ትራምፕ የተመድ በጀት በ15 በመቶ መቀነሱን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞቹ መሰናበታቸውን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ መንግሥታቸው ከሌሎች በርካታ አገራት ጋር በመተባበር በመንግሥታቱ ድርጅት ታሪክ እጅግ ሰፊ የሆነ ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቁ።
ትራምፕ ዛሬ በተጀመረው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር የድርጅቱ በጀት በዘንድሮው የአውሮፓውያኑ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ 15 በመቶ መቀነሱን እና ከ4000 በላይ ሰራተኞቹም እንደተሰናበቱ ተናግረዋል።
ድርጅቱ "አስደናቂ አቅም" እንዳለው የጠቀሱት ፕሬዚደንቱ፣ ነገር ግን የግራ ዘመሞችን "አጀንዳ መሸከም" ማቆም አለበት ብለዋል።
ትራምፕ በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው ትላልቅ እርምጃዎችን የወሰዱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አሜሪካን ከበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አባልነት ማስወጣት ይገኝበታል።
የፕሬዚደንቱ እርምጃ ካረፈባቸው 66 ተቋማት መካከል ግማሽ ያህሉ ከመንግሥታቱ ድርጅት ጋር የተገናኙ ናቸው።
በወቅቱ ዋይት ሃውስ በሰጠው መግለጫ እርምጃው የተወሰደው ተቋማቱ "ለአሜሪካ ጥቅም የሚሰሩ" ባለመሆናቸው እና "ውጤታማ ያልሆኑ ወይም ድብቅ አጀንዳዎችን ስለሚያራምዱ" እንደሆነ ገልጿል።




















