ለሽብር ተከሳሾች የቀረበውን "የይቅርታ ሰነድ" ካልፈረሙት አንዱ የሆነው ካናዳዊው እሱባለው ማነው?

ካናዳዊው ትውልደ ኢትዮጵያዊ እሱባለው በለጠ፣ በአማራ ክልል ካለው ቀውስ ጋር በተያያዘ በሽብር ከተከሰሱት አንዱ ነው
የምስሉ መግለጫ, ካናዳዊው ትውልደ ኢትዮጵያዊ እሱባለው በለጠ፣ በአማራ ክልል ካለው ቀውስ ጋር በተያያዘ በሽብር ከተከሰሱት አንዱ ነው
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ይቅርታ ጠይቀው ከእስር እንዲለቀቁ ፊርማቸውን የሚያኖሩበት "የይቅርታ ሰነድ" ከቀረበላቸው ከ300 የሚልቁ የሽብር ተከሳሾች ውስጥ የካናዳ ዜግነት ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ይገኛል።

ካናዳዊው እሱባለው በለጠ ብርሃኔ፣ በአማራ ክልል ካለው ቀውስ ጋር በተያያዘ በሽብር ለተከሰሱ እስረኞች የቀረበውን "ይቅርታ መጠየቂያ ሰነድ" አንፈርምም ማለታቸው ከተረጋገጠ 30 ተጠርጣሪዎች አንዱ ነው።

በካናዳ የቶሮንቶ ፒርሰን አየር ማረፊያ "ከፍተኛ የአውሮፕላን ጥገና ባለሞያ" ሆኖ ሲሠራ የነበረው እሱባለው በለጠ፣ መስከረም 24/2018 ዓ.ም ነበር በቁጥጥር ስር የዋለው።

የእሱባለውን የክስ ሂደት በተመለከተ ለቢቢሲ ማብራሪያ የሰጡት ጠበቃው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ፣ እሱባለው ወደ ኢትዮጵያ የሄደው ጳጉሜ 3/2017 ዓ.ም. እንደነበረ ተናግረዋል።

ወደ ትውልድ አገሩ የሄደበትም ምክንያትም የወላጅ እናቱን ህልፈተ-ሕይወት ተከትሎ ለለቅሶ እንደነበረ ነው የጠቀሱት።

እግረ-መንገዱን አዲስ ዓመትንም በባሕር ዳር ከቤተሰቡ ጋር አሳልፎ መስከረም 22 ወደ አዲስ አበባ ስለመመለሱ የገለፁት ጠበቃው፣ መስከረም 24 ከኢትዮጵያ ወደ ካናዳ ለመመለስ "ቼኪንግ ጨርሶ ወደ ውስጥ ከገባ በኋላ" አውሮፕላን ሊሳፈር ሲል ከቦሌ አየር ማረፊያ ነው "በፀጥታ ኃይሎች የተያዘው" ብለዋል።

የተጠረጠረበት ወንጀል "በአማራ ክልል ለሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ኃይል የሎጂስቲክስ ድጋፍ ታደርጋለህ" የሚል እንደሆነ ነው ጠበቃው የሚገልፁት።

በውጭ ካሉ የፋኖ ደጋፊዎች ጋር በመተባበር እንደሚንቀሳቀስ እና ባሕር ዳር የሄደውም በዚህ መልክ የተገኘውን "የቁሳቁስ ድጋፊ ለታጣቂው ኃይል ለማድረስ ነው" በሚል እንደተጠረጠረ አክለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ምርመራው ከተጠናቀቀ በኋላ ዋስትና ተከልክሎ ዐቃቤ ሕግ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም. የመሠረተበትን የሽብር ክስ ሂደት እየተከታተለ ይገኛል።

የቀረበበትም ክስ የሽብር አዋጅ 1176/12 አንቀጽ ዘጠኝን በመተላለፍ "የሎጂስቲክስ ድጋፍ በማድረግ" የሚል ነው ጠበቃው አቶ ሰለሞን እንዳሉት።

ከታሰረ ወደ አንድ ዓመት እየተጠጋው የሚገኘው እሱባለው በለጠ፣ ባለትዳር እና የአንድ ልጅ አባት ነው።

ሰሞኑን እሱባለውን ጨምሮ ከ300 በላይ ለሆኑ ተከሳሾች በመንግሥት ቀረበ የተባለው የይቅርታ ሰነድ "በአማራ ክልል ላለው ቀውስ፣ ለሞቱ ሰዎች እና ለወደመው ንብረት" ኃላፊነት እንዲወስዱ "ፋኖንም እንዲያወግዙ" የሚጠይቅ ይዘት ያለው መሆኑ ተገልጿል። ሰነዱን ለመፈረም ፈቃደኛ አልሆነም።

አብዛኛው ተከሳሾች ሰነዱን መፈረማቸው ታውቋል።

በአሁኑ ወቅት ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተዛውሮ እዚያ ከሚገኙ የሽብር ተከሳሾች ጋር ታስሮ የሚገኘው እሱባለው፣ ምንም እንኳን "ወንጀሉን አልፈፀምኩም" ብሎ በፍርድ ቤት በመከራከር ላይ ቢሆንም "ለመፈታት ካለው ጉጉት የተነሳ ሰነዱን ለመፈረም" አስቦ እንደነበረ ጠበቃው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ የካናዳ ኤምባሲ በሰጠው ማስጠንቀቂያ ምክንያት ሳይፈርም መቅረቱን ነው የገለፁት።

"የይቅርታ መጠየቂያ ሰነዱ" ከደረሳቸው በኋላ በቤተሰቡ አማካኝነት እንዳስጠራቸው ጠቅሰው "ሄጄ አናግሬው ነበር" የሚሉት አቶ ሰለሞን፣ "ወደ ካናዳ ተመልሼ ልጄን እና ባለቤቴን መቀላቀል በመፈለጌ ሰነዱን እፈርማለሁ ብዬ ነበረ" እንዳላቸው አስረድተዋል።

ነገር ግን፣ ጉዳዩን በመከታተል ላይ እንደሚገኝ የጠቀሰውን በኢትዮጵያ የካናዳ ኤምባሲ ሲያማክር "ከፈረምክ እዚያም [ካናዳ] ስትመለስ ልትጠየቅበት የምትችልበት ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል፣ ኃላፊነቱን ራስህ ትወስዳለህ፤ ስለዚህ መፈረም የለብህም ራስህን ነጻ ለማውጣት መሞከር ነው ያለብህ" በመባሉ ምክንያት አለመፈረሙን እንደነገሩት ገልፀዋል።

የካናዳ መንግሥት "በጽኑ የሚደግፈውን" ንጹህ ሆኖ የመገመት መብት "ልታጣ አይገባም፤ ራስህን መከላከል ይሻልኻል" የሚል ምክረ-ሃሳብ እንደተሰጠው ጠቅሰዋል።

የእሱባለውን ጉዳይ ኤምባሲው በመከታተል ላይ እንደሚገኝ የካናዳው "ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል" ሚዲያ ከአምስት ወር ገደማ በፊት መጋቢት ወር ላይ በድረገጹ ባወጣው ዘገባ ላይ አስፍሮ ነበር።

የካናዳ ባለሥልጣናት የማማከር አገልግሎት እየሰጡት እና ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገሩ እንደሚገኙም ከኤምባሲው ማረጋገጡን ዘገባው አካቷል።