የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ከወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲንን ጋር ትውውቅ የለኝም ሲሉ አስተባበሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ ከወሲብ ወንጀለኛው ጄፍሪ ኤፕስቲን ጋር ግንኝነት እንደሌላቸው በዋይት ሐውስ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ሐሙስ ዕለት ቀዳማዊ እመቤቷ ባስተላለፉት ያልተጠበቀ ንግግር በኤፒስቲን ወንጀል ሰለባ የሆኑ ሴቶች የምክር ቤት ምስክርነት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ኤፕስቲን ከባለቤታቸው ዶናልድ ትራምፕ ጋር እንዳስተዋወቃቸው የሚወራውን አሉባልታ ያስተባበሉት ሜላኒያ ትራምፕ፤ ክስተቱን "ስሜን ለማጠልሸት የሚደረግ ክፉ መኩራ" ሲሉ አጣጥለውታል።
የቀዳማዊት እመቤቷን ያልተጠበቀ መግለጫ ምን እንደገፋው ግልፅ አይደለም።
ከፅሕፈት ቤታቸው በኩል ይህን ዓይነት ንግግር እንደሚያደርጉ ቀደም ብሎ ፍንጭ አልተሰጠም ነበር። ዋይት ሐውስም የመግለጫቸውን ይዘት በተመለከተ ለጋዜጠኞች ያለው ነገር የለም።
የኤፒስቲን ተጎጂ እንዳልሆኑ እና ከባለቤታቸው ጋር ከተዋወቁ በኋላ ወንጀለኛውን ግለሰብ ያገኙት እ.አ.አ በ2000 ለአጭር ጊዜ እንደሆነ ተናግረዋል።
"ኤፕስቲን በተጎጂዎቹ ላይ ይፈፅም ስለነበረው በደል አላውቅም ነበር" ብለዋል። "በምንም ዓይነት መጠን አልተሳተፍኩም። ተሳታፊ አልነበርኩም" ሲሉም ተደምጠዋል።
ቀዳማዊት እመቤቷ ከሴቶች የወሲብ ዝውውር ጋር ተያይዞ እስር ቤት የምትገኘውን የጄፍሪ ኤፕስቲን ግብረአበር ግሌን ማክስዌልንም እንደማያውቁ አስተባብለዋል።
በኤፒስቲን ዶሴዎች ውስጥ እ.አ.አ በ2002 የተለዋወጡት ኢሜል ይፋ መውጣቱን በተመለከተ "ተራ ልውውጥ" እና "የትህትና ምላሽ" ነው በማለት አስተባብለዋል።
በሐሙሱ መግለቸው ሜላኒያ ትራምፕ "ተጎጂዎች በምክር ቤት ፊት ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ዕድል ስጧቸው" ሲሉ ለሕግ አውጭዎች ጥሪ አቅርበዋል።
"እያንዳንዷ እና ሁሉም ሴቶች ፍላጎት ካላቸው በሕዝብ ፊት ታሪካቸውን እንዲናገሩ ጊዜ ስጧቸው። እናም ይህ ምስክርነታቸው በኮንግረሱ ማኅደር ይቀመጥ" ያሉት ቀዳማዊት እመቤቷ፤ "ያኔ ብቻ ነው እውነቱን የምናገኘው" ብለዋል።
ባለፉት ወራት በርካታ ስመጥር የንግድ ሰዎች ከኤፕስቲን ጋር ያላቸው ግንኙነት ከተጋለጠ በኋላ ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ የተገፉ ሲሆን፤ ይህንም ሜላኒያ ትራምፕ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
"በእርግጥ ይህ ጥፋተኝነትን የሚያመላክት ባይሆንም፤ ነገር ግን እውነቱን ለማጋለጥ በግልፅ አሁንም መስራት አለብን" ብለዋል።
ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ ከጋዜጠኞች ጥያቄ አልተቀበሉም።
ከመግለጫቸው በኋላ ዲሞክራት የሆኑት የሆኑት የካሊፎርኒያ ተወካይ ሮበርት ጋርሲያ "ሕዝባዊ ምስክርነት እንዲኖር ሜላኒያ ትራምፕ ያቀረቡትን ጥሪ እንቀበላለን" ካሉ በኋላ የምክር ቤት መሪዎች ለጥሪው ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
በቀዳማዊት እመቤቷ እና በጄፍሪ ኤፕስቲን መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ፍርድ ቤት ክርክር አምርቶ የሚያውቅ ሲሆን በዋናነት ከባለቤታቸው ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ያስተዋወቋቸው ኤፕስቲን ነው የሚሉ ፅሁፎች እንዲታረሙ በሚል በተለያዩ ጊዜያት ፍርድ ቤት አምርተዋል።
"ጠበቆቼ እና እኔ እነዚህን መሠረተ ቢስ ውሸቶች በስኬት ተዋግተናል፤ እናም ወደ ኋላ ሳንል ስሜን መጠበቃችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።















