ፌስቡክ እና ኢንስታግራም "ሱስ በማስያዛቸው" እንደሚቀጡ የአውሮፓ ኅብረት ገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ፌስቡክ እና ኢንስታግራምን የሚያስተዳድረው ሜታ፤ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹን "ሱስ አስያዥ" አሠራር ካልቀየረ በስተቀር ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣልበት የአውሮፓ ኅብረት አስጠነቀቀ።

የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ያደረገው ምርመራ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት እንደሚያሳየው፤ ማኅበራዊ ሚዲያዎቹ "ማቆሚያ ለሌለው ዕይታ (scroll)" የሚያጋልጥ አሠራር አላቸው።

ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን በራሳቸው ይሁንታ በማጫወት (autoplaying) እና ተጠቃሚዎች ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ በገጾቹ ላይ እንዲቆዩ ለማስገደድ ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረገ ይዘት በመግፋት (personalised recommendations) ተጠያቂ ተደርገዋል።

የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ በተለይም ልጆችን እና ታዳጊዎችን ሱስ በማስያዝ ሲወነጀሉ ቆይተዋል።

ሜታ ጉልህ ማሻሻያ የማያደርግ ከሆነ በዓመታዊ ዓለም አቀፍ ትርፉ ላይ የ6 በመቶ ቅጣት እንደሚጣልበት የአውሮፓ ኅብረት ገልጿል።

የሜታ ቃል አቀባይ በምክር ቤቱ ድምዳሜ እንደማይስማሙ ለቢቢሲ ገልጸው "ወጣቶችን ለመጠበቅ የወሰድናቸውን ቁልፍ ማሻሻያዎች ከግምት አላስገባም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት እንዳለው፤ ባደረገው ምርመራ መሠረት ማለቂያ የሌለው ይዘት በመልቀቅ "አእምሮ ያለ ማቋረጥ መረጃ እንዲሰበስብ" በማድረግ ለጤና እክል የሚዳርግ አሠራር ተዘርግቷል።

የአውሮፓ ኅብረት የቴክኖሎጂ ኃላፊ ሄና ቪርኩነን "ማኅበራዊ ሚዲያዎች የአውሮፓውያንን አካላዊ እና አእምሯዊ ጤና መጠበቅን ቅድሚያ ሊሰጡት ይገባል" ብለዋል።

ሜታ፤ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ምን ያህል አደጋ እንደጋረጡ ማየት እንዳልቻለ ተናግረዋል።

በተለይም ምሽት ላይ ልጆች ረዥም ጊዜ በማኅበራዊ ሚዲያዎቹ እንደሚያጠፉ ጠቅሰዋል።

እንደ ሪልስ (Reels) እና ስቶሪስ (Stories) ያሉ ይዘቶች ከልክ ያለፈ ጊዜ በገጾቹ ላይ እንዲጠፋ እንደሚያበረታቱ ተናግረዋል።

ሜታ ያስቀመጣቸው የደኅንነት ጥበቃ አሠራሮች መቂ አለመሆናቸውን ኅብረቱ አስታውቋል።

ታዳጊዎች በገጾቹ ያላቸውን ቆይታ ለመገደብ የተዘረጋው አሠራር ውጤታማ እንዳልሆነ ተገልጿል።

ሜታ፤ ወላጆች ቁጥጥር እንዲያደርጉ የሚያስችል አሠራር ቢኖረውም፤ ወላጆች ጊዜ እና የቴክኖሎጂ እውቀት ከሌላቸው ሊተገር እንደማይችልም የአውሮፓ ኅብረት ጠቁሟል።

ሜታ በበኩሉ የታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች "ወላጆች ቁጥጥር እንዲያደርጉ የሚያስችሉ" እንደሆኑ እና ምሽት ላይ የስክሪን ቆይታን በ15 ደቂቃ የሚገድቡ መሆናቸውን ገልጿል።

ቃል አቀባዩ "ወጣቶች ደኅንነታቸው የተጠበቀ እና በመልካም ተሞክሮ የሚያልፉ መሆን እንዳለባቸው ከአውሮፓ ኅብረት ጋር እንስማማለት። ገንቢ መሆነ መንገድ ውይይት እንቀጥላለን" ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የማኅበራዊ ሚዲያ ቁጥጥሩን እንዲያጠናክር ከአባል አገራቱ ጫና እየተደረገበት ነው። ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ታዳጊዎች የማኅበራዊ ሚዲያ ክልከላ መጣልን ጨምሮ ሌሎችም የቁጥጥር እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው የገለጹም አገራት አሉ።