የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ሆን ብለው ሆስፒታሎችን ዒላማ ማድረጋቸውን የቢቢሲ ምርመራ አረጋገጠ

የሕክምና ባለሙያዎች በባትሪ የቀዶ ሕክምና እያደረጉ
የምስሉ መግለጫ, በኤል ፋሸር በሚገኘው የሳዑዲ ሆስፒታል የነበሩ የሕክምና ባለሙያዎች፣ ሆስፒታሉ በቦምብ በተመታበት ዕለት በስልክ ብርሃን ታግዘው የቀዶ ሕክምና አድርገዋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ (አርኤስኤፍ) ተዋጊዎች ባለፈው ዓመት የዳርፉር ከተማን ከተቆጣጠሩ በኋላ ስልታዊ በሆነ መንገድ የኤል-ፋሸር የጤና ስርዓትን ማውደማቸውን የቢቢሲ ምርመራ አረጋገጠ።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኃላፊ የቢቢሲን ግኝት "እጅግ የሚረብሽ" ብለውታል።

ኃላፊው ቮልከር ተርክ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የጤና ተቋማትን ጨምሮ የሲቪል መገልገያዎችን በተደጋጋሚ ማጥቃቱ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ ጥሰት እና የጦር ወንጀል ሊሆን ይችላል ብለዋል።

አርኤስኤፍ የቢቢሲ ግኝቶችን ውድቅ አድርጓል።

በኤል-ፋሸር የሚገኙ ምንጮችን በመጠቀም ቢቢሲ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከግንቦት 2024 እስከ ጥቅምት 2025 ድረስ በሆስፒታሎች እና የጤና ተቋማት ላይ 43 የተለያዩ ጥቃቶችን ለይቷል።

በዓለም አቀፍ ሕግ የጤና ተቋማትን ወይም የጤና ባለሙያዎችን በግጭት ወቅት ማጥቃት ሕገ ወጥ ነው።

ምርመራው በጤና ባለሙያዎች ላይ የደረሰውን ጥቃትም ይፋ አድርጓል። የቢቢሲ መረጃ እንደሚያሳየው ከሚያዚያ 2023 እስከ ጥቅምት 2025 ድረስ 55 የጤና ባለሙያዎች ሲገደሉ፣ 120 ቆስለዋል፣ 10 የሚሆኑት ደግሞ "ጠፍተዋል" ወይም ታግተዋል።

ኤል-ፋሸር በከበባ በነበረበት ወቅት የነበሩት የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ዶ/ር ሙሐመድ ሱሌማን "የጤና ስርዓት የአንድ ከተማ ወይም የአንድ ግዛት የጀርባ አጥንት በመሆኑ ምክንያት አርኤስኤፍ የሆስፒታሎችን አገልግሎት ለማቋረጥ እየሞከረ ነበር" ብለዋል።

ሲቪሊያን በአካባቢው እንዳይቆዩ ለማድረግ ሆን ተብሎ የጤና ተቋማትን እያጠቁ እንደነበርም ገልፀዋል።

ይህ ምርመራ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የእርስ በእርስ ጦርነቱ ከተጀመረ ከ2023 በኋላ እጅግ ከባድ ጦርነት የተደረገበት ኤል-ፋሸር በታጣቂ ቡድኑ ቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ የወጣ ነው።

የመንግሥታቱ ድርጅት መርማሪዎች በኤል-ፋሸር የተደረገው ውጊያ "የዘር ፍጅት ምልክት" እንደሆነ ተናግረዋል። የአርኤስኤፍ ኃይል የጀርባ አጥንት የሆኑት የአረብ ሚሊሻዎች አረብ ያልሆኑ የከተማ ነዋሪዎችን ዒላማ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በሚሳዔል ከተመታ በኋላ በእሳት የተቃጠለ በኤል ፋሽር በሚገኝ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኝ መጋዘን እና የኩላሊት እጥበት ማዕከል
የምስሉ መግለጫ, በኤል ፋሽር በሚገኝ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኝ መጋዘን እና የኩላሊት እጥበት ማዕከል በሚሳዔል ከተመታ በኋላ በእሳት ተቃጥሏል
Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቢቢሲ ምርመራ ለረዥም ጊዜ ከተማዋ በከበባ ውስጥ በነበረችበት ወቅት የጤና ተቋማት ላይ የተፈፀመውን ጥቃት በቅደም ተከተል ለመጀመሪያ ጊዜ ለይቷል።

በከተማዋ አንዳንድ የጤና ተቋማት ጦርነቱ እንደተጀመረ በሳምንታት ውስጥ ተዘግተዋል። ከእነዚህም ውስጥ በከተማዋ መሀል የሚገኘው ዋነኛ እና ወሳኝ የሆነው የማስተማሪያ ሆስፒታል ይገኝበታል።

ሆስፒታሉ አገልግሎቱን ወደ ደቡብ የከተማዋ አካባቢ ቀይሮ ለመቀጠል የሞከረ ሲሆን፤ አገልግሎቱ ግን በኃይል አቅርቦት መቆራረጥ እና በግብዓት እጥረት ተፈትኗል።

ከዓመት በኋላ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የከተማዋን ከበባ ሲያጠናክር ሁኔታው በፍጥነት ተቀይሯል።

እአአ ግንቦት እና ሰኔ 2024 አርኤስኤፍ ከይዞታው እየገሰገሰ ሲጠጋ ሆስፒታሉን በርካታ ጊዜ በከባድ መሣሪያ ደብድቧል።

በሚሳዔል የተመታው የሆስፒታሉ ክፍል በከተማዋ ብቸኛ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት የሚሰጠው እና በሰዎች የተጨናነቀው እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ሱሌማን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲደበደብ እንደደነገጡ ይናገራሉ።

በዚህ ቀን የጤና ባለሙያዎች ለ16 ቁስለኞች ቀዶ ሕክምና አድርገዋል።

ጥቃቶቹ አርኤስኤፍ ሰኔ 8 ሆስፒታሉ ውስጥ ሲገባ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ታካሚዎች መገደላቸውን፣ በርካታ ባለሙያዎች ማምለጣቸውን እና የሕክምና መሣሪያዎች መውደማቸውን ምንጮች ተናግረዋል።

በወቅቱ ሆስፒታሉ የተዘጋ ሲሆን ጦሩ ከወጣ በኋላ ደግሞ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እጅ ወድቋል።

በአርኤስኤፍ የተሾሙት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር አላ ኤዲን ኑጉድ፣ ሆስፒታሉ ለወታደራዊ ሰፈርነት ጥቅም ላይ እየዋለ ነበር ብለዋል።

በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሆስፒታሎች በተፋላሚ ወገን በጦርነቱ ውስጥ "ጠላት ላይ ጉዳት" ለመፈፀም ጥቅም ላይ ከዋሉ ከለላቸውን ያጣሉ።

ሚኒስትሩ ከሱዳን ጦር ዋና መስሪያ ቤት ጎን በሚገኘው ሆስፒታሉ የተተከሉ ከባድ መሣሪያዎችን እና የተቀበሩ ፈንጂዎችን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን እና ካርታዎችን አሳይተዋል።

ይሁን እንጂ ሐኪሞች ሆስፒታሉ ከጦር ሰፈሩ ጋር አንድ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ቢቢሲ የጤና ሚኒስትሩን ክስ የሚያሳይ ምንም ገለልተኛ ማስረጃ አላገኘም። የዳርፉር አስተዳደርም የቀረበውን ክስ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ አድርጓል።

ሆስፒታሉ ከተዘጋ በኋላ ባለሙያዎቹ እና የሕክምና ቁሳቁሶቹ የጦሩ ዋነኛ ሰፈር ባለበት የሳዑዲ የእናቶች ሆስፒታል ተዛውሯል። በዚህም ሆስፒታል በቀናት ውስጥ ጥቃቶች ተፈፅመዋል።

ለዚህ ምርመራ ቢቢሲ ያናገራቸው ስድስት ዶክተሮች ስልታዊ ማነጣጠር መፈፀሙን ገልፀዋል።

የሳዑዲ ሆስፒታል በቀን እስከ 25 ጊዜ እየተለየ መደብደቡን ተናግረዋል። በድንኳን የተሰራ አንድ የቀዶ ሕክምና ክፍል በ2025 አምስት ጊዜ ጥቃት እንደተፈፀመበት ዶክተሮች ተናግዋል።

አነስተኛ የጤና ተቋማትም የጥቃት ዒላማ ከመሆን አልዳኑም።

የጤና ተቋማቱ ከጥቃቶች በኋላ ቦታ ሲቀይሩም ጥቃቶቹ ቀጥለዋል። ከእነዚህም ውስጥ የሕፃናት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና የኩላሊት እጥበት ማዕከል ይገኙበታል።

እአአ ጥቅምት 2025 አርኤስኤፍ ከተማዋን ሲቆጣጠር ብቸኛ አገልግሎት የሚሰጠው ሆስፒታል የሳዑዲ ሆስፒታል ብቻ ነበር።

የጤና ባለሙያዎች ድሮኖች የታካሚዎችን እንቅስቃሴ እንደሚከታተሉም ተናግረዋል። ለአብነትም በጥቃት የቆሰሉ ሰዎችን ወደ ጊዜያዊ የሕክምና ክፍል እየወሰዱ የነበሩ ሰዎችን ሲከታተል የነበረ ድሮን ሕንፃው በር ላይ ሲደርሲ በፈፀመው ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ተገድለዋል።

የኤአርኤስኤፍ የጤና ሚኒስትር እነዚህን ጥቃቶች ውድቅ በማድረግ በጦሩ እና በአካባቢው አጋሮቹ "የቀጠሉ ውሸቶች" ናቸው ብለዋል።

ዶክተሮች የአርኤስኤፍ ኃይሎች የጤና ተቋማትን ሆን ብለው ዒላማ የሚያደርጉት ከታካሚዎች ውስጥ የጦሩ ወይም የአጋር ኃይል ወታደሮች ስለሚገኙበት እንደሆነም ተናግረዋል።

አሁን በኤል-ፋሸር የጤና ስርዓቱ በአርኤስኤፍ በተመሠረት አስተዳደር ይመራል። ሆስፒታሎችን ዳግም እየከፈተ እንደሆነ የሚናገረው ይኸው አስተዳደር ዶክተሮችን አግቶ እያሰራ መሆኑን አስተባብሏል።

ኤል-ፋሸር በአርኤስኤፍ እጅ ከወደቀች ከአንድ ዓመት በኋላም በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ጥቁር ምዕራፍ የሆነው የጥቃቱ ቁስል አልሻረም።

የጦር ግንባሮች ቦታ ተቀያይሯል፤ ግጭቱን ለማስቆም ግን ምንም ምልክትም የለም። በጤና ማዕከላት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች በጦርነቱ ሰፊ የሰብዓዊ ቀውስ አካል ሆነው ቀጥለዋል።