የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ፍጥጫ ያሳሰባት አሜሪካ ንግግር እንዲጀመር ጥሪ አቀረበች

በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል እየበረታ ያለው ውጥረት ያሳሰባት አሜሪካ ሁለቱ አገራት ከግጭት ተቆጥበው ወደ ንግግር እንዲመለሱ ጠየቀች።
በትግራይ እና በአዋሳኞቹ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት ተባብሷል።
በዚህም ሳቢያ የአሜሪካ መንግሥት ባወጣው በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ከሚካሄደው ጦርነት በተጨማሪ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ድንበር ተሻጋሪ ውጥረት እየተባባሰ መሆኑን እና አጠቃላይ ቀጣናውን የሚጎዳ መሆኑን ገልጿል።
የአሜሪካ መግለጫ የወጣው የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት እና አጋሮቹ ወደ ትግራይ ዘልቀው በመግባት የክልሉን ዋና ከተማ ከተቆጣጠሩ እና ኤርትራ የምትሳተፍበት በግብፅ የሚካሄደው ስብሰባ መጀመሩን ተከትሎ ነው።
በኤርትራ ይደገፋሉ የሚባሉት የህወሓት ኃይሎች ከሌሎች አማጺያን ጋር ጥምረት በመፍጠር የኢትዮጵያ መንግሥትን ለመጣል የጀመሩት ጥቃት ከአስር ቀናት በላይ የቆየ ሲሆን፣ በበርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ ተዘግቧል።
በጦርነቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራ የህወሓት ኃይሎችን እየደገፈች መሆኑን በመግለጽ ሲከስስ የነበረ ከመሆኑ በተጨማሪ የአፋር ክልል ባለሥልጣናት የኤርትራ ወራደሮች ድንበር ተሻረግው ጥቃት መክፈታቸውን ሲገልጹ ነበር።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግንኙነታቸው ከወዳጅነት ወደ ጠላትነት ተሸጋግሮ ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች መቀለን ተቆጣጥረው ወደ ሌሎች አካበቢ እየተንቀሳቀሱ ባለበት ጊዜ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ፍጥጫ በቀጣናው ላይ ተጽዕኖ እንዳለው አመልክቷል።
የአፍሪካ ቀንድ ሌላ ወታደራዊ ግጭት እና ሰብዓዊ ቀውስ መሸከም አይችልም ያለው የአሜሪካ መንግሥት፤ በሁለቱ አገራት መካከል ግጭት የሚከሰት ከሆነ "አሜሪካ ከአገራቱ ጋር በጋራ ጥቅሞች ላይ የምደታርገውን ትብብር ይጎዳዋል" ብሏል።
"ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የጎረቤቶቻቸውን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲያክብሩ እና ከግጭት ተቆጥበው ወደ ንገግር እና ትበብር እንዲመለሱ" በመጠየቅ በአውሮፓውያኑ 2018 የተፈረመውን የሰላም ስምምነት እንዲያከብሩ ጥሪ አቅርቧል።
በመጀመሪያው የትግራይ ጦርነት ወቅት በአንድ ተሰልፈው የህወሓት ኃይሎችን የወጉት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት ግንኙነታቸው የተበላሸው ደም አፋሳሹን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ነው።
ከዚያም በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ሉዓላዊ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎቱን ይፋ ካደረገ በኋላ ሁለቱ አገራት ይፋ ወደ ወጣ ውዝግብ ውስጥ ገብተው ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና መገናኛ ብዙኃን የኤርትራ መንግሥት ህወሓትን እና ታጣቂ ኃይሎችን በመደገፍ የአገሪቱን ሰላም ለማናጋት እየሠራ መሆኑን በመግለጽ ሲከስሱ ቢቆዩም ኤርትራ ግን ክሱን በተደጋጋሚ አስተባብላለች።
ከሁለት ሳምንት በፊት የኢትዮጵያን ፌደራል መንግሥት መጣል ዓላማቸው ያደርጉ አማጺ ቡድኖች ጥምረት መፍጠራቸውን ተከትሎ በህወሓት ኃይሎች ወታደራዊ ዘመቻ መከፈቱን ተከትሎ የኤርትራ ኃይሎች ድንበር አልፈው መግባታቸውን ሲገልጽ ቆይቷል።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት አስር የኤርትራ ዲፕሎማቶችን ከአዲስ አበባ ሲያባርር ኤርትራ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኑነት አቋርጣለች። ይህም ለ20 ዓመታት ተቋርጦ ከስምንት ዓመት በፊት መልሶ የተጀመረውን የሁለቱን አገራት ግንኙነት እንዲቋረጥ አድርጎታል።
የገዢው ፓርቲ እና የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አብረሃም በላይ (ዶ/ር) ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት የኤርትራ ወታደሮች ኢትዮጵያን ድንበር አልፈው መግባታቸውን በመግለጽ የኢትዮጵያ መንግሥት አጸፋውን አንደሚመለስ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከሦስት አሥርት ዓመታት ገደማ በፊት በድንበር ይገባኛል ምክንያት ለሁለት ዓመታት የቆየ ደም አፋሳሽ ጦርነት ማድረጋቸው ይታወሳል።



































