ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
'በሕይወት እንተርፋለን አላልንም' ፡ በህወሓት ቁጥጥር ስር የቆዩት የቀድሞ ባለሥልጣናት ምን ገጠማቸው?
የቀድሞ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደን ጨምሮ፣ አራት የቀድሞ ባለሥልጣናት ከኤርትራ ድንበር አቅራቢያ በህወሓት ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ከነበሩበት እስር ቤት አምልጠው በኢትዮጵያ ሠራዊት እጅ ከገቡ በኋላ ወደ መቀለ መመለሳቸውን ተናገሩ።
ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት ከመጀመሩ በፊት በቀድሞ ጓዶቻቸው ከየቤታቸው ታግተው የተወሰዱት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ፣ ኮሎኔል ተወልደ ገብረትንሳኤ፣ ኮሎኔል ዓለምሰገድ ገብረእግዚአብሔር እና አቶ ኢሳይያስ ታደሰ ላለፉት ሳምንታት የነበሩበት ሳይታወቅ ቆይቶ ነው ነጻ መውጣታቸው የተገለጸው።
ቢቢሲ ትግርኛ ከታሳሪዎቹ አንዱ ከሆኑት ኮሎኔል ተወልደ ገብረትንሳኤ እና ከሌሎቹ የቅርብ ሰዎች እንዳረጋገጠው የቀድሞ ባለሥልጣናቱ ከህወሓት ታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር አምልጠው ወደ መቀለ ተመልሰዋል።
በህወሓት አመራሮች ውሳኔ ተይዘው መቀለ በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ቁጥጥር እየተደረገባቸው የቆዩት ባለሥልጣናት ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ በኃይል ከሆቴል እንዲወጡ ተደርገው ከዋና ከተማዋ መቀሌ ውጪ ወደ ተለያዩ ቦታዎች መወሰዳቸውን ኮሎኔል ተወልደ ገብረትንሳኤ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከአራቱ ታሳሪዎች አንዱ የሆኑት የቀድሞው የትግራይ ኃይሎች ወታደራዊ መረጃ ኃላፊ ኮሎኔል ተወልደ ገብረትንሳኤ ለቢቢሲ ትግርኛ በሰጡት ቃለ ምልልስ መከላከያ ሠራዊት እና አጋሩ የትግራይ ሰላም ኃይል ወደ ከተማዋ ከመግባታቸው ቀደም ብሎ ምሽት 5፡00 ከሆቴል ክፍላቸው አስወጥተው እንደወሰዷቸው ተናግረዋል።
መቀለ ሆቴል ውስጥ በቆዩባቸው ቀናት ከጠባቂዎቻቸው በስተቀር ቤተሰብን ጨምሮ ከማንም ጋር እንዲገናኙ እንዳልተፈቀደላቸው የሚናገሩት ኮሎኔሉ፣ ከሆቴል ከወጡ በኋላ ሌሊቱን ሲጓዙ አድረው መጀመርያ ወደ አክሱም ቀጥሎ ወደ ዓድዋ መወሰዳቸውን ገልጸዋል።
ከመቀለ ከወጡ በኋላ አራቱን የቀድሞ ባለሥልጣናት እንደለያይዋቸው እና ኮሎኔል ተወልደ እና ኮሎኔል ገብረእግዚአብሔር ዓድዋ እንዲሁ ሌ/ጄነራል ታደሰ እና አቶ ኢሳያስ በአክሱም ተለያይተው በጥበቃ ስር እንዲቆዩ ተደርገዋል።
በእገታቸው ወቅት ከማንም ጋር እንዲገናኙ ካለመፈቀዱ ውጪ "ምንም ዓይነት እንግልት፣ ድብደባ እና ስድብ እንዳልደረሰባቸው" ፤ነገር ግን በዓድዋ ቆይታቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ገጥሟቸው እንደነበር ኮሎኔል ተወልደ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በአራት ቀኑ ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ነበር ምግብ የሰጡኝ። ከአራት ቀናት በኋላ እንጀራ በሽሮ ላኩልኝ። ነገር ግን ለአራት ቀናት ምግብ አልነበረም። ሆን ተብሎ የተደረገ ይመስለኛል።" ብለዋል።
የህወሓት ባለሥልጣናት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የገቡት ውዝግብ እየተካረረ ሲሄድ ሌ/ጄነራል ታደሰን ጨምሮ አራቱን ባለሥልጣናት ከቤታቸው እና ከያሉበት በቁጥጥር ሥር ማዋላቸው "ለደኅንነታቸው" ሲሉ የወሰዱት እርምጃ እንደነሆነ ገልጸው ነበር።
ኮሎኔል ተወልደ ግን "ለደኅንነታቸው ሲባል በጠመንጃ ጥበቃ ስር፣ ቤተሰብ እና ሌላ ሰው ማግኘት በማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ለደኅንነት የሚባል ነገር የለም" በማለት በቁጥጥር ስር እንዲሆኑ መደረጋቸውን እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
"ምክንያቱ ፖለቲካዊ ነው። የሀሳብ ልዩነት ነበረን፤ 'ነባሩ መንግሥትን እንመልሳለን' ሲሉ፣ እኛ የለም አይሆንም፣ የፕሪቶሪያ ስምምነትን የሚያፈርስ ነው አልን። የፕሪቶሪያ ስምምነት መጣስ እንደሌለበት እና መንግሥት ይመለስ የሚባል ነገር አንቀበልም ብለን ተናግረናል።" ሲሉም አብራርተዋል።
የቀድሞ ባለሥልጣናቱ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ የተፈለጉበት ጉዳይ እና የእስራቸው ምክንያት ምን እንደሆነ እና እርምጃው በማን ትዕዛዝ እንደተፈጸመ ማወቅ ሳይችሉ ቆይተዋል።
"የትግራይ ፖሊስ እኔን አይመለከተኝም አለ፣ ፍርድ ቤትም እሱ የያዘው ጉዳይ እንዳልሆነ ነበር የሚገልጸው። ማን እንዳሰረን እንኳን ማወቅ አልቻልንም፤ ማን እኛን ለማሰር እንደወሰነ፤ ከላይ ማን እንደሚያዝዝ አናውቅም" ብለዋል ኮሎኔል ተወልደ።
ኮሎኔል ተወልደ እና አጋሮቻቸው የህወሓት መሪዎች የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት መፍረስ እና ሥልጣንን መልሶ መቆጣጠር "ወደ ጦርነት ይመራናል፤ ሕዝቡ ሌላ ጦርነት የመሸከም አቅም የለውም። ሰላም ነው የሚፈልገው" በማለት በመናገራቸው ከህወሓት መሪዎች ጋር ልዩነት መፈጠሩን አመልክተዋል።
አራቱ የቀድሞ የክልል ባለሥልጣናት ከመቀለ ወጥተው ወደ ሌላ የትግራይ አካባቢ በተወሰዱበት ጊዜ እንዲለቀቁ ለማድረግ በተለያዩ ወገኖች አማካይነት ንግግሮች እና ጥረቶች የነበሩ ቢሆንም ውጤት አላመጡም።
ኮሎኔል ተወልደም "ሰዎቹ እኮ [የህወሓት መሪዎች] ንግግር የሚገባቸው አይደሉም፤ የውጭ ኃይሎች፣ ዲፕሎማሲ፣ ሰላማዊ ንግግር፣ ድርድር የሚባል ቋንቋ የሚገባቸው አይደለም። ይህንን የሚረዱ ሰዎች አይደሉም" በማለት ጥረቶቹ ውድቅ የሆኑበትን ምክንያትም ተናግረዋል።
አራቱ የቀድሞ ባለሥልጣናት ከእገታ የወጡት በህወሓት ታጣቂዎች ከኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ወደ ምትገኘው ራማ ከደረሱ በኋላ ነው። ኮሎኔል ተወልደ እንደሚሉት ራማ ውስጥ ለአምስት ቀናት ቆይተዋል።
"መጀመርያ ለየብቻ ወደ ሆቴል ወሰዱን፤ ከዚያም ወደ መኖሪያ ቤት። የማን እንደሆነ መናገር በማልፈልገው በአንድ ግለሰብ መኖርያ ቤት ውስጥ ነበር ያቆዩን። በራማ ከዓድዋ የተሻለ አያያዝ ተደርጎልናል።"
"ነገር ግን ወደ ራማ ስንወሰድ ወደ የት ሊወስዱን እንደሚችሉ እናውቃለን፤ ቀስ በቀስ ወደ ድንበር እያስጠጉን እንደሆነ እናውቃለን፤ ወደ ኤርትራ በድብቅ ሊያዛውሩን እየሞከሩ እንደሆነም ተረድተናል። ድንበር አቋርጠው ሊያሻግሩን ወስነው ነበር። እኛም ይህንን ተረድተናል።"
በዚህም የተነሳ እንደማይለቋቸው እና የሚደረግባቸው ጥበቃ ጥብቅ እንዲሆን መታዘዙን መረዳታቸውን የሚገልጹት ኮሎኔል ተወልደ፣ "አጠቃላዩን ሁኔታ ካረጋገጥን በኋላ፣ ብዙ ሰዎች የተሳተፉበት፣ ብዙ ሥራ እና ጥረት" በማድረግ ከእስሩ ማምለጣቸውን ተናግረዋል።
ቢቢሲ አራቱ የቀድሞ ባለሥልጣናት እንዴት ከእስር እንደወጡ የተለያዩ መረጃዎች መውጣታቸውን በመጥቀስ በዝርዝር እንዲያስረዱ ለኮሎኔሉ ላቀረባለቸው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
"በፈቃዳቸው አልለቀቁንም፤ በራሳችን መንገድ ነው የወጣነው፤ እኔ ብቻዬን ስለእሱ ማውራት ስለማልችል ዝርዝሩን አሁን ባልናገር እመረጣለሁ። ነገር ግን ያለፍላጎታቸው ነው አምልጠን የወጣነው። ዝርዝሩን ቀስ ብለን ብንነጋገርበት ይሻላል።"
ኮሎኔል ተወልደ እንደሚሉት እሳቸው እና ጓዶቻቸው የህወሓት መሪዎች ወደ ኤርትራ ሊያሻግሯቸው እንደሆነ ከተረዱ በኋላ "በፍጹም ወደ ኤርትራ መሄድ እንደሌለብን እርግጠኞች ነበርን። አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብን ወስነን የምናመልጥበትን መንገድ ፈልገን ወጥተናል" ብለዋል።
ነገር ግን በዚህ ሙከራቸው ውስጥ አደጋ ሊገጥማቸው እንደሚችል ሰግተው እንደነበረ እና "ሁላችንም በሕይወት እንተርፋለን የሚል እምነት አልነበረንም፣ ነገር ግን በማናቸውም መንገድ መውጣት እንዳለብን ወስነን ነበር" ብለዋል ኮሎኔል ተወልደ።
"ምን እያደረግን እንደሆነ ስለምናውቅ፤ ውጤቱን ከቀን ወደ ቀን እያየን ነበር፤ መውጣት እንደምንችል ገምተን ነበር። ግን በቀላሉ እንደማይሆን፣ አደጋን እንደምንጋፈጥ እና መስዋዕትነት እንደምንከፍል አስበን ነበር። በመጨረሻም አደረግነው፤ በሕይወት መውጣት ችለናል።" ብለዋል።