ትራምፕ ወደ ሥልጣን በተመለሱ በመጀመሪያው ዓመት ከክሪፕቶ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አገኙ

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ዓመት በክሪፕቶከረንሲ ባደረጉት የንግድ ስምምነቶች ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማግኘታቸውን የ2025 የገንዘብ ሪፖርታቸው አመለከተ።

927 ገጽ ያለው ሪፖርቱ እንዳለው ትራምፕ ወደ ዋይት ሃውስ ከመግባታቸው ቀናት አስቀድሞ ከተዋወቀው እና የትራምፕ ምሥል ካለው ኮይን ክፍያ 635 ሚሊዮን ዶላር ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በልጆቻቸው እና በልዩ መልዕክተኛቸው ስቲቭ ዊትኮፍ ልጆች ከተመሰረተው 'ዎርልድ ሊበርቲ ፋይናንሻል' ከተባለው የክሪፕቶከረንሲ ድርጅት ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አግኝተዋል።

ከሪልስቴት እና በስማቸው ከተሰሩ ብራንድ ምርቶችም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን አካብተዋል።

ሆኖም ዋይት ሃውስ ትራምፕ በፕሬዚደንትነታቸው ያገኙት ትርፍ የለም ብሏል።

በቅርቡ የወጣው የፋይናንስ ሪፖርት ላይ የተጠቀሰው የትራምፕ ገቢ ከቀደመው ዓመት ማለትም እአአ በ2024 ከነበረው እጅግ የላቀ ነው።

ትራምፕ በ2024 ይፋ ያደረጉት ገቢያቸው ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነበር።

ዋይት ሃውስ ትራምፕ ንግዳቸው በልጆቻቸው እንዲተዳደር ማድረጋቸውን በተደጋጋሚ አፅንኦት በመስጠት ከሥልጣናቸው ጋር ምንም የሚያጋጨው ነገር እንደሌለ በድጋሚ ገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዋይት ሃውስ ምክትል ፕረስ ሴክሬታሪ አና ኬሊ ፕሬዚደንቱ አሜሪካ "የዓለም የክሪፕቶ መዲና" እንድትሆን አድርገዋል ብለዋል።

ኬሊ በመግለጫቸው "ፕሬደዚንቱም ሆኑ ቤተሰባቸው ከሥልጣናቸው ጋር በሚጋጭ ነገር ውስጥ ገብተው አያውቁም፤ አይገቡምም" ሲሉ አክለዋል።

ጨምረውም "በፕሬዚደንት ትራምፕ እና አስተዳደራቸው የተወሰዱት ሁሉም እርምጃዎች ለአሜሪካ ሕዝብ ጥቅም ሲባል የተወሰዱ ናቸው፤ 'ጋዜጠኞች የሚባሉት' ዲሞክራቶች እና የእነሱ ደጋፊ ሚዲያዎች ለአስር ዓመት እያራገቡ ያሉትን ተመሳሳይ ፣ አሰልቺ እና ሐሰተኛ የሆነ ትርክት ነው እየደጋገሙ ያሉት" ብለዋል።

ፕሬዚደንቱ በበኩላቸው ከሕግ ጋር የሚጋጭ ነገር እንዳላደረጉ ገልጸዋል።

ትራምፕ የሆነ ጊዜ ላይ ቢትኮይን በሚል የሚታወቀውን ክሪፕቶከረንሲ "ማጭበርበር እና "ጊዜን የሚጠብቅ አደጋ" ብለውት ነበር።

ሆኖም ማክሰኞ ዕለት የወጣው የፋይናንስ ሪፖርታቸው ከክሪፕቶ ያገኙት ገቢ ወደ ዝና ካስፈነጠራቸው ከሪልስቴት ንግዳቸው ከሚያገኙት ገቢ እንደላቀ አመልክቷል።

ትራምፕ ከማር ኤ ላጎ ክለብ 77 ሚሊዮን ዶላር ገደማ፣ በፍሎሪዳ ዶራል ከሚገኘው የጎልፍ ክለባቸው ደግሞ 122 ሚሊዮን ዶላር አግኝተዋል።

በቤድሚኒስትር፣ ኒው ጀርሲ፣ ጁፒተር፣ ፍሎሪዳ እና ተርንቤሪ፣ ስኮትላንድ ከሚገኘው የጎልፍ ክለባቸው ደግሞ ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ አካብተዋል።

ከሌሎች የንግድ ሥራዎቻቸውም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን እንዳካበቱ የፋይናንስ ሪፖርታቸው ያስረዳል።

ይህም በትራምፕ ብራንድ ከተሰሩ የእጅ ሰዓቶች፣ መጽሐፍ ቅዱሶች፣ አልባሳ፣ ሽቶዎች እና ጊታሮች የተገኘውን 4.7 ሚሊዮን ዶላር ይጨምራል።

በፋይናንስ ሪፖርቱ ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕም ከ2025 ጀምሮ ያገኙት ገቢ ተጠቅሷል።

ሜላኒያ ባለፈው ዓመት ከወጣው ዘጋቢ ፊልማቸው ጋር ከተያያዘ የፈቃድ ስምምነት 10 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተዋል።

በኦንላይን ከተሸጠ ምሥል ደግሞ ተጨማሪ 6 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቸታው ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ፕሬዚደንቱ ከተለያዩ የሕግ እርምጃዎች ሚሊዮን ዶላሮች ማግኘታቸው ተጠቅሷል።

ይህም በኤቢሲ ላይ ከመሰረቱት ክስ 16 ሚሊዮን ዶላር፣ ከሲቢኤስ 16 ሚሊዮን ዶላር፣ ከሜታ 24.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ከዩቲዩብ 22 ሚሊዮን ዶላር፣ ከኤክስ 8 ሚሊዮን ዶላር ያገኙትን ያካትታል።

ሆኖም ዋይት ሃውስ አብዛኛው ገንዘብ ወደፊት ለሚሰራው የትራምፕ ፕሬዚደንታዊ ቤተ መጽሐፍት መግባቱን እና በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ለሚገኘው ትርፋማ ላልሆነ ፓርክ ለመጠበቅ መመደቡን ገልጿል።

በፎርብስ መጽሔት እንደሚዘጋጀው የዓለም ቱጃሮች ዝርዝር ከሆነ ትራምፕ ወደ 6 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብት አላቸው። ይህም በ2024 ከነበረው 2.3 ቢሊዮን ዶላር ሃብታቸው እጅግ የላቀ ነው።

ትራምፕ ወደ ዋይት ሃውስ ከተመለሱ በኋላ ለክሪፕቶከረንሲ ኢንደስትሪ ተስማሚ የሆነ አሰራር ያመጡ ሲሆን ከቤተሰባቸው ጋር የተገናኙ ኩባንያዎች ዲጂታል የሆነ መገበያያ አድርገውታል።

በትራምፕ የተመደቡት የፋይናንስ ተቆጣጣሪ፣ የፀጥታ እና የግብይት ኮሚሽን ኃላፊ ፖል አትኪንስም የክሪፕቶ ኢንደስትሪ አጋር ተደርገው ይታያሉ።

ባለፈው ሐምሌ ወርም ትራምፕ አሜሪካን በዲጂታል ሃብት መሪ ለማድረግ በተለይ ምንዛሬያቸው ከዶላር ጋር ለሚስተከካል ስቴብልኮይኖች ለግብይት እንዲውሉ የሚፈቅደውን 'ጂኒየስ አክት' ሕግ ፈርመዋል።

ከ900 በላይ ገጾችን የያዘው የባለፈው ዓመት የትራምፕ ዓመታዊ ገቢ ሪፖርት የገጽ ብዛት ቀድሞ ከነበሩ መሪዎች የበዛ ነው።

የጆ ባይደን የመጨረሻ የሥልጣን ዓመት ሙሉ የፋይናንስ ሪፖርት 11 ገጾችን የያዘ ነበር።