ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፈረንሳይ ሁከትን ተከትሎ በተለያዩ ከተሞች የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ
የፈረንሳይ ባለሥልጣናት፣ ቅዳሜ እና እሑድ በመላ አገሪቱ የተቀሰቀሰውን ሁከት እና ዘረፋ ተከትሎ በማዕከላዊ ፓሪስ የተወሰኑ አካባቢዎች እንዲሁም በሌሎች ከተሞች የሰዓት እላፊ ገደብ ጣሉ።
የፓሪስ ፖሊስ፣ ተቃዋሚዎች ቅዳሜ እና እሑድ ተሰባስበውበት በነበረው ፕላስ ደ ላ ሬፑብሊክ እና በሌይ አል የገበያ አካባቢ ከሌሊት 6፡00 እስከ ጠዋቱ 1፡00 ድረስ የሰዓት እላፊ ገደብ እንደሚኖር ገልጿል።
በከተማዋ መሃል በሚገኙ ሌሎች በርካታ አካባቢዎችም ያልተፈቀዱ ስብሰባዎች እንዳይካሄዱ እገዳ ተጥሏል።
ማርሴይ፣ ቦርዶ፣ ኒስ እና ሊዮንን ጨምሮ በደቡብ ፈረንሳይ በሚገኙ ከተሞች፣ እንዲሁም በሰሜኖቹ ሊልና ሌሎች ከተሞች የወጣቶችን እንቅስቃሴና መሰባሰብ በተለያየ መጠን የሚገድቡ ከፊል የሰዓት እላፊ ገደቦች መጣላቸውም ተገልጿል።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሎራን ኑኔዝ፣ ፖሊስ አንዳንድ ከተሞችን "መቆጣጠር እንዳልቻለ" አምነዋል።
ሚኒስትሩ የተቀሰቀሰውን ሁከት ለመከላከል ከነበረው ዝግጅት ጋር በተያያዘ በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ከፍተኛ ትችት ቢደርስባቸውም፣ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሥራ መልቀቂያቸውን ውድቅ አድርገዋል።
ሁከትና ዘረፋ የተቀላቀለባቸው ተቃውሞዎች የተጀመሩት ባለፈው ወር ተማሪዎች የተሻለ የትምህርት ቤት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን መነሻ በማድረግ ነበር።
ከዚያ ወዲህ ግን ተቃውሞው በርካታ ሌሎች ጉዳዮችንም ማካተት ጀምሯል። ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በተካሄዱት ሰልፎችም የሠራተኛ ማኅበራትና የተለያዩ የተቃውሞ ቡድኖች በመቀላቀላቸው የተሳታፊዎች ቁጥር ጨምሯል።
ባለሥልጣናት እንዳሉት ከ2,500 በላይ ሰዎች ታስረዋል። ኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደዘገበው፣ ፖሊስ ሰልፈኞችን ለመበተን በተጠቀመው ፈንጅ አንድ የሰልፉ ተሳታፊ እጁን አጥቷል። ወደ 1,000 የሚጠጉ የፖሊስ አባላትም ቆስለዋል።
የተፈጠረውን ቀውስ በተመለከተ ሰኞ ዕለት ከተካሄደ ስብሰባ በኋላ፣ ከንቲባዎች "አስፈላጊ በሆነባቸው ቦታዎች" የሰዓት እላፊ ገደብ እንዲጥሉ ሥልጣን እንደተሰጣቸው የፈረንሳዩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ሆኖም ገደቡ በየትኞቹ ከተሞች እንደሚተገበር አልገለፁም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሴባስቲያን ለኮርኑ በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊታወጅ እንደሚችልም ገልፀው፣ መንግሥት በሁከቱ የተጎዱ አካባቢዎች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንዲመለሱ ለመደገፍ ገንዘብ እንደሚመድብ ተናግረዋል። ወጪውም ጥቃቱ ጀርባ ካሉ አካላት እንደሚሸፈን ገልፀዋል።
"ንብረት ያወደሙ ሰዎች የጉዳቱን ወጪ እንዲከፍሉ የሚያስችሉ መንገዶችን የሚፈጥር ሕግ ይወጣል" ሲሉ ለኮርኑ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በሁከቱና በዘረፋው ምክንያት ከሥራ ውጭ ለሆኑ ሰዎች የሚውል ከፊል የሥራ አጥ ድጋፍ ፈንድ እንደሚቋቋም አስታውቀዋል።
ቅዳሜና እሑድ ወደ 550 ሺህ የሚጠጉ ሰልፈኞች የነዳጅ ዋጋ መናርን፣ የኑሮ ውድነትን እና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ እየተዳከሙ ያሉ የሕዝብ አገልግሎቶችን በመቃወም ለሰልፍ ወደ ጎዳና ወጥተዋል።
ጥቁር ልብስ የለበሱና ፊታቸውን በጭምብል የሸፈኑ አንዳንድ በሁከት የተሳተፉ ቡድኖች፣ በፓሪስ፣ ማርሴይ እና በሌሎች ከተሞች መኪኖችንና ሕንፃዎችን ሲያቃጥሉ እንዲሁም የንግድ ተቋማትን ሲዘርፉ ታይተዋል።
በማዕከላዊዋ የፈረንሳይ ከተማ ሊሞዥ፣ ቅዳሜ ዕለት ሁከት ፈጣሪዎች ባስነሱት እሳት በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተገነባውና ባማሩ ጌጣጌጦች የተዋበው የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት በእሳት ወድሟል። እሳቱ እየተስፋፋ ሄዶ የሕንፃው የሰዓት ማማና ጣሪያ ፈርሰው እንዲወድቁ አድርጓል።