በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ የክልል ፕሬዝደንቶች ሰጡ የተባለው አስተያየት እና የጎላው ልዩነት

የምክክር ጉባኤ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian National Dialogue Commission

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

አገራዊ ምክክሩ ከተጀመረ አንድ ወር ከአንድ ሳምንት ሆኖታል። በዚህ ጉዞ ውስጥ ታዲያ አዲስ አበባ የምክክሩ አስኳል ሆና ዘልቃለች። አስካሁን ባለው የምክክሩ ሂደት የአዲስ አበባ ጉዳይ መግባባት ያልተደረሰበት እና ሂደቱን ያዘገየ አጀንዳ ሆኗል።

ረቡዕ ዕለት የአጀንዳ ምክረ-ሃሳብ አጠናቃሪዎች ጥንቅራቸውን ካቀረቡ በኋላ "በደስታ ያነቡ ነበሩ" የሚሉን አንድ የምክክሩ ተሳታፊ፣ በቀጣዩ ቀን ትላንት ሐሙስ ነሐሴ 14 ደግሞ ነገሮች የተለየ መልክ መያዛቸውን ይገልጻሉ።

የአዲስ አበባን እና የድሬዳዋን ጉዳይ በሚዳስሰው በፌዴራል ከተሞች አጀንዳ ላይ የሚመክረው የ500 ቡድን አባል የሆኑት የቢቢሲ ምንጭ፣ ባለፉትን ሁለት ቀናት የታዘቡትን ሲገልፁ፣ ተመካካሪዎች ስምምነት የተደረሰ መስሏቸው "ብሩህ ተስፋ" ሰንቀው የመጨረሻ የውሳኔ ምክረ-ሃሳብ የሚሰጡበትን ጉባኤ በጉጉት ሲጠባበቁ እንደነበር ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ የተጠናቀረው የምክክሩ ውጤት ሲቀርብ ግን አንዳንዶች አዳራሹን ጥለው እስኪወጡ ያደረሰ ልዩነት መፈጠሩን ሌላ ተሳታፊ ያስረዳሉ።

ቢቢሲ በመጨረሻዎቹ ቀናት በምክክሩ ሂደት ላይ የነበሩ ሁኔታዎችን በተመለከተ ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ በሂደቱ ሲሳተፉ ከነበሩ ስማቸውን እንዲገለጽ ካልፈለጉ ሁለት የምክክሩ ተሳታፊዎች ዝርዝር ሁኔታውን መረዳት ችሏል።

ረቡዕ ዕለት የነበረው ድባብ

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ወ/ሮ ሂሩት ገብረ ሥላሴ ረቡዕ ነሐሴ 13/2018 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ከስምንቱ ባለ 500 ቡድን የተውጣጡ 120 አጠናቃሪዎች ሥራቸውን አጠናቅቀው ለየቡድኖቹ አንድ ወጥ የምክረ-ሃሳብ ሰነድ ረቡዕ ጠዋት ማቅረባቸውን ተናግረው ነበር።

አጠናቃሪዎቹ ከስምንቱ ቡድኖች የተሰጧቸውን ግብዓቶች በማካተት የመጨረሻውን ሰነድ ሐሙስ ዕለት ለ4,000 ተሳታፊዎች እንደሚቀርብ ተናግረዋል። "አንድ ትልቅ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል ማለት ነው" በማለት የሂደቱን ስኬታማነት በወቅቱ ገልፀዋል።

በየአዳራሹ የተከፈሉት 500 አባላት ያሏቸው የሥራ ቡድኖች በስምንቱም ዓበይት አጀንዳዎች ላይ የተደረሱ ስምምነቶችን እና የልዩነት ሃሳቦችን አዘጋጅተው ለየቡድናቸው ሲያቀርቡ መልካም ድባብ እንደነበረ ያነጋገርናቸው ሁለት ተሳታፊዎች ጠቅሰዋል።

በፌደራል ከተሞች አጀንዳ ስር ያለውን የአዲስ አበባን ጉዳይ የሚያየው 7ኛው ቡድን የውይይት ውጤቱን ሲያቀርብ ግን፣ በየአዳራሹ "ጥቂት የቅሬታ ድምፆች ሲሰሙ" ነበር ይላሉ በምክክሩ ሂደት ላይ እስከመጨረሻው በንቃት መሳተፋቸውን የነገሩን ተመካካሪ።

"በጥቅሉ ግን የነበረው መንፈስ የደስታ ነበር። አንዳንዶች ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው በደስታ ሲያነቡ ታይተዋል" በማለትም ድባቡን አስረድተዋል።

አክለውም "ለዓመታት በብሔር ተቧድና በግጭት ስትታመስ ለከረመች ሀገር ልዩነቶችን በውይይት መስመር ለማስያዝ የተኬደው መንገድ እዚህ ላይ በመድረሱ በደስታ የሚፈነድቁ፣ ሂደቱን የብሩህ ተስፋ አዲስ ጅማሮ አድርገው የቆጠሩ በርካቶች ነበሩ" በማለት ቀጣዩን 4,000 ተመካካሪ የሚታደምበትን ትልቅ ስብሰባ በጉጉት እየጠበቁ ወደ ማረፊያቸው መሄዳቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የምክክር ጉባኤ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian National Dialogue Commission

ሐሙስ የቀዘቀዘው አዳራሽ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኮሚሽኑ በተያዘው ቀጠሮ መሠረት 500 አባላት የያዙት ቡድኖች በአጠናቃሪዎቻቸው አማካኝነት ያዘጋጁት አንድ ወጥ የምክረ-ሃሳብ ሰነድ ሲቀርብ ለመስማት 4,000ዎቹ ተመካካሪዎች ጠዋት በአዳራሹ ተገኝተዋል።

ሆኖም አዳራሹ ውስጥ የነበረው ድባብ "የተለየና የከበደ ነበር" ይላሉ የቢቢሲ ምንጭ። ቅርቃር ውስጥ የገቡ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት የመፍትሔ ሀሳብ እንዲያቀርብ የተቋቋመው 230 አባላትን የያዘው "የክልል ጉባኤ" ረቡዕ ምሽት "ድንገተኛና አስቸኳይ ስብሰባ" ተጠርቶ እንደነበር መስማታቸውን ይናገራሉ።

በአዳራሹ ውስጥ የነበረው የከበደ ድባብም የተፈጠረው በዚያ ምክንያት እንደነበር በመጥቀስ "ስብሰባው ለምን እንደተጠራ አስቀድሞ የሚያውቅ ባይኖርም፣ በጭምጭምታ ግን የአዲስ አበባ ጉዳይ እንደሆነ ይናፈስ ነበር" ብለዋል።

ጠዋት 4 ሰዓት የገባው ተመካካሪ ሙሉ ረፋዱን ያለአንዳች ተግባር ማሳለፉን የሚገልፁት እኚሁ ምንጫችን፣ "ለምን እንደዘገየ ምክንያቱን የሚናገር አንድም አካል አልነበረም" ይላሉ።

በመሆኑም ሁለቱም ምንጮቻችን እንደሚሉት "አዳራሹ በስጋትና በጥርጣሬ ጭጋግ ተሸፈነ። 4,000ው ተመካካሪ በቡድን በቡድን እየሆነ ያንሾካሽካል። በተባራሪ የሰማውን ጥርጣሬ ይተነትናል። ይገምታል፣ ያነሳል ይጥላል።"

4,000ው ተሳታፊዎች በጋራ የሚጠባበቁት የሐሙሱ መድረክ የተጀመረው ከቀኑ 6:00 ሰዓት አካባቢ እንደነበረም ይናገራሉ።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በግል ጉዳይ ምክንያት በሀገር ውስጥ ስለሌሉ ሰሞኑን በምክክሩ ላይ አልተገኙም።

ሰባቱ ኮሚሽነሮች ወደ መድረክ ከወጡ በኋላ ከመካከላቸው አንዱ "በአዲስ አበባ የኦሮሚያ መንግሥት ርዕሰ ከተማነት ጉዳይ ላይ በጉባኤው ስምምነት ባለመደረሱ፣ ከኦሮሚያ የተወከሉ ተመካካሪዎች ቅሬታ አቅርበዋል" የሚል ብዙዎች ያልጠበቁትን አዲስ ሃሳብ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

በመቀጠልም "ኮሚሽኑ ይህንን ለመፍታት በመቸገሩ የመፍትሔ አቅጣጫ እና ምክር እንድትሰጡን አጀንዳውን ወደዚህ አምጥተነዋል" ማለታቸውን ሁለቱ ተሳታፊዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አስተያየት የመስጠት ዕድል ሲጀመር፣ ከመድረኩ ፊት ለፊት የተቀመጡት የ12ቱ ክልሎች ፕሬዝደንቶች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ከንቲባዎች የመጀመሪያው ዕድል እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።

ከአማራ ክልል ውጭ "የክልል ፕሬዝደንቶች ተራ በተራ እየተነሱ፣ 'አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ ከተማ እንድትሆን' ከሰፊ ማብራሪያ ጋር የውሳኔ ሃሳብ አቀረቡ" ሲሉ ምንጩ ተናግረዋል።

በመቀጠል ዕድሉ የተሰጣቸው "ከየክልሉ መጣን የሚሉ ተመካካሪዎችም" ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ያነሱትን ሃሳብ በመደገፍ ማስተጋባታቸውን ተናግረዋል። እነዚህ ዕድል ያገኙ ተመካካሪዎች ረቡዕ ምሽት በተጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የታደሙ የ250 ቡድን አባላት መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በአዲስ መልክ የተነሱትን ሃሳቦች "የ500ዎቹ የሥራ ቡድኖች በጥቅል የደረሱበትን የውሳኔ ሃሳብ ወደ ጎን ያለ ነው" የሚሉት ሁለቱ ተሳታፊዎች፣ ምክረ-ሃሳብ የመስጠቱ ሂደት ከምክክሩ አካሔድ ያፈነገጠ እንደሆነ፣ በኮሚሽነሮች መካከልም ልዩነት መፈጠሩን በማንሳት አስረድተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ እና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian National Dialogue Commission

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር

የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች እና ሌሎች ተሳታፊዎች የውሳኔ ሃሳብ በሚያቀርቡበት ወቅት፣ አንድ ኮሚሽነር ሂደቱን አቋርጠው "እኛ የጠየቅነው የመፍትሔ አቅጣጫ እና ምክር እንጂ፣ አንደኛውን አማራጭ ምክረ-ሃሳብ ብቻ ደግፋችሁ አስተያየት እንድትሰጡ አይደለም፤ አካሄዱ መታረም አለበት!" ማለታቸውን ገልፀዋል። "ይህን ሲሉ ከአዳራሹ የተደራጀ የተቃውሞ ጉርምርምታ ተነሳባቸው" ሲሉም አክለዋል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና ምክትላቸው ከሌሎች አቻዎቻቸው የተለየ ንግግር ማድረጋቸውን ምንጫችን ተናግረዋል።

በንግግራቸውም "ኮሚሽኑ የአንድ ወገን ስሞታ ብቻ ነጥሎ ማቅረቡ ስህተት እንደሆነ፣ ጉዳዩ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሆኖ ሳለ የሁለት ወንድማማች ሕዝቦች አለመግባባት አስመስሎ ማቅረብ እንደማይገባ፣ የክልል ፕሬዝደንቶች የተናገሩበት ወገንተኝነት የተሞላበት መንገድ እንደሚያሳዝን ገለጹ" ብለዋል።

ከምክክሩ መስመር ወጥቶ "በኃይል ለመወሰን መሞከር ዘላቂ ሰላም እንደማያመጣ" ማስገንዘባቸውን እና አጀንዳው ጊዜ ተወስዶ ታስቦበት ወደፊት እንዲታይ ለጊዜው ግን በይደር እንዲታለፍ ሀሳብ ማቅረባቸውንም አስረድተዋል።

የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አስታራቂ የሚመስል የፖለቲካ ሃሳብ ማምጣታቸውን አንስተው፣ ነገር ግን ሁሉም ሃሳቡን ከሰነዘረ እና የአዳራሹ ድባብ ከተቀየረ በኋላ ነው ይላሉ።

በመጨረሻም፣ ጉዳዩን መዝጋት ይቻል ዘንድ ከ12ቱ ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ከሁለቱ ከንቲባዎች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከባለሙያዎች የተውጣጣ ኮሚቴ ተሰይሞ "የመፍትሔ ሃሳብ" እንዲያቀርብ ተወሰነኖ ከቀኑ 8 ሰዓት ተኩል አካባቢ ስብሰባው መበተኑን ገልፀዋል።

ነገር ግን ስብሰባው ከመጠናቀቁ በፊት አዳራሹን ጥለው የወጡ መኖራቸውን ሲገልፁ "ከታች ጀምረው በጉባኤው ላይ ሲሳተፉ እና ምክክሩን ሲመሩ የነበሩ፣ አንዳንዶች አንገታቸውን ደፍተው አዳራሹን ጥለው ወጡ" በማለት ነበር።

የነበረው ሁኔታ፣ "ሀገራዊ ምክክሩ በመንግሥት ተጠልፏል" ብለው እንዲረዱ እንዳደረጋቸው የሚገልፁት ምንጫችን "ዐይን ያወጣ እጅ ጥምዘዛና የፖለቲካ የበላይነት ጎልቶ ታይቷል" በማለት በሂደቱ ላይ ጫና እንደተፈጠረ ስሜታቸውን ገልጸዋል።

ፍጻሜው ምንድነው የሚሆነው የሚለው ጥያቄ እንደሚያሳስባቸው የሚናገሩት ሁለቱ የቢቢሲ ምንጮች፣ የመፍትሔ ሃሳብ እንዲያመነጭ ተቋቋመው ኮሚቴ የተለየ ለውጥ ያመጣል ብለው እንደማያስቡ ይገልፃሉ።

ሌላው ተመካካሪም እንዲሁ፣ በዚህ ሂደት የአዲስ አበባ ጉዳይ እልባት ያገኛል የሚል ተስፋ እንደሌላቸው ነው ለቢቢሲ የተናገሩት።

ከአራት ዓመታት በላይ ዋነኛ የሚባሉ የሀገራዊ መግባባት የምክክር አጀንዳዎችን እና ተሳታፊዎችን ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ ሲያሰባስብ የነበረው ሀገራዊ ምክክሩ ከአንድ ወር በላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎችን በማካተት አዲስ አበባ ውስጥ ሲካሄድ ቆይቷል።

በዚህም ምክክሩ ካነሳቸው ስምንት አጀንዳዎች መካከል በአብዛኞቹ አስማሚ ሃሳብ ላይ መድረሱን ተሳታፊዎች የሚናገሩ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ ግን አስከ መጨረሻው ሲያወዛግብ እና ሂደቱን ሲያጓትት ዘልቋል።