ቀጥታ, የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ የጋዛ የሰላም ዕቅድን ለማስፈጸም ከሐማስ መሪዎች ጋር ተገናኙ

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ የሆኑት ጃሬድ ኩሽነር፣ ባልተለመደ ሁኔታ በአሜሪካ ስለሚደገፈው የጋዛ የሰላም ዕቅድ አተገባበር ከሐማስ መሪዎች ጋር ተወያዩ። የትራምፕ አማች የሆኑት ኩሽነር በአዲሱ የሐማስ መሪ ኻሊል አል ሃያ የሚመራውን ልዑክ ያገኙት ትናንት እሁድ ግብፅ ውስጥ እንደሆነ አንድ የፍልስጤም ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ የጋዛ የሰላም ዕቅድን ለማስፈጸም ከሐማስ መሪዎች ጋር ተገናኙ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ጥቃቶች ከተፈጸሙ በኋላ በሆርሙዝ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀነሰ

    ሆርሙዝ ወሽመጥ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ባለፈው ሳምንት በነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ጥቃቶች ከተፈጸሙ በኋላ፣ ቅዳሜ እና እሁድ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ያለፉ መርከቦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን መረጃዎች አመለከቱ።

    ይህ ዜና የተሰማው በኢራን እና በአሜሪካ መካከል እየተካሄደ ያለውን ግጭት ለማስቆም የሚደረገው ድርድር ተቋርጦ ባለበት ሁኔታ ነው።

    ኢራን ወሳኙ የባሕር መተላለፊያ መስመር፣ የሆርሙዝ ወሽመጥ የሉዓላዊ ግዛቷ አካል በመሆኑ በቁጥጥሯ ስር እንደሚሆን እየገለጸች ነው። አሜሪካ ደግሞ ስፍራው ነጻ ዓለም አቀፍ የባሕር አካል እንዲሆን እየጣረች ነው።

    በዚህም ሳቢያ ኢራን ሳያሳውቁ እና ከተፈቀደው መስመር ውጪ በሆርሙዝ በኩል ለማለፍ በሚሞክሩ መርከቦች ላይ ጥቃት እየፈጸመች ሲሆን፣ አሜሪካ በበኩሏ የኢራን መርከቦች በወሽመጡ እንዳይንቀሳቀሱ ዕገዳ ጥላለች።

    ባለፈው ሳምንት በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት በአካባቢው በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ስጋት ተፈጥሯል። ኬፕለር የተባለው የባሕር ጉዞ እንቅስቃሴን የሚከታተል ተቋም ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ቅዳሜ ዕለት አምስት የጭነት መርከቦች ሲያልፉ፣ እሁድ ዕለት ግን አንድም መርከብ በሆርሙዝ አላለፈም።

    በወዲያኛው ሳምንት ቅዳሜ እና እሁድ 31 መርከቦች በወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ወሽመጥ በኩል ማለፋቸው ተመዝግቦ ነበር። ይህም ካለፉት ቀናት ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ የመርከቦች እንቅስቃሴ መገታቱን ያመለክታል።

  2. የትራምፕ ልዩ መልዕክተኛ የጋዛ የሰላም ዕቅድን ለማስፈጸም ከሐማስ መሪዎች ጋር ተገናኙ

    በጋዛ ፍርስራሾች መሃል ልጆች ይዛ የምትሄድ ሴት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመካከለኛው ምሥራቅ መልዕክተኛ የሆኑት ጃሬድ ኩሽነር፣ ባልተለመደ ሁኔታ በአሜሪካ ስለሚደገፈው የጋዛ የሰላም ዕቅድ አተገባበር ከሐማስ መሪዎች ጋር ተወያዩ።

    የትራምፕ አማች የሆኑት ኩሽነር በአዲሱ የሐማስ መሪ ኻሊል አል ሃያ የሚመራውን ልዑክ ያገኙት ትናንት እሁድ ግብፅ ውስጥ እንደሆነ አንድ የፍልስጤም ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    የሰላም እቅዱን ትግበራ የሚቆጣጠረው የትራምፕ የሰላም ቦርድ ሐማስ እና በጋዛ የሚገኙ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች “ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈቱ” የሚያደርግ ስምምነት ላይ መድረሱን ሐምሌ ላይ አስታውቆ ነበር።

    ባለፈው ሳምንት ግን እስራኤል ወታደሮቿን እንድታስወጣ እንዲሁም ጋዛ ውስጥ አዲስ የፍልስጤም ሲቪል አስተዳደር እንዲመሠረት የሚያደርገውን ባለ 15 ነጥብ እቅድ እንደማትቀበለው ገልጻለች።

    ስምንት ሙስሊም አገራት ትናንት እሁድ ባወጡት መግለጫ እስራኤል እቅዱን ውድቅ ማድረጓን ኮንነዋል።

    መጀመሪያ ላይ ጋዛ ውስጥ ሰላም ለማምጣት ታስቦ የተቋቋመውን እና ኋላ ላይ በዓለም ዙሪያ የሚካሄዱ ግጭቶችም እንዲያካትት የተቋቋመውን የሰላም ቦርድ የሚመሩት ፕሬዝዳተት ትራምፕ ናቸው።

    የትራምፕ መልዕክኛ ኩሽነር ከሐማሱ መሪ አል ሃያ ጋር ያደረጉት ስብሰባ፣ የጋዛ ተኩስ ማቆም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ የተካሄደ የመጀመሪያው ንግግር እንደሆነ ተገልጿል።

    የሰላም ቦርድ መልዕክተኞች የሆኑት ኒኮላይ ምላደኖቭ እንዲሁም የቀድሞው የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ስብሰባው ላይ መገኘታቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል። የሰላም ጥረቱን ሲያሸማግሉ የቆዩት የግብፅ፣ ኳታር እና ቱርክ ተወካዮችም መሳተፋቸው ተሰምቷል።

    የሐማስን ትጥቅ መፍታት በተመለከተ ስለሚወሰዱ ተግባራዊ እርምጃዎች እንዲሁም የእስራኤል ወታደሮችን መውጣት እና ሰብዓዊ ጥረቶችን በተመለከተ በውይይቱ ምን እንደተባለ እስካሁን ይፋ አልሆነም።

    የትራምፕ መልዕክተኛ ኩሽነር በግብፅ ቆይታቸው፣ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ጋርም ተገናኝተዋል። ዛሬ ሰኞ ደግሞ ኩሽነር፣ ምላደኖቭ እና ብሌር የትራምፕን እቅድ ለማስፈጸም ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር ይገናኛሉ።

    የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ስምምነቱ እንዲተገበር መጀመሪያ ሐማስ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ መፍታት እንዳለበት ገልጸዋል።

    ኔታንያሁ ባለፈው ሳምንት ባደረጉት ንግግር፣ “እስራኤል የሰላም ቦርዱን ባለ 15 ነጥብ የጋዛ ሰነድ አትቀበልም። ሐማስ የእውነት ትጥቁን እስካልፈታ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በምንም አይነት አይወጣም” ሲሉ የቅርብ አጋራቸው አሜሪካን ተቃውመዋል።

    ግብፅ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ኳታር፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ዮርዳኖስ፣ ቱርክ፣ ፓኪስታን እና ኢንዶኔዥያ እሁድ ዕለት ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ እስራኤል የአሜሪካን ዕቅድ ውድቅ ማድረጓ የትራምፕን የሰላም ጥረት አደጋ ላይ ይጥለዋል የሚል ስጋታቸውን አንጸባርቀዋል።

    ከጥቅምት አንስቶ ወደ ሥራ የገባው የተኩስ አቁም ስምምነት አሁንም ተግባራዊ መሆን አላቆመም።

    ነገር ግን እስራኤል ስምምነቱ ከተፈረመ ጊዜ ጀምሮ በጋዛ ውስጥ በርካታ ጥቃቶችን ፈጽማለች። ሐማስ ተኩስ አቁሙን ጥሷል በሚል የመጨረሻውን ጥቃት ያደረሰችው ኻን ዩኒስ እና ኑሴራት በተባሉት የጋዛ አካባቢዎች ነው።