የዩክሬን ድሮኖች ፍጥነት የቀነሰው በአሜሪካ ክልከላ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ኤሎን መስክ ተናገረ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የተወሰኑ የዩክሬን የጦር መሣሪያዎች የሚጓዙበት ፍጥነት የቀነሰው የአሜሪካ መንግሥት በጣለው ክልከላ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ኤሎን መስክ ተናገረ።

የዩክሬን ድሮኖች እና ሌሎችም የጦር መሣሪያዎች ከስታርሊንክ ኢንተርኔት ጋር ለመተሳሰር የሚወስድባቸው ጊዜ መጓተቱንም ገልጿል።

ስታርሊንክ የኤሎን መስክ ተቋም በሆነው ስፔስኤክስ የሚቀርብ የኢንተርኔት አገልግሎት ነው።

የዩክሬን ድሮኖች በዋናነት የሚንቀሳቀሱት እና የአየር ክልሏን የምትጠብቀውም በስታርሊንክ አማካኝነት ነው።

ያለፈው ማክሰኞ ምሽት የስታርሊንክ ፍጥነት እንደቀነሰ እና ይህም የጦር ግንባር ተልዕኮዎችን እንዳስተጓጎለ ዩክሬን ይፋ አድርጋለች።

የፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አማካሪ እንዳሉት በስታርሊንክ ላይ የተጣለው ገደብ የአጋጣሚ ጉዳይ ሳይሆን ከዋሽንግተን ጋር ያለው መቃቃር ውጤት ነው።

ከሰሞኑ ኪየቭ እና ዋሽንግተን መካከል ውጥረት ተፈጥሯል።

የስታርሊንክ ወታደራዊ መሣሪያዎች ክንፍ የሆነው ስታርሺልድን የሚቆጣጠረው የአሜሪካ መንግሥት ነው።

"ፍጥነቱ ላይ የሚፈጠር ገደብ እና አጠቃቀሙ የሚወሰነው በአሜሪካ ጦር እና በፕሬዝዳንቱ ነው" ሲል መስክ ተናግሯል።

የዩክሬን ባለሥልጣናት ስታርሊንክ እንዲስተካከል ኤክስ ላይ መስክን እየጠየቁ ነው።

ዜሌንስኪ ለዩናይትድ ኪንግደም መገናኛ ብዙኃን "ስህተት ነው ብዬ አስባለሁ፤ ምናልባት ትልቅ የቴክኒክ ችግር ሊሆን ይችላል። በትክክል አናውቅም፤ እንዲከፈትልን ግን ጠይቀናል" ብለዋል።

ማክሰኞ የስታርሊንክ ፍጥነት 100 ማይል በሰዓት (160 ኪሎሜትር በሰዓት) ሆኗል። ከዚህ ፍጥነት በላይ የሚጓዙ የጦር መሣሪያዎች ከኔትወርክ ትስስር ይወጣሉ ማለት ነው።

ትናንት ረቡዕ ፍጥነቱ በተወሰነ ደረጃ መሻሻሉን የዩክሬን የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትር ማይክሀሎ ፊዶሮቭ ተናግረዋል።

መስክ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና ከሰጡ በኋላ "የስታርሺልድን የፍጥነት ገደብ ሙሉ በሙሉ ማንሳት ለዩክሬን መከላከያ ቁልፍ ነው" ብለዋል።

መስክ በበኩሉ የስታርሺልድ ሥርዓት በአሜሪካ መንግሥት ቁጥጥር ሥር እንደሆነ እና ውሳኔ ሰጪው ፕሬዝዳንቱ እንደሆኑ ገልጿል።

ስታርሊንክ "ለሲቪሎች እና ለመከላከያ እርምጃዎች እንጂ ጥቃት ለመሰንዘር አይውልም" ሲልም አክሏል።

የአሜሪካ መንግሥት እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ጥቃት ሰዎች መገደላቸው መገለጹን ተከትሎ የስታርሊንክ ትስስር መዘግየቱ ተገልጿል።

ዜሌንስኪ ማክሰኞ የተፈጸሙት ጥቃቶች "ከፍተኛ መጠን ያላቸው" መሆናቸውን ገልጸዋል።

አብዛኞቹን የሩሲያ ድሮኖች መትተው ቢጥሉም ጉዳትም እንደደረሰ ተናግረዋል።

ያለ ማስጠንቀቂያ በተተኮሱ ድሮኖች ምክንያት በመላው ዩክሬን 600,000 መብራት ጠፍቶባቸዋል።

"አጋጣሚ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። አሁን ካለው የፖለቲካ ሁኔታ ጋር የሚያያዝ ነው" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ዩክሬን በሩሲያ የኃይል አቅርቦት ላይ በምታደርሰው ጥቃት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደስተኛ አይደሉም።

በሁለቱ አገራት መካከል "የኢነርጂ ተኩስ አቁም" ተደርጓል ቢሉም ሩሲያ በዩክሬን መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ፈጽማለች።