የሱዳኑ ተፋላሚ አርኤስኤፍ ሰብዓዊ ወንጀል መፈፀሙን የአምነስቲ ሪፖርት አጋለጠ

በትካዜ የተቀመጡ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለፈው ዓመት በኤል ፋሽር ከ6 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተመድ አስታውቋል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

ከሱዳን ጦር ጋር እየተፋለመ ያለው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል- አርኤስኤፍ ሰብዓዊ ወንጀል እና የዘር ማጽዳት መፈፀሙን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሪፖርቱ አጋለጠ።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ረቡዕ ዕለት ባወጣው አዲስ ሪፖርት የአርኤስኤፍ ተዋጊዎች በምዕራብ ሱዳን የምትገኘውን ኤል ፋሽር ከተማን ለመቆጣጠር ባደረጉት ውጊያ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል ሲል ከስሷል።

ሪፖርቱ አርኤስኤፍ ከአውሮፓውያኑ 2024 መጀመሪያ እስከ ጥቅምት 2025 ባሉት ጊዜያት ከሱዳን ጦር እና አጋሮቹ ጋር ፍልሚያ ባካሄደበት ወቅት በኤል ፋሽር ከተማ ውስጥ እና በዙሪያዋ ግድያን፣ የግዳጅ ዝውውርን፣ እስርን፣ ስቅይትን፣ መድፈርን፣ የወሲብ ባርነትን እና ሌሎች ዓይነት ወሲባዊ ጥቃቶችን ፈፅሟል ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለመፈናቀል እንደተገደዱ እና በርካታ ሕፃናት ወላጆቻቸውን እንዳጡ ሪፖርቱ አትቷል።

በጥቃቱ ዒላማ ከተደረጉ ሰዎች መካከል አረጋውያን እና አካል ጉዳተኛ ሰዎች ይገኙበታል ብሏል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ፀሐፊ አግንስ ካላማርድ "በሱዳን ያለው ጦርነት በንጹኃን ላይ የሚካሄድ ጦርነት ነው። አርኤስኤፍ ከተማዋን በከበበት ወቅት በኤል ፋሽር የሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች የተጋፈጡትን አስፈሪ ሁኔታ ዓለም ባስጠነቀቀበት ወቅት የደረሰ የማይሽር ጠባሳ ነው" ብለዋል።

ካላማርድ ጨምረው እንደገለፁት ሕፃናት ሆነ ተብሎ የጥቃት ዒላማ ከመሆናቸው እና ክፉኛ ከመሰቃየታቸው ባሻገር "ተገድለዋል፤ ተጎድተዋል፣ ተጠልፈዋል፤ ለውትድርና ተመልምለዋል"።

አርኤስኤፍ ከዚህ ቀደም የተወሰኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያመነ ሲሆን ተፈፀመ የተባለው የጥሰት መጠን ግን ተጋኗል ብሏል።

ሱዳን በሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት ተቀስቅሶ በአገሪቱ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል ላለፉት ሦስት ዓመታት እየተካሄደ ባለው ጦርነት ከመላው ዓለም ግንኙነቷ ተቋርጧል።

እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከ14 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለመፈናቀል ተገደዋል።

በሕፃናት፣ በሴቶች እና ወንዶች ላይ መጠነ ሰፊ የወሲብ ጥቃት እንደ የጦር መሣሪያ ጥቅም ላይ እንደዋለ የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።

በእነዚህ ወንጀሎች ተፋላሚዎቹ አርኤስኤፍ እና የሱዳን ጦር ኃይሎች ይከሰሳሉ።

ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር አርኤስኤፍ ከዋና መዲናዋ ኻርቱም ተገፍቶ ከወጣ በኋላ ትኩረቱን በኮርዶፋን ክልል እና በኤል ፋሽር ከተማ ላይ አድርጓል።

መሬት ላይ ቁጭ ብላ ሁለት ልጆቿን ያቀፈች እናት

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሱዳን ሁለቱም ተፋላሚዎች ሰላማዊ ዜጎችን በተለያዩ መንገዶች እና ሆን ብለው ስልታዊ ጥቃት በማድረስ ይከሰሳሉ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ለሪፖርቱ ከጥቃት የተረፉ እና ጥቃቱ ሲፈፀም የተመለከቱ 208 ሰዎችን ጨምሮ ለ247 ሰዎች ቃለመጠይቅ አድርጓል።

ተቋሙ የሰበሰበው መረጃ እንደሚያመለክተው አብዛኞቹ ሰለባዎች ዒላማ የተደረጉት እና የተገደሉት በብሔር ማንነታቸው ነው።

በ2024 መጀመሪያ ላይ በኤርኤስኤፍ ተፈፀመ የተባለው ወንጀል ዒላማ ያደረገው በሱዳን የሚኖሩ እና አረብ ያልሆኑ - ዛጋዋ ብሔርን እንደሆነ ሪፖርቱ ጠቅሷል።

እነዚህ ከአርኤስኤፍ ጋር የተያያዙ ወንጀሎች አሁንም በተቆጣጠራቸው አካበቢዎች መቀጠላቸውን የገለጸው አምነስቲ፣ የተፈናቀሉ ሰዎች እንዳይመለሱ በመከልከል በኤል ፋሽር አካባቢ የሚገኙ ዛግዋ ብሔር ላይ የዘር ጭፍጨፋ መፈፀማቸውን ገልጿል።

አምነስቲ ቃለ መጠይቅ ያደረገለት ከኤል ፋሽር ደቡባዊ ክፍል 35 ኪሎሜትር በምትርቀው አቡ ዘረጋ ከተማ ነዋሪ የሆነ የ17 ዓመት የዛግዋ ብሔር ታዳጊ የደረሰበትን ጥቃት ሲገልጽ "አስረው እግሬን እንዳይሆን አድርገው ደበደቡኝ" ብሏል።

ያቆብ የተባለው ታዳጊ [ስሙ የተለወጠ] አሁን ላይ በክራንች በመታገዝ ነው የሚራመደው።

ዕድሜያቸው ከ11 እስከ 17 የሚሆን አራት ወንድ ልጆችን ጨምሮ ስምንት የአክስትና አጎት ልጆቹም በተመሳሳይ ጥቃት ተገድለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ አምነስቲ ከግንቦት 2024 እስከ ጥቅምት 2025 ባሉት ጊዜያት ኤል ፋሽርን ከበባ ውስጥ በማስገባት ምግብ እና ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ከተማ እንዳይገባ በማድረግ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ከስሷል።

በሰሜን ዳርፉር ግዛት መዲና ጥቅምት 2025 የመጨረሻው ጥቃት ከመፈፀሙ በፊት ሴቶች የቦምብ ድብደባ እየተፈፀመ በሆስፒታል ውስጥ እንዲወልዱ የተገደዱ ሲሆን በርካቶች ጨቅላ ልጆቻቸውን መመገብ አልቻሉም።

ሪፖርቱ አርኤስኤፍ መድፈርን ጨምሮ መጠነ ሰፊ ወሲባዊ ጥቃቶች መፈፀሙንም ጠቅሷል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ጥቃቱ በደረሰበት ወቅት ለአቅመ ሄዋን ያልደረሱ ታዳጊዎች የነበሩ ተጎጂዎችን አነጋግሯል።

ታስኒም [ስሟ የተለወጠ] የተባለች የ13 ዓመቷ የዛጋዋ ብሔር ታዳጊ "ለመጀመሪያ ጊዜ ስደፈር ሦስት ሰዎች ነበሩ። ዓይኔን ሸፍነውኝ ነበር" ስትል ለአምነስቲ ተናግራለች።

የምርመራ ሪፖርቱ አርኤስኤፍ አረብ እንዲሁም አረብ ያልሆኑ በርካታ ወንድ ታዳጊዎችን ለውትድርና በግዳጅ መመልመሉንም ገልጿል።

አምነስቲ ከፍተኛ በሆነ ዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት የአርኤስኤፍ የጦር አዛዦችን ተጠያቂ አድርጓል።

በመብት ተሟጋቹ የተሰበሰቡ ቪዲዮዎች በስፋት አቡ ሉሉ በመባል የሚታወቁት ኮማንደር አል ፋታህ አብዱላህ ኢድሪስ የሲቪል ልብስ የለበሱ ሰዎችን ሲረሽኑ አሳይተዋል።

አቡ ሽኩር በመባል የሚታወቁትን ገዶ ሃምዳን አሕመድ መሃመድንም በሰሜን ዳርፉር በሚገኘው አስከፊው ሚና አል ባሪ እስር ቤት የሰብዓዊ ጥሰት እንዲፈፀም ትዕዛዝ በመስጠት ከስሷል።

አምነስቲ የአርኤስኤፍ መሪ መሃመድ ሃምዳን ደጋሎን ምላሽ እንዲሰጡ እንደጠየቀ እና ሪፖርቱ እስከሚወጣበት ጊዜ ድረስ ምላሽ እንዳለገኘ ገልጿል።

በሱዳን አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ ያቀረበው አምነስቲ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድም አሳስቧል።

ጨምሮም በሱዳን ለሚገኙ ተፈላሚ ወገኖች የጦር መሳሪያ እና ተተኳሾችን በማቅረብ የሚደግፉ አገራትም በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርቧል።

ሪፖርቱ በኤል ፋሽር የተፈፀመው ጥቃት ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ላይ የተባበሩት መንግሥታት እንዳለው "ለዘር ማጥፋት የተቃረበ" እንደሆነም አክሏል።

ተመድ በሪፖርት በኤል ፋሽር በሦስት ቀናት ውስጥ በተፈፀመ ጥቃት ከ6 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን ማስታወቁ ይታወሳል።