ሩሲያ በዩክሬን ከተማ ትምህርት ቤቶች፣ ቢሮዎች እና አውቶብሶችን በድሮን ደበደበች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ከሌሊቱ 11 ሰዓት ነበር። አና ሆሎቭቸንኮ በምሥራቅ ዩክሬን ዛፖሪዛዚያ ከተማ የመኖሪያ ሰፈሮችን ፍንዳታ ሲያናውጣቸው ነው ከእንቅልፏ የነቃችው።

በሳምንታት ውስጥ በከተማዋ የፀጥታ ሁኔታው አሽቆልቁሏል። ዛፖሪዛዚያ ከጦር ግንባር 24 ኪሎ ሜትር ገደማ የምትርቅ ብትሆንም የ750 ሺህ ሰዎች መኖሪያ ናት። ጦርነቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደቀረበ ይሰማል።

ከአንድ ሰዓት በኋላ በሁለተኛ ዙር ጥቃት ድሮኖች በአና ቤት ላይ በርረዋል። ድሮኖቹን የዩክሬን አየር መከላከያ ለማክሸፍ ሞክሯል። "ከዚህ በኋላ እንደማልተኛ ገባኝ እና ለሥራ መዘጋጀት ጀመርኩ" ትላለች አና።

ባለፉት ሳምንታት በርካታ አውቶብሶች፣ የነዳጅ ማደያዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግሥት ቢሮዎች እና መኖሪያ ቤቶች በሩሲያ ድሮኖች እና ቦምቦች ተደብድበዋል።

የከተማዋ ጊዜያዊ ከንቲባ ረጂና ካራቼንኮ በጣም ጠንካራ ጥቃት በተፈፀመበት ጊዜ "ወደ መጠለያ አልሄድኩም። ይሁን እንጂ ድምፁ እየገነነ ሲመጣ በመፀዳጃ ቤት ተከለልኩ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

'ሻሂድ' ድሮን ከአና ቢሮ ብዙም ሳይርቅ ከባድ ፍንዳታ በማሰማት ወድቋል። ሌላኛው ድሮን ደግሞ ገመድ ላይ ጉዳት በማድረስ ኢንተርኔት እንዲቋረጥ አድርጓል። "ይህ በዛፖሪዛዚያ የተለመደ ቀን ነው" ትለላች።

ከተማቸው የዛፖሪዛዚያ ግዛት የአስተዳደር ከተማ ሲሆን በዩክሬን ደቡብ እና ምሥራቅ ከሚገኙ አምስት ግዛቶች ውስጥ አንዱ ነው። አካባቢው ሩሲያ የይገባኛል ጥያቄ የምታነሳበት ነው።

የአውሮፓ ትልቁ የሆነው የዛፖሪዛዚያ የኒውክሌር ጣቢያ ከከተማው 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሩሲያ ቁጥጥር ስር በሚገኘው የግዛቱ ክፍል ላይ ይገኛል።

የሩሲያ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ተከትሎ የዛፖሪዛዚያ ከተማ ምክር ቤት የተባባሰው ሁኔታ ላይ ለመነጋገር መሬት ውስጥ በተቀበረ መጠለያ ውስጥ ተሰብስቧል።

"ጠላት ንፁሃን ላይ፣ የሕዝብ ትራንስፖርት፣ የግለሰብ አውቶብሶች፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመኖሪያ ሕንፃዎች እና ሕፃናት ላይም ሳይቀር ሽብሩን አጠናክሯል" ብለዋል ከንቲባዋ።

በመላው ከተማዋ ሰፊ እንቅስቃሴ ባለበት እና በተጋላጭ ስፍራዎች የአደጋ ጊዜ መጠለያዎችን ለመገንባት እና ፀረ ድሮን መረቦችን ለመዘርጋት እቅዶች እንደተነደፉ ከስብሰባው በኋላ ጊዜያዊ ከንቲባዋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"በግሌ በጣም ፈርቻለሁ" ይላሉ። አንዳንዴ ቤታቸው ወለል ላይ እንደሚተኙ ሲገልፁ፤ "በተለመደ ረጅም ሕንፃ ሰባተኛ ወለል ላይ እኖራለሁ። በግሌ መጠለያ እና 10 ጠባቂዎች የሉኝም። መደበኛ ሕይወት ነው የምኖረው።"

የዩክሬን ጦር የሩሲያ ኃይሎች ከከተማዋ በተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ አድርጓል። ይሁን እንጂ በዛፖሪዛዚያ ጥቃቶች ተባብሰዋል።

ለዚህም ምክንያቱ አብዛኞቹ ጥቃቶች የሚፈፀሙት አንድ ሰው ብቻ በሚመለከታቸው አነስተኛ እና ገዳይ ድሮኖች መሆኑ ነው። እነዚህ ድሮኖች ከዚህ ቀደም ወደ ከተማዋ መግባት አይችሉም ነበር።

የሩሲያ ኃይሎች የረጅም ርቀት ድሮኖች አነስተኛ ድሮኖችን እንዲሸከሙ በማድረግ ከዚያም ድሮኖቹ ተሰራጭተው ዒላማቸውን ይመታሉ። እነዚህ ድሮኖች ያለ ተሸካሚ በራሳቸው አቅም የሚደርሱ እንዳልሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

መረጃቸውን ለመጥለፍ ከባድ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው እና በራዲዮ ግንኙነት መልዕክት የሚለዋወጡ መሆናቸው ደግሞ ለመቀልበስ አስቸጋሪ አድርጓቸዋል።

የዩክሬን ባለሥልጣናት በሰኔ ወር መጨረሻ ሳምንት ብቻ 884 የሩሲያ ድሮኖችን ማክሸፋቸውን ተናግረዋል።

ምንም እንኳ የሩሲያ ኃይሎች በዛፖሪዛዚያ ደቡብ በኩል ቢያፈገፍጉም፤ በሌሎች አካባቢዎች ከዚህ ቀደም ከበራቸው ፍጥነት በመቀነስ እየገሰገሱ ነው።

ግስጋሴው ዩክሬን በሩሲያ ግዛቶች ላይ ውጤታማ የድሮን ጥቃቶች ተሸፍኗል።

አሁን በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ባሉበት የሚቆዩ ሲሆን የዛፖሪዛዚያ ሕዝብ ከአራት ዓመት ከመንፈቅ ጦርነት በኋላ ከስጋቱ አልተላቀቀም።

"ምግብ እና ነዳጅ አለን፤ ለምን ለቅቀን እንወጣለን? ምንአልባት በቀላሉ የምደነግጥ አይነት ሰው አይደለሁም" ትለላች አና።

ከተማውን ለቅቆ የመውጣት ሀሳብ አስባ እንደምታውቅ የምታምነው አና፤ ዛፖሪዛዚያ በሩሲያ የምትወድም ሌላኛዋ ከተማ እንድትሆን አትፈልግም።

"በደኅንነት ለመቆየት እየሞከርን ነው፤ እና እስከ ድላችን ድረስ ለመቆየት የተቻለንን ሁሉ እያደረግን ነው።"