ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ ዛሬ የምናውቀውን ቅርጿን ለመያዝ በግዢ የጠቀለለቻቸው ግዛቶቿ ታሪክ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዴንማርክ ከፊል ግዛት የሆነችውን የአርቲክ ደሴት ግሪንላንድ ላይ ዐይናቸውን ሲጥሉ የታሪክ ተመራማሪዎች ደግሞ አሜሪካ መሬት መግዛት የታሪክ መስፋፋትን እያጤኑ ነው።
በታሪክ "ዋሽንግተን እንደ ግሪንላንድ ሁሉ በኃያላን እጅ ከመውደቃቸው በፊት እነዚህን ግዛቶች መቆጣጠር አስፈላጊ ነው ትላለች" ይላሉ በሚሲሲፒ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ተመራማሪው ጄይ ሳክስተን ።
ትራምፕ ለደኅንነት ሲሉ ግሪንላንድን አሜሪካ "ባለቤት" ማድረግ እንዳለባት ይወተውታሉ። በአንድ ወቅትም በኃይልም ቢሆን ግሪንላንድን የግላቸው ለማድረግ እየተዘጋጁ እንደሆነ የተናገሩት ትራምፕ፤ አሁን ላይ "አስቸኳይ ድርድር" እና "ኃይል አልጠቀምም" እያሉ ነው።
ከዚህ በታች ባለፉት ሁለት ክፍለ ዘመናት አሜሪካ ድንበሯን ለማስፋፋት የገዛቻቸው ግዙፍ ይዞታዎች ይቀርባሉ።
የሊዊዚያና ግዢ (1803)
ፕሬዝዳንት ቶማስ ጄፈርሰን በአውሮፓውያኑ 1803 የሊዊዚያናን ግዛት ከፈረንሳይ ለመግዛት መወሰኑ ሁለት ሚሊዮን ስኩየር ኪሎ ሜትር መሬት ለማግኘት ወሳኝ ምዕራፍ ነው። የሊዊዚያና ግዢ ለአዲሲቷ አገር እና አኅጉራዊ ኃያል ለመሆን ላደረገችው ሽግግር ቁልፍ ነው።
የሊዊዚያና ግዛት ለፈረንሳይ የሰሜን አሜሪካ ትልቁ የቅኝ ግዛት ይዞታዋ ነበር። ይሁን እንጂ በፈረንሳይ ቁጥጥር ስር በነበረችው በዛሬዋ ሄይቲ በቀድሞ ስሟ ሴንት ዶሚኒግ የተነሳው ተደጋጋሚ የባሪያዎች አመፅ ከብሪታኒያ የጦርነት ስጋት ጋር ተዳምሮ የፈረንሳዩ መሪ ናፖሊዮን ቦናፓርት ግዛቱን ለአሜሪካ እንዲሸጥ ገፍቶታል።
ሊዊዚያና በወቅቱ ዛሬ ካላት ግዛት የሰፋች ነበረች። ዛሬ 15 የአሜሪካ ግዛቶች ተሸንሽነው የወጡባት እና ከሚሲሲፒ ወንዝ እስከ ሮኪ ተራሮች ድረስ የተዘረጋች ነበረች።
ይህን መሬት ማግኘት የዩናይትድ ስቴትን መፃኢ አገርነት ቶማስ ጄፈርሰን ለወጠነው የመስፋፋት ዕቅድ ቁልፍ ነበር።
የአሜሪካ እና የፈረንሳይ መንግሥታት በኅዳር 1803 አሜሪካ ሊዊዚያናን ለመግዛት 15 ሚሊዮን ዶላር ለመክፈል ተስማምተዋል። በዛሬ የዶላር ዋጋ ገንዘቡ 400 ሚሊዮን ዶላር ማለት ነው።
የሜክሲኮ ዝውውር (1948)
በአውሮፓውያኑ 1840 አብዛኛው የአሜሪካ ማኅበረሰብ በፓስፊክ ዳርቻ ወደ ምሥራቅ መስፋፋት ከፈጣሪ የተሰጠኝ ዕጣ ፈንታ ነው ብሎ ያምን ነበር። ይህም ሜክሲኮን ዋጋ አስከፍሏታል።
የአሜሪካ ድንበሯን የማስፋፋት እንቅስቃሴዋ ከዋነኛ ደጋፊዋ ውስጥ ኬምስ ኬ ፖልክ አንዱ ነው። በ1845 በዓለ ሲመቱ በኋላ በ1836 ነፃነቷን ያገኘችውን ቴክሳስን ለመቆጣጠር የነበረውን ግጭት ወርሷል።
ዋሽንግተን በ1845 ቴክሳስን ገንጥላ የአገሪቱ አካል አደረገቻት። በቀጣዩ ዓመት በአሜሪካ እና በሜክሲኮ ወታደሮች መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ የአሜሪካ ኮንግረስ ሜክሲኮ ላይ ጦርነት አውጇል። ይሁን እንጂ የጦርነቱ መንስኤ ከዚህ የሰፋ ነው።
የታሪክ ባለሙያ የሆኑት ጄይ ሳክስተን "አሜሪካ ያኔ የሜክሲኮ በነበረችው ካሊፎርኒያ ላይ ፍላጎት አሳይታ ነበር። ከእስያ ጋር ለሚደረግ የንግድ ልውውጥ ጥልቅ ውሃ ያላቸው ወደቦች አሏት፤ በአሜሪካ በኢኮኖሚ ከተነቃቁ አካባቢዎች አንዷ ነበረች" ይላሉ።
ይሁን እንጂ የትኛውም የሜክሶኮ መንግሥት ካሊፎርኒያን ለመሸጥ ተስማምቶ በሥልጣን እቀጥላለሁ ብሎ ማሰብ አይችልም ይላሉ ባለሙያው ሲያብራሩ።
አሜሪካኖች ጦርነቱን ካሸነፉ በኋላ ሁለቱ አገራት በ1848 "ጓዱላፔ ሂዳልጎ" የተባለውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
በመጨረሻም ዋሽንግተን 15 ሚሊዮን ዶላር፤ በዛሬው ገንዘብ 615 ሚሊዮን ዶላር በመክፈል መሬቱን ወደ ራሷ አዘዋወረች።
ይህ መሬት የዛሬዎቹን ካሊፎርኒያን፣ ኔቫዳ እና ዩታህን እንዲሁም የተወሰኑ የአሪዞና፣ የኮሎራዶ፣ የኒው ሜክሲኮ እና ዋዮሚንግ ግዛቶችን ያካተተ ነው።
ነገር ግን የታሪክ ተመራማሪው ሳክስተን የሜክሲኮ ወገን ጦርነቱን ባይሸነፍ ኖሮ መሬቱን ለመሸጥ አይስማማም ነበር ይላሉ።
"መሣሪያ ተደቅኖ የተደረገ ሽያጭ ነው" ይላሉ።
በአጠቃላይ ሜክሲኮ ከጦርነቱ በፊት ከነበራት ግዛት ግማሹን ስታጣ፤ አሜሪካ 1.360 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር መሬት አግኝታለች።
የላ መሲላ ሽያጭ (1853)
የአሜሪካ-ሜክሲኮ ጦርነት በ1848 ቢጠናቀቅም በሁለቱ አገራት መካከል ውጥረቱ ቀጥሏል። በ1854 በተጠናቀቀ ስምምነት የሁለቱ አገራት መንግሥታት በሜክስኮ ደቡብ ግዛት ስር የነበረች አነስተኛ ሰርጥ ሽያጭ ተስማምተዋል።
በሜክሲኳዊያን 'ቬንታ ደል ላ መሲላ' በመባል የሚታወቀው ሽያጭ አሜሪካ አኅጉር አቋራጭ የባቡር መስመር ለመገንባት የነበራት ዕቅድ አካል እና በከፊል የሜክሲኮ መንግሥት የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ በመግባቱ ነው።
የአሜሪካ መንግሥት 10 ሚሊዮን ዶላር በዛሬው ገንዘብ 421 ሚሊዮን ሶላር ከፍሎ 76,900 ስኩዌር ኪሎሜትር የሆነውብ መሬት ጠቅልሏል። ይህ መሬት በዛሬይቷ አሜሪካ ደቡባዊ ድንበር ለመሆን ችሏል።
የአላስካ ከሩሲያ ግዢ(1867)
በአውሮፓውያ 1967 ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዊሊያም ስወርድ የአርቲክ ግዛት የሆነችውን አላስካን ከሩሲያ ለመግዛት የያዘውን ቁርጠኝነት አብዛኞቹ አልተረዱትም ነበር።
ሚኒስትሩ መሬቱ ትልቅ ስልታዊ ዋጋ እንዳለው እምነት ነበረው። ይህም ብሪታኒያዊያን ሰሜን አሜሪካን እንዳይዘልቁ እና ለአሜሪካ ትልቅ የዓሳ ምርት በመስጠት ታይቷል።
ሩሲያ ለማስተዳደር ከፍተኛ ወጪ እያስወጣት ያለውን እርባነ ቢስ ዋጋ ያለው ግዛቷን አሽቀንጥራ እየጣለች እንደሆነ ታምን የነበረ ሲሆን፣ በጊዜው ዋነኛ ተቀናቃኟ የሆነችውን ዩናይትድ ኪንግደም ለምትሰነዝረው ጥቃት ስስ ቦታ ተደርጎ ይታይ ነበር።
ስወርድ 1,554,000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለውን መሬት በ7.2 ሚሊዮን ዶላር፤ በዛሬው ገንዘብ 158 ሚሊዮን ዶላር ከሩሲያ ለመግዛት ስምምነት ላይ ቢደርስም የአሜሪካ ሕዝብ አጨብጭቦ አልተቀበለውም።
ስምምነቱ "የስወርድ ሞኝነት" የሚል ስያሜ በተቃዋሚዎቹ ተሰጠው። ውዝግብ ያስነሳው ስምምነቱ በአምዛኛው አሜሪካዊም እርባነ ቢስ መሬት ስለመግዛቱ እምነት ነበረው።
ስምምነቱ ምንም እንኳ ተቃውሞ ቢገጥመውም ኮንግረስ ግዢውን በማፅደቅ አላስካ የዩናይትድ ስቴትስ አካል ሆነች። ሆኖም ግን የአሜሪካ ግዛት የሆነችው በ1959 ነው።
በመጨረሻም የስወርድ መዋዕለ ነዋይ ዋጋውን የከፈለው በአላስካ ወርቅ እና ትልቅ የነዳጅ ክምች ሲገኝ እና ግዛቱ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የወታደራዊ ጠቀሜታ ሲሰጥ ነው።
የአሜሪካ ቨርጂን ደሴቶች ግዢ (1917)
አሜሪካ ለመጨረሻ ጊዜ ግዛት የገዛችው ከዴንማርክ ነው። በጊዜው የዴኒሽ ዌስት ኢንዲስ ተብሎ የሚታወቅ አካባቢ በካሪቢያን የሚገኙ የደሴቶች ስብስብ ሲሆን፣ አሜሪካ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ ዓይን ውስጥ የገባ ነው።
ዊሊያም ስወርድ ይህን አካባቢም ሰላማዊ የማስፋፋት ዕቅዱ ቁልፍ ስፍራ አድርጎ አይቶታል።
ዛሬ የአሜሪካ ቨርጂን ደሴቶች ተብለው ከሚታወቁት ሦስት ዋነኛ ደሴቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የሴንት ቶማስ ወደብ በዋናነት ዐይን ውስጥ የገባ ነው። ካሪቢያንን ለመቆጣጠር ወደቡ ዋነኛ ማዕከል ይሆናል የሚለው አንዱ ምክንያት ነው።
በዚህ ወቅት ዴንማርክ በደሴቶቹ ፍላጎቷ እያሽቆለቆለ ነበር። በደሴቱ ግዙፍ የስኳር እርሻ በመመሥረት ከአፍሪካ በአውሮፓ ነጋዴዎች በተሸጡ ባሪያዎችን ታሠራ ነበር።
በዓለም ገበያ የስኳር ዋጋ መቀነስ ሲጀምር የዴንማርክም እርሻውን የማስቀጠል ፍላጎት አብሮ ቀነሰ።
በ1867 ሁለቱ አገራት ሁለቱን ደሴቶች በ7.5 ሚሊዮን ዶላር፤ በዛሬ ገንዘብ 164 ሚሊዮን ዶላር ለመግዛት ቅድመ ስምምነት ላይ ደረሱ። ይሁን እንጂ ይህ ስምምነት የአሜሪካ ኮንግረስ ሊያፀድቀው ባለመቻሉ ከሸፈ።
የአንደኛው የዓለም ጦርነት መፈንዳት እና የጀርመን ስርጓጅ መርከቦች በአሜሪካ መርከቦች ላይ የደቀኑት ስጋት ዋሽንግተን ፍላጎቷን አንድታድስ አድርጓታል።
ጀርመን ዴንማርክን በመውረር ደሴቶቹን ትቆጣጠራለች የሚለው ፍርሃት እንዲሁም ሴንት ቶማስ ያለው ስልታዊ ጠቀሜታ ዋሽንግተንን አነሳስቷል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ድረ ገፅ መረጃ የፕሬዝዳንት ውድሮው ዊልሰን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴንማርክ ደሴቶቹን ለአሜሪካ የማትሸጥ ከሆነ በሌላ ከመያዛቸው በፊት አሜሪካ ደሴቶቹን እንደምትቆጣጠር ማስጠንቀቃቸውን ይገልፃል።
በዴኒሽ ዓለም አቀፍ ጥናት ኢንስቱትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ለሆኑት አስትሪድ አንደርሰን በደሴቶቹ እና አሁን እያየነው ባለው የግሪንላንድ ሁኔታ ትይዩ አድርጎ አለማየት አስቸጋሪ ነው።
"አሁን ግሪንላንድን በተመከተ እየሰማን ያለነው ያስተጋባል። ምክንያቱም አሜሪካ ያለችው 'ሽጪልኝ አሊያም እንወርሻለን' ነው'" ይላሉ።
በአውሮፓውያኑ 1917 ሁለቱ አገራት ስምምነት የደረሱ ሲሆን፤ የካሪቢያን ደሴቶቹን በ25 ሚሊዮን፤ በዛሬ ገንዘብ 630 ሚሊዮን ዶላር ሽያጭ ተስማምተዋል።
በዚህ ስምምነት አካል ዴንማርክ በግሪንላንድ ፖለቲካዊ እና ኦኮኖሚያዊ ጥቅሟን ስታስፋፋ አሜሪካ እንዳትቃወማት ተስማምተዋል።