ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው በብዛት መግባታቸውን የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናገሩ
የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው ወደ ትግራይ ክልል ዘልቀው መግባታቸውን እንደተመለከቱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአዲግራት ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒም ነዋሪዎችን ጠቅሶ የኤርትራ ወታደሮች በአዲግራት ከተማ በኩል በስተደቡብ ወደ ማዕከላዊው የትግራይ ክፍል መሰማራታቸውን ዘግቧል።
ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኤርትራ ወታደሮች በአዲግራት ከተማ በኩል ወደ ሌሎች የትግራይ አካባቢዎች በጭነት ተሽከርካሪዎች እና በእግራቸው ሲያቋርጡ የተመለከቱት ከዛሬ ረቡዕ መስከረም 27/ 2019 ዓ. ም. ማለዳ ጀምሮ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የመሰማራታቸው ዜና የተሰማው የትግራይ አስተዳደርን ተቆጣጥሮ የነበረው እና የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ይደገፋል የሚለው የህወሓት ኃይሎች ዋና ከተማዋ መቀለን ለቅቀው ከወጡ ከቀናት በኋላ ነው።
ቢቢሲ ረቡዕ እኩለ ቀን ላይ ያነጋገራቸው ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ 115 ኪሎ ሜትር እና ከኤርትራ ድንበር ደግሞ 40 ኪሎ ሜትር የምትርቀው የአዲግራት ከተማ ሁለት ዋሪዎች እንደገለጹት የኤርትራ ወታደሮች በበርካታ መኪኖች ተጭነው እንዲሁም በእግራቸው ሲያልፉ ተመልክተዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ነዋሪዎች እንደተናገሩት ረቡዕ ጠዋት ላይ የኤርትራ ወታደሮች በጭነት ተሽከርካሪዎች እና በእግር ወደ መቀለ መስመር ወዳለችው እዳጋ ሐሙስ አልፈው ሲሄዱ መመልከታቸውን አስረድተዋል።
አንደኛው ነዋሪ በአካበቢው የትግራይም ሆነ የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት አባላት ባለመኖራቸው እና ከዚህ ቀደም በነበረው ጦርነት ወቅት የኤርትራ ወታደሮች አልባሳትን እና ተሽከርካሪዎቻቸውን ስለሚያውቁ በቀላሉ ለመለየት እንደቻሉ ገልጸዋል።
"ወታደሮቹ ከመኪና በተጨማሪ በእግርም የሚጓዙ ስለነበሩ ለመለየት አያስቸግሩም፤ ነጣ ያለ እና ቅጠልያ ወደታራዊ ልብስ የለበሱ ናቸው። እንዲሁም መኪኖቻቸው ሲኖ የሚመስሉ የጭነት መኪኖች እና የኤርትራ የሰሌዳ ቁጥር ያላቸው ናቸው።"
ባለፉት ቀናት ከኤርትራ ተነስተው በዛላምበሳ በኩል ፋጺ የሚባል አካበቢ ኤርትራ ወታደሮች መግባታቸውን ሲሰሙ እንደነበር የገለጹት አንደኛው ነዋሪ፣ "ከዚያ ተነስተው ዛሬ ሌሊት እና ማለዳ ላይ በአዲግራት ከተማ በኩል ሲያልፉ" መመልከታቸውን ተናግረዋል።
ነዋሪዎች ወታደሮቹን ጭነው የገቡት የጭነት መኪኖች "በግምት ከ40 በላይ" እንደሚሆኑ እና በእግርም ሲጓዙ የነበሩት "ብዙ" መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
መስከረም 13/2019 ዓ.ም. ትግራይን ከአማራ እና ከአፋር ክልል ጋር በሚያዋስኑ ሥፍራዎች በህወሓት ኃይሎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ይፋዊ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ የኤርትራ ወታደሮች ተሳታፊ መሆናቸውን የአፋር ክልል ባለሥልጣናት ሲናገሩ ነበር።
እንዲሁም የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ዶ/ር አብርሃም በላይ ባለፈው ሳምንት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃለ ምልልስ "በዚህ ጦርነት ላይ የሻዕቢያ መንግሥት፣ የሻዕቢያ ሠራዊት ግንባር ወስዶ ከእነ ትጥቁ፣ ከእነ መሣሪያው ተሳትፏል" በማለት የሞቱ እና የተማረኩ መኖራቸውን ተናግረው ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ያሉ ታጣቂዎችን በመርዳት የአገሪቱን ሰላም ለማናጋት እየጣረ መሆኑን በመግለጽ ቢከስም፣ የኤርትራ መንግሥት ግን ክሱ በአገር ውስጥ ያለውን ችግር አቅጣጫ ለማስቀየር ነው በሚል ውድቅ ያደርጋል።
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ባልተለመደ ሁኔታ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ "የብልጽግና መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ እየተፈጠሩ ካሉት በርካታ ግጭቶች ላይ ትኩረት ለማስቀየር ጎረቤት አገራትን መወንጀል ልማዱ ሆኗል" በማለት የቀረበባቸውን ክስ አጣጥለውታል።
በቀደመው የትግራይ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ተሰልፎ ትግራይ ውስጥ የተዋጋው የኤርትራ ሠራዊት በተፈጸሙ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከሚከሰሱት ኃይሎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የአዲግራት ነዋሪ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የፌደራሉ መከለከያ ሠራዊት አጋር የሆነው የትግራይ ሰላም ኃይሎች አዛዥ የሆነው ገብረእግዚአብሔር በየነ ለኤኤፍፒ "የኤርትራ ጦር ከነዩኒፎርሙ ከባድ መሣሪያዎችን ታጥቆ ወደ ትግራይ ገብቷል" ሲል ተናግሯል።
"ይህ ኃይል በድሮን እየተመታ ነው" በማለት ኤርትራ ጦነርቱ ወደ ግዛቷ እንዳይደርስ "ውጊያው በትግራይ ውስጥ እንዲሆን ሆን ብላ እያደረገ ችነው" ሲል ከስሷል።
አንድ የአዲግራት ከተማ ባለሥልጣን ስማቸው ሳይጠቀስ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት ደግሞ የኤርትራ ወደታሮች ለቀናት በአካባቢው እንደነበሩ እና "ሕዝቡ ስጋት እንደተፈጠረበት" ገልጸዋል።
አንድ የዐይን ምስክር ደግሞ "በትላልቅ የጭነት መኪኖች፣ በክፍት መኪኖች እና በሌሎች ተሽከርካሪዎች የተጫኑ የኤርትራ ወደታሮች ከከባድ መሣሪያዎች ጋር" ከአዲግራት በስተደቡብ እያመሩ መሆናቸውን አረጋግጧል።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ ወደ ይፋዊ ጦርነት የሚያመራ ከሆነ ከ25 ዓመታት በፊት በሁለቱ አገራት መካከል ከተካሄደው ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት የከፋ እንደሚሆን በርካቶች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
አገራት፣ ቀጣናዊ እና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት አገራቱ ሉዓላዊነትን እንዲያከብሩ እና ከግጭት ተቆጥበው አለመግባባቶችን በንግግር እንዲፈቱ እየጠየቁ ነው።