ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አገራዊ ምክክር እየተደረገ ያለው የአገሪቱን መሪ የሥልጣን ዘመን "ለመገደብ" መሆኑን ተናገሩ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አገራዊ ምክክር እየተደረገ ያለው በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ያለ ማብቂያ የተቀመጠውን የአገሪቱን መሪ የሥልጣን ዘመን "ለመገደብ" መሆኑን ተናገሩ።
መንግሥት "ሥልጣኑ በሕግ ተገድቦ" ሕገ መንግሥት እንዲሻሻል እየጠየቀ ባለበት ሁኔታ በአገራዊ ምክክሩ "አንወያይም" ያሉ አካላትን ተችተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን የተናገሩት የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዛሬ አርብ ግንቦት 7/2018 ዓ.ም. የአፈፃፀም ሪፖርቱ ባቀረበበት ዝግጅት ላይ ነው። ዝግጅቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንደተገኙ ተገልጿል።
በፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ መንግሥታቸው ለኮሚሽኑ የሚያደርገው ድጋፍ እንደቀሚጥል በድጋሚ አረጋግጠዋል።
"አሁን ያለው መንግሥት ሥልጣን ዘመኑን" ከማጠናቀቁ በፊት ኮሚሽኑ ምክረ ሀሳቦቹን ካቀረበ "በተቻለ መጠን […] መሬት ለማውረድ" እንዲሁም "ምክረ ሃሳቦቹን ተጠቅሞ ለማሻሻል" ዝግጁ እንደሆነም አስረድተዋል።
ብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ የቀረበው የሦስት ደቂቃ ገደማ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ቪድዮ እንደሚያሳየው፤ ዐቢይ በኮሚሽኑ የሥራ አፈጻጸም "መኩራታቸውን" ገልጸዋል።
"ልጆቻችን በታሪክ ማኅደር ውስጥ የእናንተን ሥራ፣ የእናንተን ታሪክ እየመነዘሩ እያዩ ብዙ ትምህርት እንደሚያገኙበት ብዙ ጥርጥር የለውም" ብለዋል።
ዐቢይ እንደተናገሩት "በብዙ የአፍሪካ አገራት" ይህ ዓይነቱ ተግባር የተከናወነው የምክክር ኮሚሽኑ አመራሮች "ባለፉበት መንገድ" አይደለም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "የአብዛኛው አፍሪካ አገራት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ የተደረገው የመሪዎቹን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት "የሚቀየረው" ግን ከዚህ ተቃራኒ በሆነ ሁኔታ የአገሪቱ መሪ የሥልጣን ቆይታ ላይ ገደብ ለማበጀት መሆኑን አስረድተዋል።
"በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲው እስካሸነፈ ድረስ እና መመረጥ እስከቻለ ድረስ የጊዜ ገደብ የለበትም። አሁን እየተወያየን ያለነው ግን ያ አደገኛ ነው፤ እንገድብ ብለን ነው" ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ሕገ መንግሥቱ የጸደቀው "ጥቂት መቶዎች ተሰብስበው ነው" ያሉት ዐቢይ፤ "በሌላም አገር እንደዚህ ዓይነት ውይይት አይተን አናውቅም" ሲሉ ተደምጠዋል።
መንግሥት ይህንን ዓይነት ተነሳሽነት መውሰዱ በአገራዊ ምክክሩ "አልወያይም ያሉ ሰዎች ራሳቸውን እንዲጠይቁ የሚያስገድድ ነው" የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት መንግሥት "ወዶ፣ ፈቅዶ፤ ሕዝብ ተወያይቶ፣ ሥልጣኔ በሕግ ተገድቦ፣ የሕዝብ ጥያቄዎችን በሕገ መንግሥት ተካትተው እንዲሻሻሉ ፈቃድ አለኝ" እያለ መሆኑን አንስተዋል።
መንግሥት ይህንን ሲል "ለዚያ መሻት የሚታገሉ ሰዎች እንዴት 'አንወያይም' ይላሉ? ካልተወያዩስ ለምን ፖለቲካ ይፈልጋሉ? ፖለቲካ በዋነኛነት ውይይት ነው" ሲሉ ተችተዋል።
"የፖለቲካ፣ የሥልጣን ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ይሄንን ለማሻሻል ክፍተት የሚሰጥ ውይይት ከመንግሥት በላይ ደስተኛ ሆነው መሳተፍ የሚጠበቅባቸው ይመስለኛል" ብለዋል።
ይህም ቢሆን ግን አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ተግባር "ከበቂ በላይ፤ የኢትዮጵያን ፍላጎት መመለስ የሚችል ከ90 ፐርሰንት በላይ ኢትዮጵያውያንን ያሳተፈ ሂደት" መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ የተነሳም "ለምናስበው ለውጥ፣ ለምናስበው ሪፎርም መሠረት መጣል የሚችል ይመስለኛል" ሲሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአገሪቱ 1,234 ወረዳዎች ውስጥ "ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና ልየታ" ተግባር ማከናወኑን ዛሬ ባቀረበው ሪፖርት ገልጿል። በዚህ ተግባሩም የአገሪቱን "93 በመቶ" መሸፈኑን አስታውቋል።
ይህንን ተመሳሳይ ሂደት ትግራይ ክልል ውስጥ ማካሄድ ያልቻለው ኮሚሽኑ፤ በአዲስ አበባ ባካሄደው ስብሰባ "ከመላው የትግራይ ክልል የተውጣጡ ባለድርሻ አካላትን እና በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጆችን" ማሳተፉን በሪፖርቱ ጠቅሷል።
በቀጣይ የአገራዊ ምክክር አጀንዳዎችን እንደቀሚርጽ እና የአገራዊ ምክክር ጉባኤን እንደሚያካሂድ አስታውቋል። "በአገር ደረጃ ስምምነት የተደረሰባቸውን ውጤቶች እና ምክረ ሀሳቦች ተፈፃሚነትን" እንደሚያመቻችም ተገልጿል።