልሎችን የሚወክሉ የፕሬዝዳንትነት እና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ዕጩዎች በክልሎች ድጋፍ ተደርጎላቸው የሚቀርቡበት አሰራርም በተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ ተቀይሯል።

አቶ ኢሳያስ ጅራ
የምስሉ መግለጫ, አቶ ኢሳያስ ከአራት ዓመታት በፊት ለሁለተኛ ዙር ፕሬዝዳንትነት ከአቶ መላኩ ፈንታ እና ከአቶ ቶኪቻ ዓለማየሁ ጋር ነበር የተወዳደሩት
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አቶ ኃይሉ ሞላ ለቢቢሲ በሰጡት አጭር ማብራሪያ፣ "ፕሬዝዳንታዊ ዕጩው ነው ሄዶ ድጋፍ ስጡኝ የሚለው እንጂ ክልሎች አይወክሉትም" ብለዋል።

በአዲሱ መተዳደሪያ መሠረት ለውድድር የሚቀርቡት ፕሬዝዳንቶች ብቻ ናቸው። ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና ለምክትል ፕሬዝዳንትነት የሚባል ምርጫ የለም።

ለውድድር የሚቀርቡት እጩ ፕሬዝዳንቶች እያንዳንዳቸው አንድ ምክትል ፕሬዝዳንትን ጨምሮ ስምንት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ወይም ካቢኔያቸውን ይዘው መቅረብ አለባቸው። በተጨማሪም እያንዳንዱ ዕጩ አምስት ተጠባባቂ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ማዘጋጀት አለበት።

የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴው የአሰራር መመሪያ ለሚዲያዎች በተናጥል ዝርዝር ማብራሪያ መስጠትን እንደማይፈቅድ በመጥቀስ፥ መስፈርት አላሟላም ስላሉት ሌላኛው ዕጩ እና ስላላሟላቸው መስፈርቶች ለማብራራት የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ ፈቃደኛ አልሆኑም።

ቢቢሲ ስለጉዳዩ ከክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም። የሲዳማ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና የአማራ ክልሎችን የሚመለከታቸው ኃላፊዎች በስልክ እና በጽሁፍ አግኝቶ ለማነጋገር ጥረት ቢያደርግም ምላሽ አልሰጡም።

ከኢትዮጵያ ባሕል እና ስፖርት ሚኒስትር በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነውም ጥረት ቃል አቀባዩ ስልካችንን ባለማንሳታቸው እና በጽሑፍ ላቀረብነው ጥያቄም ምላሽ ባለመስጠታቸው አልተሳካም።

አቶ ኢሳያስ ጅራ ብቸኛ ተወዳዳሪ ሆነው መቅረባቸው ግን በርካታ የስፖርት ቤተሰቦችን እያነጋገረ ይገኛል።

ብዙዎችም ትችት እየሰነዘሩ ነው። የኢትዮጵያን እግር ኳስ በቅርበት የሚከታተለው ቴዎድሮስ ባጫ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ በርካታ የስፖርት አፍቃሪያን አንዱ ነው።

"የኢትዮጵያን እግር ኳስ ላለፉት 30 ዓመታት ተከታትያለሁ" የሚለው ቴዎድሮስ፣ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ "በተቋም ግንባታ እና በክለብ ላይሰንሲንግ ላይ ለውጥ አላማጡም" ሲል አቶ ኢሳያስን ይተቻል።

ቴዎድሮስ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የሚፈለገውን እድገት ያላሳየበት ትልቁ ምክንያት ተቋም መገንባት ባለመቻሉ እንደሆነ አብራርቷል። የዘመናዊ እግር ኳስ ዋናው መሠረት የተቋም ግንባታ ነው የሚለው ቴዎድሮስ፥ ፌዴሬሽኑ ተተኪዎችን ማሳደግ በሚያስችል ልክ "ተቋማዊ አደረጃጀት አለመገንባቱን" ይተቻል።

ቴዎድሮስን የሚያሳስበው የአቶ ኢሳያስ ለቀጣይ 4 ዓመታት መቀጠል ሳይሆን፣ "የሥልጣን ጉዳይ ከእግርኳሱ በላይ መታየቱ" እንደሆነ ይገልፃል።

"እኔ 4 ዓመት አይደለም ከዚህ በኋላ 40 ዓመት ኢሳያስ ቢመራ ችግር የለብኝም። ነገር ግን ተቋም አለመገንባቱ ነው። የጉልቻው መለዋወጥ አይደለም ወጡን የሚያጣፍጠው ሼፉ ነው ወጡን የሚያጣፍጠው" ይላል ስለሚያሳስበው ጉዳይ ሲያስረዳ።

አብዛኛው የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ከኢትዮጵያ አንጻር በታዳጊዎች ልማት ላይ የተሻለ ሥራ መስራታቸውን ታንዛኒያን በምሳሌነት በማንሳት ያስረዳል። ለምሳሌ የታንዛኒያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለፉት 9 ዓመታት ተቋማዊ መሠረት በመጣል ከታች ጀምሮ ተተኪዎች የሚፈሩባቸው አካዳሚዎችን በመገንባት ትልቅ ለውጥ ማሳየት እንደቻለች ጠቅሷል።

በኢትዮጵያ የትምህርት ቤቶች የታደጊዎች ውድድር እንኳን በቅጡ እንደሌለ በመግለጽ፣ "ብዙ ልጆች ያለውድድር ነው 17 ዓመታቸው ላይ የሚደርሱት፤ ይህ ከኢትዮጵያ ውጭ የትም አገር ላይ የለም" ሲል ክፍተቱን ያነሳል።

ኳስ እና የኢትዮጵያ ባንዲራ

ቴዎድሮስ በአሁኑ ወቅት ከታዳጊ ልጁ ዳግማዊ ጋር ከ 3 ዓመት በላይ ኳታር ይገኛል። ወደ ኳታር የሄዱበት ምክንያት ደግሞ በብዙ ጥረት ልጁ በአንድ የክለብ አካዳሚ ውስጥ ባገኘው የስልጠና ዕድል ምክንያት ነው።

በኳታር ልጁ የሚሰለጥንበትን ክለብ ጨምሮ ከ4 ዓመት ጀምሮ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ በእድሜ የተከፋፈለ የሥልጠና ሂደት እና ልጆች ደረጃ በደረጃ የሚያድጉበት አሠራር መኖሩን ይናገራል።

"እኔ ለምንድነው አገር ጥዬ የወጣሁት? ልጄ ከልጅነቱ ጀምሮ በውድድር ማለፍ አለበት። ውድድር እያደረገ ሲያድግ ነው ቀጣይ የእግር ኳስ ግቡ ሊሳካ የሚችለው፤ መሠረት ይዞ ያድጋል ማለት ነው" ይላል።

ሌላው ተተኪዎችን ከማፍራት ጋር በማያያዝ ቴዎድሮስ የሚያቀርበው ትችት፣ ክለቦች ፈቃድ የሚያገኙበት 'የክለብ ላይሰንሲንግ' ሕግ አለመተግበሩን ነው።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የክለብ ላይሰንሲንግ ሕግ፣ ክለቦች በውድድሮች ለመሳተፍ ሊያሟሏቸው የሚገቡ ጥብቅ ደንቦችን ያካተተ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ አሰጣጥ ሥርዓት ነው።

አቶ ኢሳያስ ከአራት ዓመታት በፊት ለሁለተኛ ዙር ፕሬዝዳንትነት ከአቶ መላኩ ፈንታ እና ከአቶ ቶኪቻ ዓለማየሁ ጋር በሚወዳደሩበት ወቅት የገቡትን የክለብ ላይሰንሲንግ ሕግን የመተግበር ቃልም እንዳልጠበቁ ቴዎድሮስ ይገልፃል።

በ2014 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ፣ በብስራት ራዲዮ ላይ በነበረው "ጃንሜዳ" የተባለ የስፖርት ፕሮግራም ላይ ከእርሳቸው ጋር ባደረገው ቆይታ "ባለፉት አራት ዓመታት አላሳካሁም ብለው የሚቆጩበት አንዱ የክለብ ላይሰንሲንግን ጉዳይ እንደነበረ ተናግረዋል" ይላል። ዳግም ከተመረጡ በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ውስጥ ይህን የማሳካት ግብ እንደነበራቸው በቁጭት መናገራቸውንም ያስታውሳል። ይሁን እንጂ "ይህን ቃላቸውን እንኳን ሳያሳኩ በተሻሻለ ሕግ ለሦስተኛ ዙር ህያውም ብቸኛ ዕጩ ሆነው መቅረባቸው" እንዳልተዋጠለት ያስረዳል።

ክለቦች የውድድር ፈቃድ ለማግኘት ታዳጊዎችን ቢያንስ ከ12 ዓመታቸው ጀምሮ ተቀብለው ተተኪ የሚያፈሩበት ሥራ መስራት ቢጠበቅባቸውም ይህ መስፈርት ብዙም እየተተገበረ አይደለም። ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ወደ ፕሪሚየር ሊግ መጥተው፣ ከሊጉ ሲወርዱ "የፈረሱ ቡድኖች" የኖሩት በዚህ ምክንያት እንደሆነ ነው ቴዎድሮስ የሚያምነው።

ፌዴሬሽኑ የካፍ የልቀት ማዕከልንም በተገቢው መንገድ እየተጠቀመ አለመሆኑን ተችቷል።

እናም ይላል ቴዎድሮስ "ፕሬዝዳንት ለ3ኛ ዙር ይመረጥ ተብሎ ሕግ ከሚሻሻል ምን አለበት እንዴት እግር ኳሱን እናደራጀው የሚል ሕግ ቢያወጡ።"

ቢቢሲ በአቶ ኢሳያስ ላይ ለቀረበው ትችት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

አቶ ኢሳያስ በኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ ላይ ተገኝተው ዋንጫ ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Football Federation

ቢቢሲ ያነጋገርናቸው ሁለት የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞችም በቴዎድሮስ ሀሳብ ይስማማሉ።

ከጋዜጠኞቹ መካከል አንዱ የሆነው አንጋፋው የኢቢሲ የስፖርት ጋዜጠኛ ማንደፍሮ ታደሰ፣ በእግር ኳሱ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል አማራጭ ሀሳብ ያለው ተወዳዳሪ ሳይቀርብ፣ አቶ ኢሳያስ ጅራ ብቸኛ ዕጩ ሆነው መቅረባቸው "ለውጥ ፈላጊውን የስፖርት ቤተሰብ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው" ይላል።

ማንደፍሮ አክሎም "የተሻሻለው የፌዴሬሽኑ ሕግ የተወሳሰቡ መስፈርቶችን ያካተተ መሆኑን፣ የተሰጠው ጊዜ አጭር መሆኑን እንዲሁም በጥቅም የመተሳሰር አዝማሚያ መኖሩን" አስተያየት ሰጪዎቹ ሌላ ዕጩ ላለመቅረቡ በምክንያቱ ይገልፃሉ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ ሞላ፣ በምርጫ ሕጉ መሠረት የትኛውም የጠቅላላ ጉባዔ አባል የአራት አባላትን እና የአንድ ክልል ፌዴሬሽንን ድጋፍ ያገኘ ፕሬዝደንታዊ ዕጩ ማቅረብ እንደሚችል ተናግረዋል። ለዚህ ሂደት የሚሰጠው 10 ቀን መሆኑን ሕጉ እንደሚደነግግ እና ይህ መተግበሩንም አክለዋል።

"በቀሩት ቀናት ውስጥ የማብራሪያ ጥያቄ የሚጠየቅ ከሆነ፣ ከፊፋ ጋር እንገናኛለን፤ በፊፋ ሕግ የሚፈታ ከሆነ በፊፋ ሕግ እንፈታለን፤ ከዚያን ለጠቅላላ ጉባዔው ቀርቦ የጠቅላላ ጉባዔው ይወስናል" ሲሉ አቶ ኃይሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ኢሳያስ ጅራን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሊሳካልን አልቻለም። አቶ ኢሳያስ ከ4 ዓመታት በፊት ለሁለተኛ ዙር ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በሚወዳደሩበት ወቅት፥ በመጀመሪያዎቹ 4 ዓመታት "ደረት የሚያስነፋም ባይሆን አንገት የማያስደፋ ሥራ" መስራታቸውን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረው ነበር።

ሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው ዘንድሮ የሚያበቃው አቶ ኢሳያስ፣ መስከረም 5/2019 ዓ.ም ለተጨማሪ አራት ዓመታት በፕሬዝደንትነት የሚያቆያቸውን ሦስተኛ የሥልጣን ጊዜ ያለማንም ተቀናቃኝ በጉባዔው ይቸራሉ ተብሎ ይጠበቃል።