አሜሪካ ወደ ፖላንድ ተጨማሪ 5,000 ወታደሮችን እንደምትልክ ትራምፕ አስታወቁ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፔንታጎን ወደ ፖላንድ 4,000 ወታደሮችን ለማሰማራት ይዞት የነበረውን ዕቅድ ከሰረዘ ከአንድ ሳምንት በኋላ ተጨማሪ 5,000 ወታደሮችን ወደ አገሪቱ እንደሚልኩ ተናገሩ።

ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ሲጽፉ ውሳኔው የተመሠረተው ባለፈው ዓመት በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ወቅት ድጋፋቸውን ከሰጧቸው የፖላንድ ፕሬዝዳንት ካሮል ናሮኪ ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ተጨማሪ ወታደሮቹ ቀደም ሲል የታቀደው የስምሪት አካል መሆን አለመሆናቸውን ወይም የተለየ ዘመቻ ስለመሆኑ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

ዋእት ሀውስ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በአውሮፓ የሚገኙትን የአገሪቱን ወታደሮች ቁጥር "ለአሜሪካ ቅድሚኣ ለመስጠት" በሚል ለመቀነስ ዕቅድ እንዳለው አስታውቆ ነበር።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ትራምፕ እና የጀርመን ቻንስለር ፍሪድሪክ መርዝ መካከል በኢራን ጦርነት የተነሳ በተፈጠረ አለመግባባት አሜሪካ 5,000 ወታደሮቿን ከአገሪቱ እንደምታስወጣ አስታውቃለች።

ትራምፕ ቀደም ሲል መርዝ አሜሪካ በኢራን ተደራዳሪዎች "ተዋርዳለች" በማለት የሰጡትን አስተያየት ተችተዋል።

ወደ ፖላንድ የሚንቀሳቀሱት ተጨማሪ ወታደሮች ከጀርመን የሚወጡት ይሁኑ ወይም የተለየ ቡድን እስካሁን ግልጽ አይደለም።

በተጨማሪም ዋሽንግተን የኔቶ አባል አገራት ኢራንን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንድትከፍት ለማስገደድ ከአሜሪካ ጎን ባለመቆማቸው ተችተዋል።

ከኔቶ አባል አገራት የተውጣጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አርብ ዕለት በስዊድን የሚሰባሰቡ ሲሆን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ይገኛሉ ተብሏል።

ሩቢዮ የኔቶ አጋሮች የዋሺንግተንን ሸክም እንዲጋሩ ጥሪ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከስብሰባው በፊት ቢቢሲ በኔቶ አባል አገር ላይ ጥቃት ቢሰነዘር አሜሪካ ልታዋጣ የምትችለውን ወታደር ልትቀንስ ትችላል የሚሉ ዘገባዎችን በሚመለከት ጥያቄ አቅርቧል።

ሩቢዮ "የተወሰኑት ጉዳዮች" በጉባዔው ላይ ተነስተው ውይይት ይደረግባቸዋል በማለት ትራምፕ በኔቶ አጋሮች ማዘናቸውን እና መበሳጨታቸውን እንደተጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።

ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ፖላንድ እንደሚልኩ ያስታወቁት የመከላከያ ሚኒስትሩ ወደ አገሪቱ 4,000 ወታደሮችን ለማሰማራት ተይዞ የነበረውን ዕቅድ በድንገት መቋረጡን ካስታወቁ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።

የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት በኋላ ላይ እንዳሉት የስምሪቱ መሰረዝ "ጊዜያዊ መዘግየት" እንደሆነ እና አሜሪካ በፖላንድ "ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል" እንደሚኖራት ተናግረዋል።

የፖላንድ ፕሬዚዳንት ናውሮኪ ለረጅም ጊዜ የትራምፕን ደጋፊ የነበሩ ሲሆን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከማድረጋቸው በፊትም የትራምፕን ድጋፍ አግኝተዋል።

የፖላንድ ፕሬዝዳንት በጥር ወር ከቢቢሲ ሬዲዮ 4 ቱዴይ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወቅት ትራምፕ ቭላድሚር ፑቲንን እና የዩክሬንን ጦርነት ማስቆም የሚችሉ ብቸኛው የዓለም መሪ ናቸው ብለው ነበር።

ትራምፕ ቀደም ሲል የኔቶ አባል አገራትን እና የአውሮፓ መሪዎችን ቢተቹም፣ ናውሮኪ አሁንም በአውሮፓ ውስጥ ላለው ደህንነት አሜሪካ ዋስትና መሆኗን አጥብቀው ተናግረዋል።

በርካታ የሪፐብሊካን ሕግ አውጪዎች ትራምፕ የአሜሪካ ወታደሮችን ከጀርመን ለማስወጣት መወሰናቸውን ለሩሲያ የተሳሳተ መልዕክት ያስተላልፋል በሚል ተችተዋል።

የአሜሪካ በጀርመን ያሏት ወታደሮች ብዛት በአውሮፓ ግዙፉ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከ36,000 በላይ የሠራዊቱ አባላት ይገኛሉ።

በጣሊያን ደግሞ 12,000 እንዲሁም በዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ 10,000 ወታደሮች አሉት።