በኢትዮጵያ ከፍተኛ ውጤት የሚመዘገብባቸው አዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚለያቸው ምንድን ነው?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 6 ደቂቃ

በአገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ በሚሰጡ የ12ኛ ክፍል ፈተናዎች፣ በአዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ሲያስመዘግቡ ይስተዋላል።

የአዳሪ ትምህርት ቤቶች ከመደበኞቹ ትምህርት ቤቶች አንጻር የተሻል የትምህርት አሰጣጥ እና ክትትል ይደረግባቸዋል። ተማሪዎች ወደ እነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚገቡት ከ9ኛ ክፍል ጀምሮ ሲሆን፤ የመግቢያ መስፈርቱም 8ኛ ክፍል ከፍተኛ ውጤት ማምጣት እና ተጨማሪ የመግቢያ ፈተና ማለፍ ነው።

ተማሪዎቹ ብቻ ሳይሆኑ አስማሪዎቹም የተመረጡ ናቸው። ምንም እንኳ ከመደበኞቹ ትምህርት ቤቶች ጋር ተመሳሳይ ሥርዓተ ትምህርት ቢከተሉም የመማሪያ አካባቢያቸው፣ የመምህራን ክትትል ፣ የጥናት ስርዓታቸው እና የሚያገኙት የትምህርት ግብዓት ልዩነት አለው።

በኦሮሚያ ክልል አምቦ ከተማ በሚገኘው አምቦ ኢፋ ቦሩ ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቷን የተከታተለችው ማህደር ጥሩነህ ትምህርት ቤቱ ምቹ አካባቢ እንደፈጠረላት እና ለትምህርት ብቻ ትኩረት እንድትሰጥ እንዳስቻላት ትናገራለች።

"ለሴት ልጅ ደግሞ በጣም አሪፍ ነው። ቤት ውስጥ ብሆን ወጥ ልሥራ፣ እንጀራ ልጋግር ማለቴ አይቀርም። እዚያ ግን ሙሉ ሰዓቴን፣ ሙሉ ትኩረቴን ለትምህርት ብቻ አደርጋለሁ" ትላለች።

ማህደር በ2018 ዓ.ም. የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ወስዳ ከ600ው 539 ውጤት አስመዝግባለች።

ከአምቦ ወጣ ብሎ በምትገኘው ጉደር ከተማ ተወልዳ ያደገች መሆኗን የምትናገረው ማህደር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷ ባደገችበት ከተማ ውስጥ ልከታተል ብትል ከቤቷ እስከ ትምህርት ቤቱ የአንድ ሰዓት እግር ጉዞ መንገድ እንደሚጠበቅባት ትገልጻለች።

አዳሪ ትምህርት ቤት መግባቷ ግን ከዚህ ድካም ገላግሎኛል ትላለች። በተጨማሪም ከቤተሰቧ ርቃ መኖሯ ውሳኔዎችን በራሷ መወሰንን እንዳስተማራት ታምናለች።

በትምህርት ቤቷ የሚዘጋጅ የትምህርት እና የጥናት መርሃ ግብር ቢኖርም፣ ተማሪዎቹ የራሳቸውን የጥናት ሰዓት እንደሚያወጡ የምትገልጸው ማህደር፣ ቦታው ተማሪዎች ከጓደኞቻቸው ጋር በቡድን እንዲሠሩ የሚያበረታታ እንደሆነ ትናገራለች።

በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኘው የክቡር ዶክተር ሃዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪው አብርሃም ጎጃም የተመረጡ ተማሪዎች መሰባሰባቸው ውጤታማ እንዳደረገው ይናገራል።

አብርሃም በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተናም 569 ነጥብ አስመዝግቧል።

አብርሃም በአዳሪ እና በመደበኛ ትምህርት ቤቶች መካከል ያለውን ልዩነት ሲያስረዳ አዳሪ ትምህርት ቤት የተሻለ የትምህርት ጥራት እና ለመማር ምቹ የሆነ አካባቢ አለው ይላል።

የተማሪ እና የመምህር ብዛት ተመጣጣኝ መሆን ተማሪዎች የተሻለ ድጋፍ እንዲያገኙ ማስቻሉን ያስረዳል። አብርሃም በአንድ የመማሪያ ክፍል ውስጥ ከ30 እስከ 40 ተማሪዎች እንደሚማሩ ሲገልጽ፣ በመደበኛ ትምህርት ቤቶች ግን ከ70 በላይ ተማሪዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጿል።

አዳሪ ትምህርት ቤት ውጤታማ ያደርጋል?

ማህደር የአዳሪ ትምህርት ቤት ልምዷ ውጤታማ እንዳደረጋት ታስባለች። በአዳሪ ትምህርት ቤት ባትማር ኖሮ ይህንን ውጤት ታስመዘግብ ነበር ወይ? ለሚለው ጥያቄ በእርግጠኝነት መመለስ እንደሚከብዳት ትናገራለች።

አብርሃምም እንደዚሁ በአዳሪ ትምህርት ቤት ባይማር ኖሮ ያስመዘገበውን 569 ነጥብ ያመጣ እንደነበር እንደማያስብ ይናገራል። ከአዳሪ ትምህርት ቤት በፊት ጠንካራ የንባብ ልምድ እንዳልነበረውም ገልጿል።

"አሁን አዳሪ ትምህርት ቤት ላይ በጣም የሚያበረታታ ሁኔታ ውስጥ ነው የምንኖረው" ይላል።

የክቡር ዶክተር ሃዲስ ዓለማየሁ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ደረጀ ከፈለኝ እንደሚገልጹት፣ ትምህርት ቤቱ በ2012 ዓ.ም. በ60 ተማሪዎችና በ12 መምህራን ተጀምሯል።

በማኅበረሰብ ተሳትፎ የተጀመረው ትምህርት ቤቱ ከ2015 ዓ.ም. ተማሪዎቹን በአገር አቀፍ ፈተና ማስፈተን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አንድም ተማሪ ዝቅተኛ ውጤት አምጥቶ አያውቅም።

አቶ ደረጀ እንደሚሉት፣ ተማሪዎቹ ከ9ኛ ክፍል ጀምረው በቡድን እንዲሠሩ ይደረጋል። አምስት አምስት ተማሪዎች በቡድን ይዋቀራሉ፤ ቡድኖቹም በተማሪዎቹ የመማር ፍጥነትና የመያዝ አቅም መሠረት እንደሚቀያየሩ ይገልጻሉ።

በትምህርት ቤቱ ተጨማሪ የሥነ-ልቦና፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥልጠናዎች እንዲሁም የግዕዝ ትምህርት እንደሚሰጥም አቶ ደረጀ አብራርተዋል። ወደፊት ተማሪዎቹ ቻይንኛና አረብኛ ጨምሮ ሌሎች ቋንቋዎችን እንዲማሩ ለማመቻቸት እንደታሰበም ተናግረዋል።

አቶ ደረጀ እንደሚሉት፣ በትምህርት ቤቱ የዕለት ውሎ በተለያዩ ተግባራት ይከፋፈላል። ከጠዋት ጀምሮ እስከ መኝታ ባለው ጊዜ ውስጥ ተማሪዎች ረጅሙን ሰዓት ትምህርት ጋር ተያያዥ የሆኑ ነገሮችን ሲከውኑ ይውላሉ።

መምህራንም በክፍል ውስጥ የሚሰጡ ትምህርቶችን እና የቡድን ጥናቶችን ይከታተላሉ፤ ማታ ደግሞ የሥነ ልቦና ባለሞያዎች እና የክፍል ተቆጣጣሪዎች ክትትል ያደርጋሉ።

ተማሪዎች ከማኅበረሰብና ከቤተሰብ እንዳይነጠሉም ወላጆች መጥተው እንዲጎበኟቸው እንደሚደረግ እና ተማሪዎቹ በወር ውስጥ ሁለት ወይም ሶስት ጊዜ ለጥየቃ መውጣት እንደሚፈቀድላቸው አስረድተዋል።

አቶ ደረጀ ትምህርት ቤቱ አንድ አይነት አላማ ያላቸውን ልጆች በማሰባሰቡ ውጤታማ ሆኖ መቆየቱን ይናገራሉ።

የኦሮሚያ ልማት ማህበር (ኦልማ) ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አቶ አበበ ገብሬም ፣ ትምህርት ቤታቸው የዓመቱን የውጤት ግብ ከመምህራን፣ ከድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች እና ከተማሪዎች ጋር በመወያየት ማውጣቱ ውጤታማ እንዲሆን እንዳስቻለው ያስረዳሉ።

ይህንንም ዕቅድ በቡድን ሥራና በተከታታይ ድጋፍ እንደሚያስፈጽም ጨምረው ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቱ በዘንድሮው ዓመት የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ማጠናቀቂያ ፈተና 591.6 በማምጣት በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛውን ውጤት ተመዝግቦበታል።

አቶ አበበ በአዳሪ እና በመደበኛ ትምህርት ቤቶች መካከል ሰፊ ልዩነት እንዳለ ያስረዳሉ። "እዚህ ተማሪዎች ጥሩ መኝታ እና ምግብ ያገኛሉ። በመደበኛ ትምህርት ቤት ግን ስንቱ በልቶ ይማራል? ስንቱስ ባዶ ሆዱን ይማራል? ልዩነቱ በጣም ሰፊ ነው" ይላሉ።

"ከማኅበረሰብ የተነጠለ ለማኅበረሰብ ቦታ ሊሰጥ አይችልም"

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር በላይ ሐጎስ፣ ተማሪዎች ከአዳሪ ትምህርት ቤት በፊትም በራሳቸው ብቃት የተሻሉ ስለሆኑ ውጤታቸውን ከትምህርት ቤቶቹ ጋር ብቻ መያያዝ የለበትም ይላሉ።

ጎበዝ ተማሪዎችን ብቻ መርጦ ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት ማስገባት ተመራጭ የትምህርት አሰጣጥ ሞዴል አይደለም የሚሉት ዶክተር በላይ፣ ከአዳሪ ትምህርት ቤት ይልቅ ብቃታቸው የታወቀ ተማሪዎች ከእኩዮቻቸው ሳይለዩ በተመሳሳይ ትምህርት ቤት ተጨማሪ "የእውቀት ማበልጸጊያ" ፕሮግራም ሊያገኙ ይችላሉ ይላሉ።

ይህ ሞዴል በእስራኤል እንደሚተገበር ዶክተር በላይ ይገልጻሉ። ሁሉም ተማሪዎቹ በትምህርት አቅማቸው መሠረት ተጨማሪ የተሻለ ትምህርት ሲያገኙ፣ ከእኩዮቻቸው ግን አይለዩም። አንዳንድ ጊዜም ለሚወስዱት የተለየ ትምህርት ተጨማሪ ጊዜ ወይም የተለየ ይዘት ያለው ትምህርት እንደሚሰጣቸው ያብራራሉ።

"ይህ አካሄድ ከፍተኛ ችሎታ ያላቸውን ተማሪዎች ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተማሪዎችንም ተጠቃሚ ያደርጋል" ይላሉ።

ተማሪዎችን ከማኅበረሰባቸው መነጠል እና ብቃት ያላቸውን ብቻ በአንድ ቦታ ማሰባሰብ ማኅበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ክፍተቶችን ሊፈጥር እንደሚችል ይጠቁማሉ።

ዶ/ር በላይ ተማሪዎች ከማኅበረሰባቸው ተነጥለው ካደጉ ማኅበረሰቡን ላያውቁት ይችላሉ፤ ትኩረታቸውም በሙሉ ብቁ የሆኑት ብቻ አስፈላጊ እንደሆኑ አድርጎ ማሰብ ላይ ይሆናል ባይ ናቸው።

ዶ/ር በላይ እንደሚሉት፣ ተማሪዎች ልዩ ችሎታ ያላቸው እኩዮቻቸው ጋር ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ችሎታ ካላቸው ተማሪዎች ጋር አብረው መደጋገፍ እና ማኅበረሰባዊ አውዳቸውን መረዳት ይገባቸዋል።

"[ይህችን አገር] ለወደፊቱ ብዙ እርምጃ የሚወስዳት ሰው ማን ነው ካልን ኅብረተሰቡን የሚያውቅ፣ አብሮ ያደገ፣ ከችግሩ ተካፋይ የሆነ፣ ለችግሩ መፍትሄ ሊሰጥ የሚችል፣ አብሮ ተቀላቅሎ የኖረ ዜጋ ነው እንጂ የተነጠለ ዜጋ አስተሳሰቡ በጣም በጣም ሊቀየር ይችላል" ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

"የሚያዩት፣ የሚያወሩት ስለ ጎበዞች ብቻ ነው፤ ችግር የሚመስላቸው ያው እርስ በእርስ በሚደረገው ፉክክር ላይ የተመሰረተ ነው " ይላሉ።

"ከማኅበረሰብ የተነጠለ ለማኅበረሰብ ቦታ ሊሰጥ አይችልም። በኋላ ሳይንቲስትም ቢሆን ለማኅበረሰቡ ዋጋ የማይሰጥ ሊሆን ይችላል፤ ያ ነው አደጋው" ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

የተመረጡ መምህራን፣ ጥሩ ቤተ ሙከራ፣ የተሻለ የመማሪያ አካባቢና ቤተ መጻሕፍት ማግኘት እንዲችሉ በአጠቃላይ ትምህርት ላይ የተሻለ ዕቅድ እንዲደረግ ይጠቁማሉ።

ዶ/ር በላይ እንደሚሉት፣ ብቃት ያላቸውን ጥቂት ተማሪዎች ማፍራት ጠቃሚ ቢሆንም እነሱ ብቻ አገር የሚገነቡ አይደሉም። በተለይም ለኢትዮጵያ ማኅበረሰባዊ አውድ፣ ተማሪዎች ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው እያደጉ ችግሮቹን እየተረዱና መፍትሄ ለመስጠት የሚያስቡ ዜጎች እንዲሆኑ እንደሚያግዝ ይገልጻሉ።

ተማሪ ማህደር እንደምታስረዳው ከቤተሰብ መለየት በመጀመሪያ ሊከብድ ቢችልም፣ እየተላመዱ ሲሄዱ በትምህርት ቤቱ አዲስ የቤተሰብ ዓይነት ግንኙነት እንደሚመሠርቱ ትናገራለች።

አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ መማር ከማኅበረሰብ ይነጥላል የሚለውን ሃሳብ አትቀበልም። በአራት ዓመታት የአዳሪ ትምህርት ቤት ቆይታዋ ከማኅበረሰብ እንዳልተለየች ትናገራለች። ይልቁንም ስለ ማኅበረሰቧ ለማሰብ፣ ምን እንደጎደለ ለማየት እና ወደፊት ለአገሯ ምን ማድረግ እንዳለባት እንድታስብ እንደረዳት ትገልጻለች።

ተማሪ አብርሃምም በማህደር ሀሳብ ይስማማል። በአዳሪ ትምህርት ቤት ቆይታው ይበልጥ የማኅበራዊ ግንኙነቱን እንዳሰፋለት ይገልፃል።

በአውሮጳውያኑ 2024 የታተመ ጥናት፣ በአዲስ አበባ በተጠኑ አዳሪና ልዩ የቀን ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው የትምህርት ይዘት ከመደበኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአብዛኛው የተለየ እንዳልሆነ ያሳያል።

በጥናቱ የአዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የጊዜ አጠቃቀምና ራስን የመቆጣጠር ችሎታቸው እንደተሻሻለ ተናግረዋል። ነገር ግን በተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ፉክክር፣ ጥብቅ ሥርዓትና ከቤተሰብ መራቅ በአንዳንድ ተማሪዎች ላይ የሥነ ልቦና ጫና ሊፈጥር እንደሚችልም ያሳያል።

በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ተማሪዎች ከፍተኛ ውጤት ማምጣታቸን አስመልክቶም የእነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚታየው ውጤት ከትምህርት ቤቱ ድጋፍ ጋር ተያይዞ ቢሆንም፣ የተማሪዎቹ ቀድሞ የነበራቸው ብቃትም ትልቅ ሚና አለው ሲል ጥናቱ ያስቀምጣል።

"ተሰጥኦ ላላቸው ተማሪዎች የተሻለ ዕድል መስጠት"

የትምህርት ሚኒስቴር የተመረጡ ብቃት ያላቸው ተማሪዎችን ችሎታ ይበልጥ ለማዳበር አዳሪ ትምህርት ቤቶችን እንደ አማራጭ እያስፋፋ መሆኑን ይገልጻል።

በሚኒስቴሩ አጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ የትምህርት ፕሮግራሞችና ጥራት ማሻሻያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዮሐንስ ወጋሶ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ሞዴሉ በአገሪቱ ደረጃ በጣም ጎበዝ የተባሉ ተማሪዎችን በመምረጥ ከፍተኛ ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ወደፊት በተለያዩ ዘርፎች መሪዎች የሚሆኑ ዜጎችን ለማፍራት ያለመ ነው።

ዶ/ር ዮሐንስ አዳሪ ትምህርት ቤት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች የተሻለ ዕድል ሳያገኙ እንዳይቀሩ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ያስረዳሉ።

ሚኒስቴሩ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በሁሉም ክልሎች አንድ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዲኖሩ እየሠራ መሆኑንም ይገልጻል። ባለፈው ዓመት አምስት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ተጀምረው ከ800 በላይ ተማሪዎች 9ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቁ እና በዚህ ዓመት አራት ተጨማሪ ትምህርት ቤቶች በመጨመራቸው አጠቃላይ ዘጠኝ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ኃላፊው ይናገራሉ።

ሆኖም ሚኒስቴሩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በሙሉ የትምህርት ሥርዓቱን እንዲተኩ አይፈልግም። ዶ/ር ዮሐንስ እንደሚሉት፣ በአገሪቱ ያሉ በርካታ ትምህርት ቤቶችን ወደ ተሻለ ደረጃ ማምጣት ዋናው ግብ ነው።

በኢትዮጵያ 56,000 የሚጠጉ ትምህርት ቤቶችና 27 ሚሊዮን ተማሪዎች እንዳሉ በመጥቀስ፣ ጥቂት ሺህ ተማሪዎችን ብቻ በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ማስተማር በአጠቃላይ ሥርዓቱን እንደማይተካ ይገልጻሉ።

ሚኒስቴሩ የ50 ሞዴል ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶችን እየሰራ መሆኑን በመግለፅ በዙሪያቸው ያሉ ሌሎች ት/ቤቶች ወደ ተመሳሳይ ደረጃ እንዲደርሱ የሞዴሊንግና የስኬሊንግ ሥራ እየሠራ እንደሆነ ዶክተር ዮሐንስ ይናገራሉ።

ሚኒስቴሩ በበኩሉ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ጥቂት ተማሪዎችን በማበልጸግ ብቻ ሳይወሰኑ፣ ከዚህ ጋር በተጓዳኝ የመደበኛ ትምህርት ቤቶችንም ደረጃ ማሻሻል እንደሚፈልግ ይገልጻል።