ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞ የቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዶሮ ስቅይት ለመፈጸም በማሴር ወንጀል ተከሰሱ
የዩናይትድ ስቴትስ አቃቤ ሕጎች የቬንዙዌላ የቀድሞ መሪ ኒኮላስ ማዱሮ እና ባለቤታቸው ሲሊያ ፍሎሬስን ስቅይት ለመፈጸም በማሴር ወንጀል ከሰሱ።
በባልና ሚስቱ ላይ የተከፈቱት አዳዲስ ክሶች ሐሙስ ዕለት ይፋ የተደረጉ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ከተከሰሱባቸው የዕፅ ዝውውር እና የጦር መሳሪያ ክሶች ተጨማሪ ናቸው ተብሏል።
ሁለቱም ተከሳሾች ክሱን አለመፈጸማቸውን በመግለጽ ተከራክረዋል።
የ63 ዓመቱ ማዱሮ እና የ69 ዓመቷ ፍሎሬስ ከባለፈው ዓመት ጥር ወር ጀምሮ በብሩክሊን በሚገኝ እስር ቤት ታስረው ይገኛሉ።
ማዱሮ እና ባለቤታቸው ወደ አሜሪካ እስር ቤት የተወሰዱት በቬንዙዌላ ዋና ከተማ ካራካስ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ላይ አሜሪካ በፈጸመችው ድንገተኛ ጥቃት ከተያዙ በኋላ ነው።
የማዱሮ ጠበቃ ባሪ ጄ ፖላክ የቀረበውን አዲሱን ክስ ውድቅ እንድርገው ጉዳዩ በፍርድ ቤት የሚቀርብበትን ቀን በጉጉት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
የፌዴራል አቃቤ ሕግ ሐሙስ ዕለት ፍሎሬስ ቀደም ሲል በተከፈተው የአደንዛዥ ዕጽ ሽብርተኝነት ክስ ውስጥ መካተታቸውን አስታውቋል።
የማዱሮ እና የፍሎሬስ ክስ በፍርድ ቤት መታየት የሚጀምረው በዚህ ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነው ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱም በብሩክሊን በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ታስረው የሚገኙ ሲሆን ፍሎሬስ ከማረሚያ ቤቱ ወጥተው በቤት ውስጥ እንዲታሰሩ ያቀረቡትን ጥያቄ ሐሙስ ዕለት ዳኛው ውድቅ አድርገውታል።
አዲሱ ክስ ማዱሮ ሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት በቬንዙዌላ ታስረው የነበሩ የአሜሪካ ዜጎችን አሰቃይተዋል የሚል ነው።
ሐሙስ ዕለት ይፋ የተደረገው አዲስ ክስ የቀድሞ ፕሬዚዳንቱ እና ባለቤታቸው በሥልጣን ላይ ለመቆየት በማሰብ "በፖለቲካ ተቃዋሚዎች ላይ የኃይል እርምጃ መፈጸም፣ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማሰር እና የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎችን ጨምሮ እስረኞችን አሰቃይተዋል" በማለት ወንጅሏቸዋል።
በክሱ መሠረት ስቅይቱ የተፈጸመው "በኤሌክትሪክ፣ መተንፈስ እንዳይችሉ አድርጎ በማፈን፣ ራቁታቸውን እንዲሆኑ በማስገደድ፣ በመድፈር፣ ለረጅም ጊዜ በመነጠል፣ በማስራብ፣ ለብቻ ቅጣት የሚፈጸምባቸው የማረሚያ ቤት ክፍሎች ውስጥ በማስቀመጥ እና የስነልቡና ስቃይ በማድረስ" መሆናቸው ተዘርዝሯል።
አቃቤ ሕግ የስነልቡና ስቃዩ የተጎጂዎችን ቤተሰቦች፣ ሕጻናትን ጨምሮ ለመግደል ማስፈራራትን እንደሚያካትት ይገልፃል።
"ይህ ሁሉ የተደረገው ማዱሮ እና ፍሎሬስ ሥልጣናቸው ተጠብቆ መቆየቱን ለማረጋገጥ ነው" ሲሉ አቃቤ ሕጎች ሐሙስ ዕለት ከፍርድ ቤቱ ውጭ ተናግረዋል።
"ይህ ድርጊት በአሜሪካ እና በአሜሪካ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ እንገልፃለን" ሲሉ አቃቤ ሕግ ድርጉቱን "የተበላሸ አስተዳደር ማሳያ" ሲሉ ጠርተውታል።
አቃቤ ሕግ ፍሎሬስን በአፋኝ ስርዓቱ ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበራቸው በሚል የከሰሳቸው ሲሆን ግለሰቦች እንዲሰቃዩ ማድረጋቸውን እና የተወሰኑ እስረኞችን ስቅይትን በሚመለከት ወቅታዊ መረጃዎችን እንዲደርሳቸው ማዘዛቸውን ጠቅሷል።
የፍርድ ቤቱ ሰነድ እንደሚያሳየው ይህንን ያደረጉት በሕገ ወጥ ድርጊቶች ውስጥ የተሳተፉ የቤተሰባቸውን አባላት ለመከላከል በሚል ነው።
በክስ ውስጥ የተዘረዘሩት ወንጀሎች በቬንዙዌላ ከእስር የተፈቱ እስረኞች ለረጅም ጊዜ ያቀረቧቸውን ብዙ ውንጀላዎች የያዙ ናቸው።
በቬንዙዌላ የሰብዓዊ መብት ቡድን ኃላፊ የሆኑት ኻቪየር ታራዞና ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ ለቢቢሲ ሙንዶ እንደተናገሩት እርሳቸው እና ወንድማቸው ያለምንም ወንጀል ከተያዙ በኋላ ለ46 ቀናት በጠባብ ክፍል ውስጥ ታስረዋል።
ሌላኛው የቀድሞ ታሳሪ አንጄል ጎዶይ ለቢቢሲ ሙንዶ እንደተናገረው ለወራት ተገልሎ እንዲቆይ እና ከሚስቱ ጋር እንዳይገናኝ መደረጉን ገልጾ የት እንዳለ ቤተሰቡ እንዳያውቅ መደረጉንም ጨምሮ አስረድቷል።
ሐሙስ ዕለት በተመሰረተው አዲስ ክስ ውስጥ የተዘረዘሩት ወንጀሎች ማዱሮ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ከተፈጸሙ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ናቸው።
ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ፣ ምክትል ፕሬዝዳንታቸው ዴልሲ ሮድሪጌዝ በትራምፕ አስተዳደር ድጋፍ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ሆነው ተሹመዋል።
በመቶዎቸ የሚቆጠሩ እስረኞች ምህረት ተደርጎላቸው የተለቀቁ ቢሆንም ከ300 በላይ የሚሆኑ አሁንም በቬንዙዌላ ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ይገኛሉ።