ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ማርኮ ሩቢዮ ኩባ ለአሜሪካ ስጋት ናት ሲሉ ሃቫና በበኩሏ ሚኒስትሩ "ይዋሻሉ" ስትል ወነጀለች
ኩባ ለአሜሪካ "የብሔራዊ ደህንነት ስጋት" ናት፤ ሰላማዊ ስምምነት ላይ የመድረስ ዕድሉም "ከፍ ያለ አይደለም" ሲሉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ተናገሩ።
ሚኒስትሩ ይህንን አስተያየት የሰጡት ከ30 ዓመት በፊት በኩባ እና በፍሎሪዳ መካከል ተመትተው ከወደቁ ሁለት አውሮፕላኖችን ጋር በተያያዘ የቀድሞው የኩባ መሪ ራውል ካስትሮ ላይ የአሜሪካ ዜጎችን ለመግደል ማሴር እና ሌሎች ወንጀሎችን የያዘ ክስ ከመሠረተች ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ሩቢዮ የዋሽንግተን ምርጫ "ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ" እንደሆነ ቢናገሩም፣ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸውን ከማንኛውም አደጋ የመጠበቅ መብት እና ግዴታ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድሪጌዝ ሩቢዮን "ሐሰተኛ" ሲሉ በመወንጀል አገራቸው ለአሜሪካ ስጋት ሆና እንደማታውቅ ተናግረዋል።
ሩቢዮ ሐሙስ ዕለት ለጋዜጠኞች ዲፕሎማሲ "ከኩባ ጋር ያለን ምርጫ ነው" ብለዋል፤ ነገር ግን "እውነቱን ለመናገር፣ አሁን ከማን ጋር እየተነጋገርን እንደሆነ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ የመከሰት ዕድሉ ከፍ ያለ አይደለም" ብለዋል።
በተጨማሪም ኩባን "በመላው ቀጣናው ውስጥ የሽብርተኝነት ግንባር ቀደም ደጋፊ ከሆኑት መካከል አንዷ" በማለት ከሰስዋታል።
የኩባው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮድሪጌዝ በበኩላቸው በኤክስ ገጻቸው ላይ የሩቢዮን ንግግር አስተባብለዋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩቢዮ "ወታደራዊ ጥቃትን ለማነሳሳት" እየሞከሩ ነው ሲሉ ተችተው የአሜሪካ መንግሥት "ያለ ርህራሄ እና ስልታዊ በሆነ መንገድ" አገራቸውን እያጠቃ መሆኑን በመግለጽ ወንጅለዋል።
አሜሪካ አገሪቱ ላይ ማዕቀቦችን የጣለች ሲሆን ከቅርብ ወራት ወዲህ ደግሞ ወደ ኩባ ነዳጅ እንዳይገባ አግዳለች። በዚህም ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ እና የምግብ እጥረት ተፈጥሯል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ረቡዕ ዕለት ለኩባ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፤ "ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአሜሪካ እና በአዲሷ ኩባ መካከል አዲስ የትብብር መንገድ እየጠረጉ ነው" ብለዋል።
ሩቢዮ አክለውም ኩባ ለሰብዓዊ እርዳታ እንዲውል አሜሪካ ለመስጠት ያቀረበችውን የ100 ሚሊዯን ዶላር ድጋፍ ለመቀበል መስማማቷን ተናግረዋል።
ኩባ በተደጋጋሚ በይፋ የአገሪቱን ኮሚኒስት አገዛዝ ከሥልጣን ለማስወገድ ሲዝቱ ነበር።
ረቡዕ ዕለት የቀድሞውን የኩባ ፕሬዝዳንት ላይ የተመሰረተው ክስ አንዳንዶች ትራምፕ በጥር ወር የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ስር የማዋላቸው ቀጣይ ክፍል አድርገው ተመልክተውታል።
ጋዜጠኞች ካስትሮን ወደ አሜሪካ አምጥቶ ክሳቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ ይቻል እንደሆን ሲጠየቁ ሩቢዮ "እዚህ እንዴት እንደምናመጣው አልናገርም፤ እዚህ የምናመጣው ከሆነ ለመገናኛ ብዙኃን ምን ዕቅድ እንዳለ ለምን እናገራለሁ?" ሲሉ መልሰዋል።
ረቡዕ ዕለት በማያሚ ክሱን ይፋ ያደረጉት ተጠባባቂ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቶድ ብላንቼ አሜሪካ "በራሳቸው ፈቃድ ወይም በሌላ መንገድ እዚህ እንደሚመጡ ጠብቁ" ብለዋል።
ሐሙስ ዕለት ሩቢዮ በኤክስ ገጻቸው ላይ እንዳስታወቁት አሜሪካ የኩባ ወታደራዊ ባለሥልጣን እህት የሆነችው አዲስ ላስትሬስ ሞሬራን በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታውቀዋል።
ሞሬራ የምትኖረው በፍሎሪዳ ሲሆን "በሃቫና የሚገኘውን የኮሚኒስትር አገዛዝ ትደግፋለች" ሲሉ ቱቢዮ ወንጅለዋታል።
በቁጥጥር ሥር የዋለችው በኢሚግሬሽን ሠራተኞች ሲሆን ወደ አገሯ እስክትባረር ድረስ በማረፊያ ቤት ትቆያለች ብለዋል።
ትራምፕ በኦቫል ኦፊስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኩባ "የወደቀች አገር" መሆኗን እና አስተዳደራቸው "በሰብዓዊነት ላይ የተመሰረተ" እርዳታ ለመስጠት እየሞከረ መሆኑን ተናግረዋል።
ኩባ-አሜሪካውያን "ወደ አገራቸው መመለስ" እና አገራቸውን ስኬታማ ለማድረግ ይፈልጋሉ ሲሉ ተናግረዋል።
"ሌሎች ፕሬዚዳንቶች ይህንን ለ50፣ 60 ዓመታት እየተመለከቱ መፍትሔ ሳይሰጡ ቆይተዋል፤ ይህንን የማስተካክለው እኔ እንደሆንኩ አምናለሁ፤ ስለዚህ በደስታ እሰራዋለሁ" ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።