የአውሮፓ ሙቀት ከ1,300 ሰዎች ሞት ጋር እንደሚያያዝ የዓለም ጤና ድርጅት ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ባለፉት ጥቂት ቀናት ከ1,300 በላይ ሰዎች ለመሞታቸው ምክንያቱ የአውሮፓ የሙቀት ወጀብ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
በአውሮፓ አገራት ከወቅቱ ቀድሞ የተከሰተው የበጋ ሙቀት ከዚህ ቀደም ከነበረው የባሰ መሆኑ ተገልጿል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሞቶች ለመመዝገባቸው ምክንያቱ ከፍተኛ ወበቅ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ አድርጓል።
ትናንት እሑድ በመላው አህጉሪቱ የተመዘገበው ሙቀት ክብረ ወሰኖችን የሰበረ ነው። ጀርመን፣ ፖላንድ እና ቼክ ሪፐብሊክ ከፍተኛ ወበቅ ከተከሰተባቸው መካከል ተጠቃሽ ናቸው። የሙቀት ወጀቡ ወደ ምሥራቅ አውሮፓ እየተስፋፋም ይገኛል።
የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ከአውሮፓውያኑ ሰኔ 21 ጀምሮ የሞት መጠን መጨመሩ "ከአውሮፓ ከፍተኛ ሙቀት ጋር ትስስር አለው" ብለዋል።
"ሙቀት የሚያሳድረው ጫና 'ዝምተኛው ገዳይ' ይባላል። ሆኖም የአውሮፓ ቤቶች፣ መሥሪያ ቤቶች እና ትምህርት ቤቶች የተገነቡት ይሄንን መቋቋም በሚያስችላቸው መንገድ አይደለም" ሲሉም አክለዋል።
የፈረንሳይ ጤና ሚኒስቴር እንዳለው ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ጀምሮ ከተጠበቀው በላይ በሆነ መጠን ወደ 1,000 ተጨማሪ ሰዎች ሞተዋል።
ያልተጠበቁ ተብለው ከተመዘገቡት ሕልፈቶች መካከል ዕድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ይገኙበታል።
ቤታቸው ሳሉ የሚሞቱ ሰዎች መጠን 40% እንደጨመረ ተገልጿል።
ዶ/ር ቴድሮስ "በምድር ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየጋለች ያለችው አህጉር አውሮፓ ናት። ሙቀቱ ከዓለም አቀፍ አማካዩ በሁለት እጥፍ ጨምሯል" ብለዋል።
በአውሮፓ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች "በከፍተኛ ሙቀት ውስጥ እየኖሩ" መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው "በመቶዎች የሚቆጠሩ ሞተዋል፤ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል" ሲሉ ያለውን ሁኔታ አስረድተዋል።
በጀመርን ትናንትን ጨምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ከፍተኛ መጠን ያለው የሙቀት ወጀብ ተመዝግቧል። በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ሙቀቱ 41.7 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ደርሷል።
በፖላንድ ድንበር አቅራቢያ የሚገኘው ማዕከልም ተመሳሳይ መጠን ያለው ሙቀት መዝግቧል።
በቼክ ሪፐብሊክ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሙቀቱ 41.1 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ደርሷል።
በፖላንድ የተመዘገበው ሙቀትም ከዚህ ቀደም የነበረውን ክብረ ወሰን ሰብሯል። በስሉባይስ ከተማ 40.5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት ተመዝግቧል።
ለሙቀት ወበቁ መባባስ ምክንያቱ የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑን ዶ/ር ቴድሮስ ተናግረዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በአውሮፓ ከዓለም አቀፉ አማካይ በሁለት እጥፍ የሚልቅ ወበቅ መከሰቱን ጠቅሰው "በትውልድ ዘመን አንድ ጊዜ የሚከሰት የሙቀት ወጀብ አሁን በየዓመቱ እየታየ ነው" ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ በጤና ላይ የሚያሳድረውን ጫና ለመቋቋም፤ የአውሮፓ አገራት "ሙቀትን ያማካለ የጤና ማዕቀፍ ዕድቅ" እንዲተገብሩ አሳስበዋል።
የአውሮፓ አገራት ከሙቀት ወጀብ ጋር የተያያዙ የጤና እክሎችን ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰዱ ይገኛሉ።
በኔዘርላንድስ ሊካሄድ የነበረው 'ዳፍቀን.1' የሙዚቃ ፌስቲቫል ተሰርዟል።
በፓሪስ በሙዚቃ ፌስቲቫል እና በሕዝብ አደባባይ አልኮል መጠጣት ተከልክሏል።
የሙቀት ወጀቡ ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ በፈረንሳይ 74 ሰዎች ውሃ ውስጥ ሰጥመው ሞተዋል።
የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ላውረንት ኑኔዝ አብዛኞቹ ሰዎች የሞቱት "ቁጥጥር በማይደረግባቸው ወንዞች እና ኩሬዎች ነው" ብለዋል።















