ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩኬ የኤርትራ ዲፕሎማቶችን እንቅስቃሴ እንደምትገድብ እና ኤርትራውያንን መቀበል እንደምታቆም አስጠነቀቀች
ዩናይትድ ኪንግደም ስደተኞች ወደ አገራቸው ከሚመለሱበት ፖሊሲ ጋር በተያያዘ ኤርትራውያን ወደ አገሪቷ እንዳይገቡ እገዳ ለመጣል ዛተች።
የዩኬ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሻባና ማሕሙድ፣ የኤርትራ መንግሥት በትናንሽ ጀልባዎች የገቡ እና ወንጀል የፈፀሙ ስደተኞችን ካልተቀበለ ኤርትራውያን ወደ አገሪቷ እንዳይገቡ እንደሚከለክሉ አስታውቀዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ከሐሙስ ጀምሮ የኤርትራ ዲፕሎማቶች ከለንደን ውጪ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ገደብ እንደሚጣልባቸው ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ለቪአይፒ ሰዎች የሚደረገው ፈጣን የቪዛ አገልግሎትም ይቆማል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ሚኒስትሮች የቪዛ ክልከላ እንደሚጥሉ በማስፈራራት ሌሎች አገራትም ተመላሽ ስደተኞችን እንዲቀበሉጫና ሲያሳድሩ ነበር።
በርካታ ስደተኞች በአነስተኛ ጀልባዎች ወደ ዩኬ የሚገቡ ሲሆን እስከ ሰኔ ባሉት 12 ወራት ውስጥ ወደ አገሪቱ ከገቡ ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ የኤርትራ ዜጎች ናቸው። በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገሪቷ ከሚገቡት ስደተኞች ውስጥም 18 በመቶ የሚሆኑትን ይይዛሉ።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ በለንደን የሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲን ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።
"ኤርትራ ወንጀለኞችን እና በዩኬ ለመቆየት ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸውን ዜጎችን ለመቀበል ሁሉም እድል ነበራት፤ ነገር ግን እንደሌሎች አገራት ፈቃደኛ አልሆነችም" ብለዋል የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ።
በመሆኑም ለመተባበር ፈቃደኛ ባልሆኑ ሌሎች አገራትም ላይ ተጨማሪ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንደማያመነቱ አክለዋል።
የዩኬ መንግሥት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የኤርትራ ባለሥልጣናት ስደተኞችን ለመመለስ ለመተባበር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከስሷል።
አሁን ላይ ዩኬ እጥለዋለሁ ያለችው ክልከላም የኤርትራ ዲፕሎማቶች ያለፈቃድ ከለንደን ከ60 ኪሎሜትር ርቀት በላይ እንዳይንቀሳቀሱ ያግዳል። ይህ በኤርትራ መዲና አስመራ ያሉ የብሪታኒያ ባለሥልጣናት ላይ የተጣለው ክልከላ ነጸብራቅ እንደሆነም የአገር ውስጥ ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ዩኬ በአንጎላ፣ ናሚቢያ እና ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ላይ ተመሳሳይ እገዳ እንደምትጥል አስታውቃ ነበር።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ላይ ክልከላ ተጥሎ የነበረ ሲሆን ስደተኞችን ለመቀበል የምታሳየው ትብብር በመሻሻሉ እገዳው መነሳቱን የአገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮው አስታውሷል።
አንጎላ እና ናሚቢያም ክልከላው ከመጣሉ በፊት ተመላሽ ስደተኞችን ለመቀበል ተስማምተዋል።
በዩኬ የጥገኝነት ጥያቄ ሥርዓት ላይ ለውጥ መደረጉ ሲገለጽ፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ፣ ሕገ ወጥ ስደተኞችን ለመመለስ ለማይተባበሩ አገራት የቪዛ ክልከላ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጸው ነበር።
እንደ የአገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮ መረጃ ከሆነ ከአውሮፓውያኑ 2026 መጀመሪያ ወዲህ ከ20 ሺህ 400 በላይ ስደተኞች በአነስተኛ ጀልባዎች ወደ ዩኬ ገብተዋል።
ይህ ቁጥር ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 40 በመቶ ቀንሷል።
ከሐምሌ 2025 እስከ ሰኔ 2026 ድረስ ባሉት ወራትም ወደየአገራቸው የተባረሩ እና የተመለሱ ስደተኞች ቁጥር ከ40 ሺህ 600 በላይ ነበሩ። ይህም በቀደመው ዓመት ከነበረው በ8 በመቶ ጨምሯል።
ከተመላሾቹ መካከል ከ6 ሺህ የሚያንሱት በወንጀል ድርጊት ጥፋተኛ የተባሉ ናቸው።