በፈረንሳይ በተካሄደ አዲስ ተቃውሞ ላይ በተፈጠረ ግጭት 1,300 ገደማ ሰዎች ታሰሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ቅዳሜ ዕለት በመላው ፈረንሳይ ከተካሄደው ተቃውሞ በኋላ ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ 1,300 ገደማ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

የትናንቱ ሰልፍ ቀኑን ሙሉ በአብዛኛው ሰላማዊ የነበረ ሲሆን ኋላ ላይ ግን ፖሊስ መዲናዋን ፓሪስን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ እና ውሃ ተጠቅሟል።

በማርሴይ ከተማ ተቀምጠው የነበሩ የመንገድ ማገጃዎች ተቃጥለዋል፤ በቦርዶ ደግሞ ተቃዋሚዎች ከመደብር ሰሌዳዎችን ሲነቅሉ ታይተዋል።

ይህም ቢሆን ባለሥልጣናቱ የባለፈው ሳምንቱ ዓይነት መጠን ያለው አመፅ እና ዝርፊያን ማስቀረት ችለዋል። የባለፈው ሳምንቱ ክስተት በፈረንሳይ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ እጅግ አስከፊው ሁከት ሆኖ ተመዝግቧል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ቅዳሜ ዕለት ተቃውሞ ያደረጉ ሰዎች ብዛት 410,000 ገደማ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን የሠራተኛ ማኅበራት ግን ቁጥሩ ወደ 800,000 እንደሚጠጋ ተናግረዋል።

ሰልፍ የተደረገው የኑሮ ውድነት እና የትምህርት ቤቶች ደረጃ መውረድን በመቃወም ነው። ባለፈው ሳምንት በነበረው ተቃውሞ ላይ የፖሊስ ቁጥር ከተቃዋሚው አንሶ የነበረ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የንግድ ተቋማት የተዘረፉበት እና ሕንጻዎች የተቃጠሉበት ሁኔታም ተፈጥሯል።

በትናንቱ ተቃውሞ ላይ ይህንን ዓይነቱን ሁኔታ ለመከላከል 70,000 የሚጠጉ የፖሊስ አባላት የተሰማሩ ሲሆን በበርካታ ከተሞችም ገደቦች ተጥለዋል።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ እውቅና ባላቸው የሠራተኛ ማኅበራት የሚዘጋጁ ሰልፎች ብቻ እንዲፈቀዱ የሚያደርግ ድንጋጌ አውጥተዋል።

ከንብረት ውድመት፣ እሳት ቃጠሎ እና ዝርፊያ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የታሰሩ ሲሆን በፍርድ ቤቶችም ፈጣን የችሎት ውሎ እየተካሄደ ነው።

ትናንትና በፓሪስ ሲካሄድ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ማጠናቀቂያ ላይ በተቃዋሚዎች እና ፖሊሶች መካከል ግጭት ተፈጥሯል። በሥፍራው የነበረው ፖሊስ የተንቀሳቀሰው የተደራጁ ወንጀሎች እና ፀረ ሽብርተኝነት ላይ ከሚሠራ የልዩ ኃይል ጋር በመሆን ነው።

የተወሰኑ ተቃዋሚዎች መንገድ ሲዘጉ እና ፖሊሶች ላይ የተለያዩ ነገሮችን ሲወረውሩ ታይቷል። ፖሊስም ፊታቸውን ሸፍነው የመኪና መሸጫ ሥፍራ መስኮቶችን ይሰባብሩ የነበሩ ወጣቶችን በዱላ ሲደበድቡ ተስተውሏል።

የፈረንሳይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሎረን ኑኔዝ፣ "ከሰልፈኞቹ ኋላ በሁከት ፈጣሪነት ወደ 500 ገደማ ግለሰቦችን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ አክራሪ አክቲቪስቶች ተሰባስበው ነበር" ማለታቸውን የዜና ወኪሉ ኤኤፍፒ ዘግቧል።

በደቡባዊቷ የወደብ ከተማ ማርሴይ የቆሻሻ መጣያዎች የተቃጠሉ ሲሆን ብረት በመጠቀመም መንገድ እንዲዘጋ ተደርጓል። በፈረንሳይ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ በሆነችው ማርሴይ፣ አንድ የፖሊስ መኪና በእሳት እየነደደ በነበረ የመንገድ ማገጃ ውስጥ ሲያልፍ ታይቷል።

በደቡባዊቷ የቦርዶ ከተማ ደግሞ ጥቁር የለበሱ እና ፊታቸውን የሸፈኑ ተቃዋሚዎች መንገድ ለመዝጋት እንዲችሉ ከአንድ ሕንጻ ላይ ጣውላዎችን ሲነቅሉ ታይተዋል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሎረን ኑኔዝ፣ በቀኑ ማብቂያ ላይ አንድ ሺህ ገደማ ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ የተናገሩ ሲሆን ቁጥሩ እንደሚጨምርም ጠቁመዋል።