ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ድርቁ፣ ረሃቡ፣ መፈናቀሉ ሳይበቃ ወደ ሌላ ዙር ጦርነት እየገባን ይመስላል"- የኤርትራ ወታደሮች ትግራይ መግባት ያሰጋቸው ነዋሪዎች
ኢትዮጵያ በኤርትራ "ወረራ እንደተፈጸመባት" አስታውቃ፣ የአሥመራ ወታደሮች አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ አሳስባለች።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአዲግራት እና እዳጋ ሐሙስ ነዋሪዎችም የኤርትራ ወታደሮችን እንደተመለከቱ እና ስጋት እንደገባቸው ገልጸዋል።
የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ነዋሪዎችን ጠቅሶ የኤርትራ ወታደሮች በአዲግራት ከተማ በኩል በስተደቡብ ወደ ማዕከላዊው የትግራይ ክፍል መሰማራታቸውን ዘግቧል።
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር የሆኑትን እናታለም መለሰ የኤርትራ ወራደሮች ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን ለብሉምበርግ ተናግረዋል።
"ሁሉም የውጭ አገር ወታደራዊ ኃይሎች የኢትዮጵያን ግዛት ለቅቀው መውጣት አለባቸው" ማለታቸውንም ዘገባው ይጠቁማል።
ህወሓትን ጨምሮ ጥምረት የፈጠሩ የፖለቲካ እና ወታዳራዊ ቡድኖች በኤርትራ ይደገፋሉ ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ሲከስስ ቆይቷል።
ኤርትራ ይሄንን ስታስተባብል ብትቆይም፤ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዐይን እማኞች ግን የአሥመራ ወታደሮች "በብዛት ወደ ትግራይ መግባታቸውን" ገልጸዋል።
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል የዐይን እማኞችን ምስክርነት "ኢትዮጵያ በጎረቤቷ ላይ ጦርነት ለመክፈት የምታደርገው ጥረት አካል ነው" ሲሉ ማጣጣላቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የእዳጋ ሐሙስ ነዋሪ፤ ባለፉት ቀናት የኤርትራ ወታደሮች በዛላምበሳ በኩል ፋጺ የተባለው አካባቢ መግባታቸውን ሲሰሙ እንደነበር ገልጸዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአዲግራት ነዋሪዎችም የኤርትራ ወታደሮች ድንበር አልፈው መግባታቸውን ተናግረዋል።
ነዋሪዎች ረቡዕ መስከረም 27/2019 ዓ. ም. ማለዳ ላይ የኤርትራ ወታደሮች ከፋጺ ተነስተው በአዲግራት ሲያልፉ መመልከታቸውን ገልጸዋል።
የእዳጋ ሐሙስ ነዋሪ "ትናንት [መስከረም 26] ውቅሮ ከተማ አራት የኤርትራ ታርጋ ያላቸው ፒክአፕ ተሽከርካሪዎች እየበረሩ አልፈው ሲመለሱ" መታየቱን ተናግረዋል።
መስከረም 27ም "አምስት መኪኖች በፍጥነት አልፈው ተመለሱ" ያሉት ነዋሪው "የት ደርሰው ነው የሚመለሱት? ብለን ስንጠይቅ ነጋሽ የሚባል ከተማ ደርሰው ነው የተመለሱት አሉን" ብለዋል።
መስከረም 27 ጠዋት ላይ "ብዙ መኪኖች" ማየታቸውን አክለዋል።
"ከዚህ በፊት እናውቃቸዋለን። ምን ያደርጉ ይሆን? በሚል ስንፈራ ነው የቆየነው። በተለይ ሴቶች ከዚህ ቀደም የደረሰባቸውን ስለሚያውቁ ሲፈሩ ነበር" ብለዋል።
ነዋሪው "ከ30 እስከ 45 ወታደር የጫኑ መኪኖችን ቆጥሬያለሁ" ሲሉም ተናግረዋል።
ስማቸው እንዳጥቀስ የጠየቁ አንድ የአዲግራት ነዋሪ ደግሞ "መኪኖቹ ከ40 በላይ ናቸው። በግምት በአንድ መኪና ከ50 እስከ 100 ወታደሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ በእግር ያለፉትም ብዙ ናቸው" ብለዋል።
የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የመሰማራታቸው ዜና የተሰማው የትግራይ አስተዳደርን ተቆጣጥሮ የነበረው እና የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ይደገፋል የሚለው የህወሓት ኃይሎች ዋና ከተማዋ መቀለን ለቅቀው ከወጡ ከቀናት በኋላ ነው።
"ድርቁ፣ ረሃቡ፣ መፈናቀሉ ሳይበቃ ወደ ሌላ ዙር ጦርነት እየገባን ይመስላል"
ከትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ 115 ኪሎ ሜትር እና ከኤርትራ ድንበር ደግሞ 40 ኪሎ ሜትር የምትርቀው የአዲግራት ከተማ ሁለት ዋሪዎች እንደገለጹት የኤርትራ ወታደሮች በበርካታ መኪኖች ተጭነው እንዲሁም በእግራቸው ሲያልፉ ተመልክተዋል።
መስከረም 13/2019 ዓ. ም. ትግራይን ከአማራ እና ከአፋር ክልል ጋር በሚያዋስኑ ሥፍራዎች በህወሓት ኃይሎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ይፋዊ ጦርነት ከተነሳ በኋላ የኤርትራ ወታደሮች ተሳታፊ መሆናቸውን የአፋር ክልል ባለሥልጣናት ሲናገሩ ነበር።
የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ዶ/ር አብርሃም በላይ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ቃለ ምልልስ "በዚህ ጦርነት ላይ የሻዕቢያ መንግሥት፣ የሻዕቢያ ሠራዊት ግንባር ወስዶ ከእነ ትጥቁ፣ ከእነ መሣሪያው ተሳትፏል" በማለት የሞቱ እና የተማረኩ መኖራቸውን ተናግረው ነበር።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የእዳጋ ሐሙስ ነዋሪ የኤርትራ ወታደሮች "እንደዚህ በብዛት ይገባሉ ብለን አልጠበቅንም ነበር" ሲሉ የተፈጠረባቸውን ፍርሃት ገልጸዋል።
"ሜካናይዝድም አላቸው፤ መድፍ፣ ታንክ፣ ዙ-23፣ ሞርታርም አይቻለሁ።... ሸራ የለበሱ መሣሪያዎች እና ምን እንደሆኑ የማናውቃቸው [መሣሪያዎች] በመኪና ተጭነው ሲያልፉ ነበር" በማለትም አክለዋል።
ቢቢሲ ይሄንን በገለልተኛ ወገን አላረጋገጠም።
መስከረም 27 ረፋድ ላይ "የተወሰኑት [የኤርትራ ወታደሮች] ከአዲግራት ወደ መቀለ አቅጣጫ፣ እዳጋ ሐሙስ ከተማ ከገቡ በኋላ ወደ ምሥራቅ እና ወደ ምዕራብ እየተከፋፈሉ ሄደዋል" ሲሉ ነዋሪው ገልጸዋል።
ወታደሮቹ "ወደ ደቡብ ከሄዱ ወደ መቀለ መስመር ነው። ወደ ፍረወይኒ-ሰንቃጣ ወይም ወደ ምዕራብ ከተገነጠሉ ወደ ሐውዜን ነው። ቀጥ ብለው ከሄዱ ወደ ውቅሮ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
የኤርትራ ወታደሮች ከአዲግራት ወደ እዳጋ ሐሙስ ሲጓዙ በድሮን መመታታቸውን ቢሰሙም "እርግጠኛ አለመሆናቸውን" ጠቅሰዋል።
የትጥቅ ግጭቶችን የሚሰንደው አክሌድ፤ የኤርትራ ወታደሮች በዛላምበሳ በኩል የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው መግባታቸውን ጠቅሶ በአዲግራት- እዳጋ ሐሙስ መስመር እየተጓዙ ሳለ ጉአዳ በተባለ አካባቢ በኢትዮጵያ መንግሥት የድሮን ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ገልጿል።
ኤርትራ "ትብብር ለኅልውና" የተባለውን አዲሱን የአማጺዎች ጥምረት ትደግፋለች ተብሎ የሚጠረጠው በሁለት ምክንያቶች እንደሆነም አክሌድ ጠቁሟል።
ኤርትራ ከ2013 እስከ 2015 ዓ. ም. የዘለቀውን የትግራይ ጦርነት ባስቆመው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ደስተኛ አለመሆኗ የመጀመሪያው ምክንያት ነው።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ወደብ ለማግኘት የያዘችውን አቋም ኤርትራ በመቃወሟ በሁለቱ አገራት መካከል መሀል ገብ መሬት ለማበጀት ትግራይ ክልልን የግጭት ቀጠና ማድረግ መሻቷ ሁለተኛው ምክንያት ነው ሲልም ያትታል።
በቀደመው የትግራይ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ተሰልፎ ትግራይ ውስጥ የተዋጋው የኤርትራ ሠራዊት በተፈጸሙ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከሚከሰሱት ኃይሎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የእዳጋ ሐሙስ ነዋሪ "የኤርትራ ወታደሮች እዚህ እዳጋ ሐሙስ የጫኑትን ከመኪና እያወረዱ ከገበሬዎች በግድ አህያ እየወሰዱ ወደተለያየ አቅጣጫ መሄድ ጀምረዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
ያጓጓዙት "የራሳቸውን እቃ ነው እንጂ እየዘረፉ አይወስዱም" ብለዋል።
ኋላ ላይ ግን አንዳንድ ቤቶችን መፈተሽ እና መንገደኞችን መመለስ እንደጀመሩ ገልጸዋል።
"መግደል አላየሁም፤ ግን የፈለጉትን ማድረግ ጀምረዋል። በጣም ነው የፈራነው። ሕዝቡ ተሸብሯል" ብለዋል።
የኤርትራ ወታደሮችን መለያ ልብስ ስለሚያውቁ የወታደሮቹን ማንነት መለየት መቻላቸውን የእዳጋ ሐሙስ እና የአዲግራትም ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የእዳጋ ሐሙስ ነዋሪው "ተጋሩ ዓለምን ምን እንዳደረግነው አናውቅም፤ ችላ ብሎናል፤ እኛም ኢትዮጵያውያን ነን፤ ድርቁ፣ ረሃቡ፣ መፈናቀሉ ሳይበቃ ወደ ሌላ ዙር ጦርነት እየገባን ይመስላል" ሲሉም ተናግረዋል።
"መንግሥት እየተበቀለን ከሆነ ያሳዝናል፤ ኢትዮጵያውያን ነን። ትግራይ የኢትዮጵያ ናት፤ መንግሥት ዝም ብሎ ሊያይ አይገባም" በማለትም ለቢቢሲ ገልጸዋል።
"ትልቁም፣ ትንሹም ሰው እነሱን ሲያይ በጣም አዝኗል"
የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት አጋር የሆነው የትግራይ ሰላም ኃይሎች አዛዥ የሆነው ገብረእግዚአብሔር በየነ ለኤኤፍፒ "የኤርትራ ጦር ከነዩኒፎርሙ ከባድ መሣሪያዎችን ታጥቆ ወደ ትግራይ ገብቷል" ብሏል።
"ይህ ኃይል በድሮን እየተመታ ነው" በማለት ኤርትራ ጦርነቱ ወደ ግዛቷ እንዳይደርስ "ውጊያው በትግራይ ውስጥ እንዲሆን ሆን ብላ እያደረገች ነው" ሲልም ከስሷል።
አንድ የአዲግራት ከተማ ባለሥልጣን ስማቸው ሳይጠቀስ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት፤ የኤርትራ ወደታሮች ለቀናት በአካባቢው እንደነበሩ እና "ሕዝቡ ስጋት እንደተፈጠረበት" ገልጸዋል።
የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ የአሜሪካ ኤምባሲ ዜጎቹ ወደ አማራ፣ አፋር እና ትግራይ ክልሎች እንዳይጓዙ መክሯል።
ኤምባሲው መስከረም 27 ባወጣው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ የወታደራዊ ተቋማት ላይ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል መረጃ እንዳለውም ጠቁሟል።
እንደ አዲስ ባገረሸው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን አቋርጠዋል።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ ወደ ይፋዊ ጦርነት የሚያመራ ከሆነ ከ25 ዓመታት በፊት በሁለቱ አገራት መካከል ከተካሄደው ደም አፋሳሽ የድንበር ጦርነት የከፋ እንደሚሆን በርካቶች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአዲግራት ነዋሪ፤ የኤርትራ ሠራዊት የጫኑ "ከ40 በላይ የሚሆኑ መኪኖች እዳጋ ሐሙስ መግባታቸው" የፈጠረባቸውን ስጋት ገልጸዋል።
ነዋሪው በአካበቢው የትግራይም ሆነ የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት አባላት እንደሌሉ ገልጸዋል።
"[የኤርትራ ወታደሮች] በመኪና ብቻ ሳይሆን በእግራቸውም ሲገቡ አይቻቸዋለሁ" ብለዋል።
የኤርትራ ወታደሮች መለያ ልብስ "ቅጠልያ እና ነጭ" በመሆኑ እና የተሽከርካሪዎቹ ታርጋ "ኤሪ" የሚል ስለሆነ ማንነታቸውን መለየት እንደቻሉ ተናግረዋል።
"መኪናዎቹ ገልባጭ ያልሆኑ ሲኖ ነው የሚመስሉት። ግን የራሳቸው የመከላከያ ታርጋ አላቸው" ብለዋል።
ከኤርትራ ወደ አዲግራት ያለው መስመር ከዛላምበሳ- ፋጺ- ቀርሰበር የሚወስድ ነው።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪ እንገለጹት፤ የኤርትራ ወታደሮች "ከፋጺ ወደ ቀርሰበር የመጀመሪያ ምሽግ ሠርተው እንደገቡ" ሰምተዋል።
እዚያ አካባቢ ቆይተው መስከረም 26 ለመስከረም 27 ሌሊት እና መስከረም 27 ጠዋት ወደ እዳጋ ሐሙስ አቅጣጫ መሄዳቸውን ተናግረዋል።
"እነሱን [የኤርትራ ወታደሮችን] ሳይ የንዴት፣ የቁጭት ስሜት ነው የተሰማኝ። እነሱ ተመልሰው ከተማችንን፣ ክልላችንን፣ አገራችንን ለጥፋት ሲገቡ በማየቴ ቁጭት ሰተምቶኛል" ብለዋል።
"እኔ ብቻ ሳልሆን የአካባቢው ትልቁም ትንሹም ሰው እነሱን ሲያይ በጣም አዝኗል። ከዚህ በፊት የነበረውን ስሜት ስለሚያውቀው ንዴትም አለው" ሲሉም አክለዋል።
የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በብዛት መግባታቸውን ተከትሎ ስጋት የተፈጠረው በትግራይ ክልል ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጦርነቱ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምን የበለጠ ሊያናጋው ይችላል በሚል እያስጠነቀቁ ነው።
የኤርትራ ወታደሮች ወደ ትግራይ መግባታቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ከዘገቡ በኋላ ኢትዮጵያ ክስተቱን ስታረጋግጥ ኤርትራ ደግሞ ክሱን አስተባብላለች። አስካሁን በሁለቱ አገራት መንግሥታት በኩል ስላለው ሁኔታ እና በቀጣይ ምን ሊከሰት እንደሚችል የሰጡት ፍንጭ የለም።