ስዊትዘርላንድ በኦሽዊትዝ አይሁዶችን ሲያሰቃይ ስለ ነበረው 'አስፈሪው ዶክተር' ምስጢራዊ ሰነዶችን ይፋ ልታደርግ ነው

የፎቶው ባለመብት, Ullstein Bild / Getty
የስዊስ የፌደራል ደህንነት አገልግሎት ለረዥም ጊዜ ተዘግቶ የቆየውን የናዚ ጦር ወንጀለኛው ጆሴፍ ሜንጌሌ ሰነዶች ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
ሰነዶቹ ይፋ የሚደረጉት መቼ እንደሆነ ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ሜንጌሌ ወደ አውሮፓ የተሰደደ ሲሆን ምንም እንኳን ዓለም አቀፍ የእስር ትዕዛዝ ቢወጣበትም ስዊዘርላንድ ውስጥ እንደኖረ አሉባልታዎች አሉ።
የታሪክ ተመራማሪዎች በተደጋጋሚ ሰነዶቹን ለማግኘት ቢጠይቁም እስካሁን ድረስ የስዊስ ባለሥልጣናት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ሜንጌሌ የሕክምና ዶክተር ሲሆን በጀርመን የናዚ ጦር ክንፍ ውስጥ ያገለግል ነበር። ሜንጌሌ ከናዚ ጀርመን ማጎሪያ ካምፖች አንዱና ትልቁ በሆነው እና በፖላንድ በሚገኘው "ኦሽዊትዝ" ውስጥ ተመድቦ በሚሰራበት ወቅት የትኛው እስረኛ ወደ ቤርከናው (ጋዝ ቻምበር) መላክ እንዳለበት የሚወስነው እርሱ ነበር።
በዚህ የኦሽዊትዝ ማሰቃያ ውስጥ 1.1 ሚሊዮን ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 1 ሚሊየን ያህሉ አይሁዳውያን እንደሆኑ ይታመናል።
"የሞት መልዓክ" በሚል ቅጽል ስም የሚታወቀው ይህ ዶክተር በተለይ ሕጻናት እና መንትያ እስረኞችን ወደ መሞቻቸው ከመላኩ በፊት በመምረጥ ስቃይ ለሞላበት የሕክምና ምርምር ያውላቸው ነበር።
ከጦርነቱ በኋላ ልክ እንደ ሌሎቹ ከፍተኛ የናዚ መኮንኖች ስሙን እና ዩኒፎርሙን ለወጠ።
ሐሰተኛ ማንነት ተጠቅሞ በሰሜን ጣሊያን በሚገኘው የስዊስ ቆንስላ ሐሰተኛ የቀይ መስቀል የጉዞ ሰነድ አስመትቶ ወደ ደቡብ አሜሪካ ተሰደደ።
ቀይ መስቀል በጦርነቱ ምክንያት አገር አልባ ለሆኑ አንዲሁም ለሚሰደዱ አውሮፓውያን በሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሰነዱን ይሰጥ ነበር። ነገር ግን ናዚዎች የሚጠብቃቸውን የሕግ ቅጣት ለማምለጥ ይጠቀሙበት የነበረ ሲሆን ቀይ መስቀል በኋላ ላይ በጉዳዩ ላይ ይቅርታ ጠይቋል።
በኦሽዊትዝ ካምፕ በሜንጌሌ እጅ ከፍተኛ ስቃይ የተቀበሉት አይሁዶች ብቻ ሳይሆኑ ሮማኒያውያን፣ ስላቮች፣ ኮሚኒስቶች፣ የግራ ፖለቲካ አቀንቃኞች፣ የናዚ ተቃዋሚ የሆኑ የጀርመን ዜጎች እና የጦር ምርኮኞች ነበሩ።
ሜንጌል ከጦርነቱ በኋላ ራሱንና ስሙን ደብቆ በአርጀንቲና፣ በፓራጓይ እና በኮሎምቢያ እንደኖረ ይታመናል።
በስተመጨረሻው ግን የብራዚል ትልቅ ከተማ በሆነችው ሳኦ ፓውሎ እየኖረ እአአ በ1979 በስትሮክ ተመትቶ ሕይወቱ አልፏል።
ሜንጌል በላቲን አሜሪካ ይኖር እንደነበረ የታወቀው እርሱ ከሞተ ከአስራ ሦስት ዓመታት በኋላ እአአ በ1992 ነበር።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ታዲያ የሜንጌል ከስዊትዘርላንድ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?
ምንም እንኳን ሜንጌል እአአ በ1949 ከአውሮፓ ቢሸሽም፣ በ1956 ከልጁ ሮልፍ ጋር በስዊስ አልፕስ የበረዶ ሸርተቴ ተዝናንቷል። ይህ መረጃ እአአ ከ1980ዎቹ ጀምሮ ይታወቃል።
ከዚያ በኋላ በይፋ የቀረውን ሕይወቱን በደቡብ አሜሪካ አሳልፏል።
ነገር ግን የስዊትዘርላንድ ታሪክ ጸሐፊ ሬጉላ ቦክስለር ሜንጌል በ1959 ላይ ዓለም አቀፍ የእስር ማዘዣ ከወጣበት በኋላ እንደገና ተመልሶ ወደ ስዊትዘርላንድ መሄዱን ያስብ ነበር።
ቦችስለር ስዊትዘርላንድ ከናዚዎች ለሚሸሹ ሰዎች እንደ መሸጋገሪያ አገር ልታገለግል ትችላለች በሚል ምርመራ ባደረገበት ወቅት፣ በሰኔ 1961 የኦስትሪያ የስለላ አገልግሎት ስዊትዘርላንዳን ሜንጌል በሌላ ስም እየመጣ እንደሆነ እና ምናልባትም በስዊትዘርላንድ ግዛት ውስጥ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቆ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሜንጌሌ ባለቤት በዙሪክ አፓርታማ ተከራይታ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት አመልክታ ነበር።
"ሜንጌል በ1959 ወደ አውሮፓ ለመጓዝ እቅድ እንደነበረው የሚያሳይ ማስረጃ ያለ ይመስላል" ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል። "ሜንጌል በዙሪክ አፓርታማ ለምን ተከራየች?"
አፓርትመንቱ የመካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ የሚገኝ ሲሆን የሜንጌሌ ቤተሰብም ከዚያ የበለጠ ማውጣት የሚያስችል አቅም ነበረው። ነገር ግን ለዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቅርብ ነበር።
ቦችለር በ1961 አፓርታማው በክትትል ስር እንደነበር የሚያረጋግጥ የዙሪክ የፖሊስ ፋይሎችን ማየት ችለዋል። ፖሊስ የሜንጌል ባለቤት ማንነቱ ካልታወቀ ሰው ጋር ቮልስዋገኗን እያሽከረከረች ተመልክቷል።
ግን ባሏ ነበር?

የፎቶው ባለመብት, Universal History Archive
እአአ በ1961 እንደ ሜንጌል ያለ ማዘዣ የወጣበት የጦር ወንጀለኛን ለመያዝ የስዊትዘርላንድ ፌዴራል ፖሊስን ያሳትፋል። በ2019 ቦችለር ሰነዶቹን ለማየት ወደ ስዊትዘርላንድ ፌዴራል መዛግብት አመልክተዋል።
ጥያቄያቸው ግን ውድቅ ተደርጓል። ሰነዶቹ እስከ 2071 ድረስ በብሔራዊ ደህንነት ምክንያት እና ለዘመዶቹ ቤተሰብ ጥበቃ ሲባል ታሽጎባቸዋል።
ቦችለር ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸው የመጀመርያው አልያም የመጨረሻው ሰው አልነበሩም። እአአ በ2025 የታሪክ ምሁሩ ጄራርድ ዌትስታይን እንደገና ሞክረው ነበር። እርሳቸውም ውድቅ ተደርጎባቸዋል።
"አስቂኝ መስሎ ታየኝ" ሲል ለቢቢሲ ተናግረዋል። "እስከ 2071 ድረስ ዝግ ሲደረጉ የሴራ ትንተናውን ያጠናክራል፣ ሁሉም ሰው 'የሚደብቀው ነገር ቢኖራቸው ነው' ይላል።"
ዌትስቴይን የስዊትዘርላንድን ባለሥልጣናት ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ ውሳኔውን ተቃውመዋል። ይህ ሂደት ውድ በመሆኑ የገንዘብ ድጋፍ እንዲጠይቁ አድርጓል።
"በጥቂት ቀናት ውስጥ 18,000 የስዊዝ ፍራንክ (23,000 ዶላር) አሰባስበናል።"

የፎቶው ባለመብት, Robert Nickelsberg / Getty Images
የስዊትዘርላንድ ፌዴራል የስለላ አገልግሎት በመጨረሻ ሀሳባቸውን የቀየሩት በዚህ ጊዜ ነበር። በዚህ ወር ሙሉ ግልጽነት የተወሰነ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ተቋሙ ባወጣው መግለጫ ላይ ገልጿል።
"ይግባኝ አቅራቢው እስካሁን ይፋ ያልሆኑ ሁኔታዎች እና መስፈርቶች ከግምት ውስጥ በማስገባት ዶሴዎቹን የማግኘት መብት ይሰጠዋል" ብሏል።
ሰነዶቹ ስለ ሜንጌል ብዙ የሚገልጹ መረጃዎች ስለመያዙ ማንም እርግጠኛ አይደለም።
የስዊትዘርላንድ የታሪክ ማኅበር ፕሬዝዳንት ሳቻ ዛላ "ስለ ሜንጌሌ ምንም ዓይነት ተዛማጅነት እንደሌለው ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ" ነገር ግን የውጭ የስለላ ድርጅት ወይም የውጭ መረጃ ሰጪዎችን የሚያመለክቱ መረጃዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስባለሁ።
በ1950ዎቹ መጨረሻ ላይ የእስራኤል ሞሳድ የሸሹትን የናዚ የጦር ወንጀለኞች በንቃት ይከታተል ነበር። እና ዛላ ከስዊዘርላንድስ ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው ይጠራጠራሉ። ይህም የስዊዘርላንድ ባለሥልጣናት ሰነዶቹን ይፋ እንዳይሆኑ ለማድረግ ምክንያት ይሰጣቸዋል፣ ምክንያቱም ከውጭ የስለላ ኤጀንሲዎች ጋር የተያያዙ ሚስጥራዊ መረጃዎች ብዙውን ጊዜ ይሰረዛሉ።
ነገር ግን ሞሳድ ከ70 ዓመታት በፊት ናዚዎችን ለማደን ካደረገው አሰሳ ጋር በተያያዘ መጠቀሱ በጣም አስጊ ነውን?
ዛላ ሰነዶቹ ይፋ የሆኑት በግዴለሽነት ነው ካሉ በኋላ ያም ወደ ግርታ እና ሴራ ትንተና በቀላሉ አምርቷል በማለት ይተቻሉ።
እንደ ጃኮብ ታነር ያሉ ሌሎች የታሪክ ምሁራን ደግሞ፣ በዶሴዎቹ ላይ ያለው ምስጢራዊነት ከሜንጌል ይልቅ ስለ ስዊዘርላንድ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ግልጽ ያደርጋሉ ብለዋል። "በብሔራዊ ደህንነት እና በታሪክ ግልጽነት መካከል ግጭት አለ፣ እና የመጀመሪያው ብዙውን ጊዜ ወደ ስዊዘርላንድ ይጠቁማል።"

ታነር በ1990ዎቹ የበርጊየር ኮሚሽን ላይ ስዊትዘርላንድ ከናዚ ጀርመን ጋር ያላትን ግንኙነት በተለይም የስዊትዘርላንድ ባንኮችን ሚና በመመርመር ውስጥ ተሳትፏል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአይሁድ ስደተኞች ድንበር ላይ እንዲመለሱ ሲደረጉ፣ የስዊትዘርላንድ ባንኮች በኋላ ላይ በናዚ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የሞቱትን የአይሁድ ቤተሰቦች ገንዘብ ሲያስቀምጡ የተፈጠረውን ጠንቅቆ ያውቃል። "እነዚህ ዶሴዎች አሁንም ይፋ አለመሆናቸው ለዴሞክራሲያዊ መንግሥት ችግር ነው" ሲል ታነር ይከራከራል።
ያም ሆኖ ሜንጌል እአአ በ1961 ስዊዘርላንድ ውስጥ እንደነበር እርግጠኛ ነው።
የሚፈለገው የናዚ የጦር ወንጀለኛ አዶልፍ ኢችማን በ1960 በአርጀንቲና በሞሳድ በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር። እና ወደ ደቡብ አሜሪካ የሸሹ ሌሎች ናዚዎች እነሱም አደጋ ላይ እንዳሉ እንዳሰቡ እና ጓደኞቻቸው እና ዘመዶቻቸው የሚኖሩባት አውሮፓም የበለጠ አስተማማኝ እንደምትሆንላቸው የሚያሳይ ማስረጃ አለ።
ታነር እንደጠቆመው ወደ ቺሊ የሸሸው ሌላኛው የናዚ የጦር ወንጀለኛ ዋልተር ራውፍ በ1960 በጀርመን ቆይታ አድርጓል።
በበርጊየር ኮሚሽን ውስጥ ያገለገለ አንድ የታሪክ ምሁር በ1999 የሜንጌሌን ፋይሎች በአጭሩ እንዲመለከት ከተፈቀደለት በኋላ በስዊዘርላንድ ግዛት ውስጥ መገኘቱን ማረጋገጥ ወይም ውድቅ ማድረግ የማይቻል ነው ብሎ ደምድሟል። ነገር ግን ይህ ስለ ጦርነቱ በሙሉ በ24 ጥራዝ ከቀረበው ዘገባ ውስጥ ጥቂት መስመሮች ብቻ ነበሩ። ፋይሎቹ እንደገና ዝግ ተደርገዋል። የታሪክ ምሁሩም ከሰባት ዓመታት በፊት ሞቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዶሴዎቹ ለሕዝብ ይፋ የሚሆኑበት ጊዜ ቀኑ አልተቆረጠም።
የፌዴራል የስለላ አገልግሎት ስለ "ሁኔታዎች እና መስፈርቶች" የሰጠው መግለጫ ለዌትስታይን አስፈሪ ይመስላል። "ከግልጽነት ይልቅ ድፍንፍን ያለ ሰነድ እናገኛለን ብዬ እፈራለሁ" ብለዋል።
ቦችስለር ሰነዶቹ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚሰረዙም ይሰጋሉ። "[ባለሥልጣናቱን] በፍፁም አላምንም። እንደ ኢፕስቲን ፋይሎች እንዳይመስሉ እፈራለሁ። እነዚህ የሜንጌሌ ሰነዶች ለምን ለረጅም ጊዜ ይፋ ሳይሆኑ ቀሩ?"
ሜንጌሌ ለአስርተ ዓመታት ሚስጥራዊ፣ ወሬ እና የሴራ ትንተና መነሻ ሆኖ ቆይቷል።
በፈጸመው አስከፊ ወንጀል ይቅርና ፈጽሞ አልተያዘም። በ1979 በብራዚል ሲሞት በሐሰት ስም ተቀበረ።
ነገር ግን ወሬው መሰራጨቱን ቀጥሏል። በ1985 አስከሬኑ ተቆፍሮ ወጣ፣ በመጨረሻም በ1992 የዲኤንኤ ምርመራ አስከሬኑ የእሱ መሆኑን አረጋግጧል።
በፈጸመው አስከፊ ወንጀል ፈጽሞ አልተያዘም። እአአ በ1979 በብራዚል ሲሞት በሐሰተኛ ስም ነው የተቀበረው።
ነገር ግን ወሬው መናፈሱ ቀጥሏል። በ1985 አስከሬኑ ተቆፍሮ ወጣ፣ በመጨረሻም እአአ በ1992 በዲኤንኤ ምርመራ አስከሬኑ የእሱ መሆኑን ተረጋግጧል።
የአውሽዊትዝ አስፈሪ ዶክተር ሞቷል።
ነገር ግን ስዊዘርላንድ ውስጥ ነበር? ስዊትዘርላንድስ አላስተዋሉትም ነበር?
እስሩ ሊያስከትለው የሚችለውን ያልተፈለገ ትኩረት ለማስቀረት በሚል እንዳላዩ ማለፍ መርጠዋል? ወይስ እንደ ሜንጌሌ ሁሉም ነገር ወሬ ብቻ ነው?
"ምናልባት ወደ እውነቱ ላንደርስ እንችላለን" ይላል ዌትስታይን። "እዚህ እንደነበረ ወይም እንዳልነበረ በፍፁም አናውቅም… ግን ምናልባት ቢያንስ የበለጠ ግልጽ የሆነ ሀሳብ ሊኖረን ይችላል።"














