ፓኪስታ እንዴት አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ላይ እንዲደርሱ ማገዝ ቻለች?

የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በኢራን እና አሜሪካ መካከል ለሁለት ሳምንታት የሚዘልቅ የተኩስ አቁም ስምምነት ከመታወጁ ከጥቂት ሰዓታት አስቀድሞ በፓኪስታን በኩል የተስፋ ጭላንጭሎች እየታዩ ነበር።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የገለጹ የፓኪስታን ምንጭ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አገራቸው በኢራን እና በአሜሪካ መካከል የማሸማገል ሥራዋን "በፍጥነት" ማከናወን ቀጥላ ነበር።

ከፓኪስታን ወገን ድርድሩን የሚመሩት ሰዎች "በጣም ጥቂት" ናቸው። አሸማጋዮቹ ዘንድ የነበረው ስሜት ሁኔታው "አስቸጋሪ እና ከባድ" እንደሆነ የሚጠቁም ነበር። የትራምፕ ቀነ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት ስምምነት ላይ ለመድረስ "ጥቂት ሰዓታት ብቻ" ቀርቷቸው ነበር።

ቢሆንም ግን "ጦርነትን የሚያስቆም ስምምነት እንደሚኖር ተስፋ አድርገው" እንደነበር የቡድኑ አባል ያልሆኑት ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፓኪስታን ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በኢራን እና በአሜሪካ መካከል አሸማጋይ ሆና በሁለቱ አገራት መካከል መልዕክቶችን ስታስተላልፍ ቆይታለች።

ፓኪስታን ከኢራን ጋር ታሪካዊ ግንኙነት ያላት ሲሆን ድንበር ከመጋራት በተጨማሪ ከአገሪቱ ጋር "የወንድማማች" ግንኙነት እንዳላት አዘውትራ ትጠቅሳለች።

ከአሜሪካ ጋርም ግንኙነት አላት። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የፓኪስታን የጦር ኃይሎች አዛዥ አሲም ሙኒር "የሚወድዷቸው" ፊልድ ማርሻል እንደሆኑ ሲናገሩ ተደምጠዋል። "ከአብዛኛዎቹ በተሻለ ሁኔታ" ኢራንን ያውቋታል ሲሉም አሞካሽተዋቸዋል።

በስምምነቱ ማንም እርግጠኛ አልነበረም። የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሻቅ ዳር ማክሰኞ ምሽት በፓርላማ ባደረጉት ንግግር እስራኤል ሰኞ ዕለት በኢራን ላይ ጥቃት ከመሰንዘሯ እና ኢራን ሳዑዲ አረቢያን ከማጥቃቷ በፊት "ነገሮች በጥሩ አቅጣጫ እየተጓዙ እንደሆነ በጣም ተስፋ አድርገን ነበር" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፓኪስታን "ነገሮችን በተቻለ መጠን ለመቆጣጠር እየሞከረች ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

ፊልድ ማርሻል ሙኒር ግልጽ የሆነ ትችት ሰንዝረዋል። ማክሰኞ ዕለት ለወታደራዊ ባለስልጣናት ሲናገሩ በሳዑዲ አረቢያ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት "ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ያበላሻል" ብለዋል።

ይህ ግጭቱ ከተጀመረ ወዲህ ፓኪስታን ለኢራን ያስተላለፈችው ጠንካራ መልዕክት ነው።

አንዳንድ ተንታኞች ይህ በኢራን ላይ ጫና ሊጨምር እንደሚችል ጠቁመዋል። ፓኪስታን ከሳዑዲ አረቢያ ጋር የመከላከያ ስምምነት አላት። ሳዑዲ አረቢያ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች መሰንዘራቸውን ተከትሎ ግን ይህ ስምምነት አልተነሳም።

እኩለ ሌሊት ላይ የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር በኤክስ ገጻቸው ላይ "ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች… ተጨባጭ ውጤቶችን ለማምጣት በሚያስችል መልኩ እየተሻሻሉ ነው" ሲሉ ጽፈዋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያስቀመጡትን የጊዜ ገደብ ለሁለት ሳምንታት እንዲያራዝሙ እና ኢራንም ለተመሳሳይ ጊዜ የሆርሙዝን ወሽመጥን እንድትከፍት ጠይቀዋል።

በፓኪስታን የኢራን አምባሳደር ሬዛ አሚሪ ሞጋዳም "አንድ ወሳኝ ደረጃ ወደፊት ተራምደናል" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

በኋላም የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር የተኩስ አቁም ስምምነት መደረሱን አስታውቀው ሁለቱ ወገኖች አርብ በኢስላማባድ ተገናኝተው "ለሁለንተናዊ ስምምነት እንዲደራደሩ" ጋብዘዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የፓኪስታን ምንጭ "አሁንም በጣም ጥንቃቄ እያደረግን ነው" ሲሉ ሁኔታው "ሊፈርስ" የሚችልበት ዕድል እንደሚኖር ጠቁመዋል። በሁለቱ ወገኖች መካከል ምንም ዓይነት እምነት የሌለ ሲሆን ጠንካራ አቋምም ይዘው ይገኛሉ።

ፓኪስታን ሁለቱንም ወገኖች ወደ ክብ ጠረጴዛ ማምጣት ብትችልም በምን ጉዳይ ላይ ሊስማሙ ይችላሉ የሚለው ግን አሁንም ጥያቄ ሆኗል።