ማኅበራዊ ኂስን በሳቅ አዋዝቶ የሚያቀርበው ኮሜዲያን ምናለ ያረጋል

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ኮሜዲያን ምናለ ያረጋል በዩቲዩብ የሚያቀርበው "ዘና ዜና" የተሰኘው የኮሜዲ ሥራው በተመልካቾቹ ዘንድ ተወዳጅ ሆኖለታል።

ይህ ትርዒት እና በመድረክ የሚያቀርባቸው የስታንድፕ ኮሜዲ ሥራዎቹ ዕውቅናን አስገኝተውለታል። በሥራዎቹ "ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጉዳዮችን፣ አጓጉል አሠራሮችን፣ ሕዝብ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ሃሳቦችን" እንደሚያነሳ ይናገራል።

አዲስ አበባ በተለምዶ "ፂዮን ሆቴል" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወልዶ ያደገው ምናለ በ2007 ዓ.ም. ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ድግሪውን አግኝቷል። ይሁን እንጂ የምሕንድስና ሙያ ከልጅነቱ አንስቶ ትወና ላይ ያረፈውን የምናለን ቀልብ መሻር አልቻለም። የተመረቀበትን ሙያ ወደ ጎን አስቀምጦ፣ ተዋናይ የመሆን ህልሙን ከፊት አድርጎ ቀጠለ።

"ምንም እንኳን በተመረቅሁበት ሙያ የመሥራት ፍላጎት ቢኖረኝም ብዙ ጥረት አላደረግሁም።...ተምሬ መጨረስ አለብኝ በሚለው አስተሳሰብ ውስጥ ነው ትምህርቴን የጨረስኩት" ሲል ይናገራል።

ኮሜዲያን ምናለ በለጋ ዕድሜ ላይ ሳለ ጀምሮ ይመኝ የነበረው በተለያዩ ፊልሞች እና ድራማዎች ላይ መሳተፍ፣ አንቱ የተባለ ተዋናይ መሆን ነው። ዛሬ ላይ የሚታወቅበትን ኮሜዲያንነት አስቦትም፣ አልሞትም አያውቅም።

በእርግጥ አባቱ አቶ ያረጋል የኮሜዲ አድናቂ ነበሩ። የተለያዩ የኮሜዲ ሥራዎችን በሲዲ እያመጡ አብረው ቢመለከቱም ምናለን የሚነሽጠው ከኮሜዲው ይልቅ ትወና ነበር።

ስለዚህ ሁኔታ ሲያስታውስ "እውነት ለመናገር ኮሜዲያን እሆናለሁ ብዬ በሕይወቴ አስቤ አላውቅም። ተዋናይ የመሆን ነው ህልሙ የነበረኝ፤ ኮሜዲያን ተብዬ እጠራለሁ የሚል ሃሳብ አልነበረኝም" ይላል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ለነበረው ምናለ "የማለዳ ኮኮቦች" የተሰኘው የትወና ውድድር መጀመሩ ትልቅ ብሥራት ነበር።

ከልጅነት አንስቶ ሲመኘው ለነበረው ተዋናይ የመሆን ፍላጎት በዚህ ውድድር መሳተፍ ማለት ውል ባለው መንገድ መጓዝ መሆኑን በመረዳት ተመዘገበ። ከአያሌ ተወዳዳሪዎች ነጥሮ በመውጣት ሦስተኛ ደረጃን ይዞ የ40 ሺህ ብር ሽልማቱን ጨብጦ ከህልሙ ጋር ለመገናኘት የሚደረገውን ጥረት አሳለጠ።

ከዚህ ውድድር በኋላ "ወዲያው አልጋ በአልጋ ሆኖ መሪ ተዋናይ መሆን፣ ጥሩ ተከፋይ ተዋናይ የምሆን መስሎኝ ነበር። እንደዚያ አልሆነም፤ የመጡልኝ ስክሪፕቶች ነበሩ ግን አብዛኞቹ ጥሩ ጥራት ያላቸው አልነበሩም" በማለት ከ10 ዓመት በፊት ያጋጠመውን ሁኔታ ያስታውሳል።

ከብዙ ጥበቃ በኋላ ግን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን የሚተላለፍ "የተቀበረው" በተሰኘ ተከታታይ ድራማ ላይ ተሳተፈ። "አትፍረድ" የሚል ፊቸር ፊልም ቀጠለ። ግሩም ኤርሚያስ ባዘጋጀው "የሱፍ አበባ" ፊልም ላይ ተወነ።

ከልጅነቱ አንስቶ ሲመኛት የነበረችው ትወና፣ ብዙ ተመልካች ከነበረው እና በአነጋጋሪው "ምን ልታዘዝ" የቴሌቪዥን ድራማ ጋር አገናኘችው። በዚህ ሲትኮም ላይ ጥቂት ክፍል ላይ እንዲሳተፍ ቢጠራም የትወና ብቃቱ በደራሲው እና ዳይሬክተሩ ስለተወደደለት የተሰጠውን ገጽ ባህሪ ይዞ እስከ መጨረሻው እንዲቀጥል አስችሎታል።

ኮሜዲያን ምናለ በዚህ ሒደት የትወና ጉዞውን ሲያሳልጥ በኮሜዲው ሙያ ከፊት ከሚጠሩት እሱም ከሚያደንቃቸው ከደረጄ ኃይሌ እና ከአስረስ በቀለ ጋር መገናኘት ቻለ። ይህ አጋጣሚ ዛሬ ላይ የታወቀበት ኮሜዲያንነት ወደፊት ብቅ ያለበት እንደነበር ይናገራል።

"ከእነሱ ጋር ቁጭ ብዬ ሳወራ እና ሲመክሩኝ አቅም እንዳለኝ፣ ኮሜዲ መሥራት እንደምችል ሲነግሩኝ ይህን ሙያ አጥብቄ መያዝ እንዳለብኝ እና ብዙ መሥራት እንዳለብኝ ተገነዘብሁ" በማለት ከአንጋፋ ኮሜዲያን ጋር መገናኘቱ የፈጠረበትን ስሜት ያስታውሳል።

በዚህ ወቅት አንድ ጥያቄ ውስጡ ተቀመጠ፤ እውን "በኮሜዲ ጉዳይ አቅም አለኝ ወይ?" የሚል። ይህን ማረጋገጥ አለብኝ አለ። ከአንድ ሰዓት በላይ የሚፈጅ ለስታንዳፕ ኮሚዲ የሚሆን ስክሪፕት ጻፈ።

ይህን ጊዜ ነው ከኮሜዲያን እሸቱ ጋር ሊገናኝ የቻለው። "ስታንዳፕ ኮሜዲን ላይ በደንብ አድርጎ ለመቆም፣ የሙሉ ጊዜ ሥራ ለመሥራት እሸቱ በጣም አስፈልጎኝ ነበር በሰዓቱ። እኔ የኮሜዲውን ስክሪፕት ጽፌ ነው የሄድኩት። ፕሮዲውስ የሚያደርግልኝ ሰው እፈልግ ነበር፤ ብዙ ነገር ረድቶኛል ማለት ይቻላል" ሲል የሙያ ጉዞውን ገልጿል።

ከኮሜዲያን እሸቱ ጋር መገናኘቱ "ስታንዳፕ ኮሜዲ እንዴት ይቀርባል የሚለውን፣ ሰው ፊት እንዴት ይወራል፣ ታዳሚን እንዴት መያዝ ይቻላል የሚለውን ነገር በሙሉ ብዙ ልምዶቹን አካፍሎኛል" ሲል ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።

ወደዚህ ሙያ ጠቅልሎ ከገባ በኋላ አንድ ሰዓት እና ከዚያ በላይ ርዝማኔ ያላቸውን አምስት የመድረክ ሥራዎችን አቅርቧል።

ከእነዚህ ሥራዎቹ ውስጥ "አያገባኝም" የተሰኘው ስታንዳፕ ኮሜዲ ተቀርጾ በራሱ የዩቲዩብ ቻናል የተጫነ ሲሆን፣ ከ400,000 በላይ ዕይታን አግኝቷል። በዚሁ ሙያ ቀጥሎ "ሳቅ ሜዳ"፣ "ሳቅ ሴንትራል" በተሰኙ የኮሜዲ ምሽቶች፣ በብሔራዊ ቴያትር በተዘጋጁ ሁነቶች ላይ በርከት ያሉ የኮሜዲ ሥራዎችን አቅርቧል።

"መተቸት ያለበት ይተቻል፣ መሽሟጠጥ ያለበት ይሽሟጠጣል"

ኮሜዲያን ምናለ ከኮሜዲ ጋር እጅ እና ጓንት ከሆነ በኋላ የራሱን የዩቲዩብ ቻናል ከፍቶ "ዘና ዜና" የተሰኘውን የኮሜዲ ሾው ጀመረ። ይህን ሾው ከጀመረ ስድስት ዓመታት አስቆጥሯል። በእርግጥ በመሃል "አንዳንድ ማቋረጦች ነበሩ" ይላል።

"በአንዳንድ ቴክኒክ፣ ፕሮዳክሽን ጉዳዮች፣ ካሜራ፣ ስቱዲዮ ማጣት መሰናክል ሆነውብኝ በመሃል ማቆም እና መምጣት ነበረው" በማለት ያስረዳል።

ዛሬ ላይ ብዙ ተመልካች ያገኘበት "ዘና ዜና" የኮሜዲ ሾው የመጀመሪያዎቹን ሦስት ዓመታት ከሌሎች የዩቲዩብ ቻናሎች ጋር ነበር ሲሠራ የነበረው።

"ከዚያ ግን በራሴ መቆም አለብኝ የሚለውን ወስኜ የራሴን 'ምናለ ያረጋል ቡቹ ኮሚክስ' የሚል ዩቲዩብ ቻናል ከፍቼ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ወደ ሕዝብ ማድረስ ጀምሪያለሁ" በማለት ሾውን የጀመረበትን ሒደት ያስታውሳል።

ይህ የኮሜዲ ሾው "ሳታየር" የተሰኘውን ዘውግ የሚከተል መሆንኑ የሚናገረው ምናለ "ሃሳቤን ለመግለጽ በጣም ምቾት የሰጠኝ የኮሜዲ ዓይነት ነው። በሥልጣን ደረጃ የሚደረጉ ክፍተቶችን፣ አጓጉል አሠራሮችን፣ የማይጠቅሙ ፖሊሲዎችን፣ ሕዝብ ላይ ተጽእኖ የሚፈጥሩ ሃሳቦችን፣ የግለሰብ ጉዳዮች፣ ጎልተው የወጡ ሃሳቦችን እያነሳ ይተቻል፣ ሳቅ ይፈጥራል" ሲል ተናግሯል።

"መተቸት ያለበት ይተቻል፣መሽሟጠጥ ያለበት ይሽሟጠጣል፣ መፌዝ ባለበት ጉዳይ ላይ ይፌዛል" ሲል ስለ ሥራዎቹ ይዘት ያስረዳል።

ሳቅ ከመፍጠር ባለፈ ግን "አእምሮ ላይ መልዕክት ማስቀመጥ" የኮሜዲ ሥራዎቹ ዋና ዓላማ መሆኑንም ገልጿል።

"አገሬ ውስጥ ያለው ነገር ሁሌም ቢሆን ያሳስበኛል"

"ማኅበራዊ ጉዳዮችን ማንሳት የአንድ ኪነጥበብ ውስጥ ያለ ሰው ኃላፊነት ነው ብዬ አምናለሁ የሚለው ምናለ፣ በሥራዎቹ ያሳስቡኛል የሚላቸውን ጉዳዮች እንደሚያነሳ፣ በሳቅ የተዋዛ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ተናግሯል።

ኮሜዲያን ምናለ "እንደ ዜጋም ሆነ እንደ አንድ ኪነጥበብ ውስጥ እንዳለ ሰው ፖለቲካው ውስጥ ባሉ ሰዎች የሕዝብ መናቅ በጣም ያሳስበኛል፤ የሕዝብ አለመከበር፣ የሕዝቡ ፍትሕ ማጣት፣ ባመናቸው ሰዎች መካዱ በጣም ያሳስበኛል፤ ማንነት ተኮር ጥቃቶች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ መቆሚያ ያጡ ጦርነቶች እነዚህ ሁሉ የሚደረጉ ነገሮች ሁሉ በጣም ያሳስበኛል" በማለት ስሜቱን አጋርቷል።

የኮሜዲ ሙያ እነዚህን አሳሳቢ ያላቸውን ጉዳዮች "የሚተነፍስበት" መድረኩ እንደሆነ ይገልጻል።

"እንደ አንድ ግለሰብ [ለሚያሳስቡኝ ጉዳዮች] መፍትሔ ብሰጠው ደስ ይለኛል። ብችል እነዚህን ነገሮች ማቆም መከልከል ብችል ደስ ይለኛል። ያንን ነገር ለማድረግ ግን አቅሙ የለኝም። አቅሜ ምንድን ነው? በጉዳዩ ላይ ማውራት ወይ ማፌዝ ነው። እንደ ሳታየር ኮሜዲ ፊት ላይ ሳቅ መፍጠር አእምሮ ላይ ደግሞ መልዕክት ማስቀመጥ ነው ሃሳቤ። ሳቅ እፈጥራለሁ ግን በዚያ ውስጥ ሕዝቡ ያለበትን ነገር የሚሰማ ጆሮ ካለ እንዲሰማ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ። እነዚን ነገሮች የምትነፍስበት ሙያው ኮሜዲ ነው" በማለት ተናግሯል።

"ሥራዎቼ ችግር ሊያመጡብኝ እንደሚችሉ ይገባኛል"

ኮሜዲያን ምናለ በአሁን ወቅት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ያለው "ዘና ዜና" የተሰኘውን የኮሜዲ ሾው ነው። ከስታንዳፕ የኮሜዲ ሥራዎች ራቅ ያለውም በዚሁ ምክንያት ነው።

በእነዚህ ሥራዎቹ ታዲያ የሚያደንቁት፤ የሚያበረታቱት እንደመኖራቸው ምንም እንኳን ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም "እንደማስፈራሪያ የሚመስል አስተያየት የሚልኩ ሰዎች አሉ" ሲል ይገልጻል።

"እስካሁን ስድስት ዓመት ስሠራ በራሴ የሶሻል ሚዲያ አድራሻ ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ናቸው እንደ ማስፈራራት የሚያደርጉት። ግን እነሱም ያጎረሳቸውን እጅ ላለመንከስ ስለሆነ እረዳቸዋለሁ" በማለት ያጋጠመውን ያስታውሳል።

በቅርቡም መታሰሩን የሚገልጽ ሐሰተኛ ዜና መሠራጨቱን በማስታወስ፣ "ከዚህ በኋላ የሚፈጠረውን ባለውቅም እስካሁን በጣም ሰላም ነኝ፤ ምንም የተለየ ነገር ገጥሞኝ አያውቅም" በማለት አብራርቷል።

ለተመልካች በሚያቀርባቸው የኮሜዲ ሥራዎች ሳቢያ "የሆኑ ነገሮች ሊመጡ እንደሚችሉ እረዳለሁ ወደፊት የሆኑ ችግር ሊያመጡብኝ እንደሚችሉ ይገባኛል" ሲል ስጋቱን አጋርቷል።

ኮሜዲያን ምናለ ሲቀጥል "ለምሳሌ አሁንም ቢሆን ብዙ ስፖንሰሮችን በማሸማቀቅ ብዙ ነገሮች ሲደረጉ አውቃለሁ። ከኋላም ብዙ ሥራዎች እንደሚሠሩ አውቃለሁ፤ ጠፍቶኝ አይደለም" ሲል የሚሠራቸውን የኮሜዲ ሥራዎች ተከትሎ ያጋጠመውን ሁኔታ ተናግሯል።

"ዘና ዜና" ዕድሜ ልኬን መሥራት የምፈልገው ሾው ነው የሚለው ምናለ፣ "የሆኑ ሰዎች ሲፈቅዱልኝ የምጀምረው፣ ሲከልክሉኝ የምትወው ሾው ነው ብዬ አይደለም የጀመርኩት። ለማወራው ነገር ሁሌም ቢሆን ኃላፊነት እወስዳለሁ" ብሏል።

ሆኖም "ሃሳቤ የማይጥመው ካለ፣ አልፈልግህም የሚል ሰው ካለ ምንም ማረግ አልችልም፤ የፈለገውን እርምጃ መውሰድ ይችላል። እነዚህ ነገሮች ሃሳቤን እንዳልገልጽ አያደርጉኝም። በእነሱ ጫና ውስጥ የምሆን ሰው አይደለሁም. . ." ሲል አቋሙን አስረድቷል።

አዲስ የስታዳንፕ ኮሜዲ ሥራ ለአድናቂዎቹ ይዞ የመምጣት ዕቅድ እንዳለውም ገልጿል።