የፈረሰው የፕሪቶሪያው ስምምነት፣ አዲስ የተቀሰቀሰው ጦርነት እና የቀጣናዊ ግጭት ስጋት

የፕሪቶሪያው ስምምነት ሲፈረም አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ኡሁሩ ኬንያታ እና ጌታቸው ረዳ
የምስሉ መግለጫ, የፕሪቶሪያው ስምምነት ሲፈረም አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ኡሁሩ ኬንያታ እና ጌታቸው ረዳ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

ደም አፋሳሹን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ያስቆመው የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም የሰላም ስምምነት የተፈረመው በጥቅምት 2015 ዓ.ም. ነበር።

ይህ 15 አንቀፆች ያሉት ስምምነት የኢትዮጵያ መንግሥትን እና የህወሓት ወኪሎችን ጨምሮ የአምስት ተሳታፊዎች ፊርማ ያረፈበት ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከትግራይ ተወካዮች ጋር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈራረሙትን ይህንን ስምምነት የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ "ወሳኝ የመጀመሪያ እርምጃ" ብለውት ነበር።

ዓለም አቀፍ ድጋፍ በተቸረው በዚህ ስምምነት ላይ ሙሉ በሙሉ አልተፈፀመም የሚሉ ክሶች መቅረብ የጀመሩት በወራት ውስጥ ነበር።

በተለይም የይገባኛል ውዝግብ ያለባቸው ደቡባዊ እና ምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች እንዲሁም የተፈናቃዮች መመለስ ጉዳይ ጠንካታ ጥያቄዎች የተነሱባቸው ናቸው።

የህወሓት አመራሮች በሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ የሚመራውን ጊዜያዊ አስተዳደር አንስተው የራሳቸውን አስተዳደር በክልሉ ውስጥ ከመሠረቱ ወዲህ የፕሪቶሪያው ስምምነት መፍረሱን በይፋ በማወጃቸው ከፌደራል መንግሥቱ ጋር መካረር ውስጥ ገብተው ቆይተዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊትም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥትን ለመጣል እንደሚፈልጉ በመግለጽ ከስድስት ታጣቂ ቡድኖች ጋርም ጥምረት መሥርተዋል።

የፕሪቶሪያ ስምምነት 11 ዋነኛ ዓላማዎችን የያዘ ሲሆን፣ ቁልፍ የሚባሉትም ግጭቶችን ማስወገድ፣ ሰላም እና ደኅንነት ማስፈን፣ የህወሓት ተዋጊዎችን ትጥቅ ማስፈታት እና ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀል፣ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም እንዲሁም የሽግግር ፍትሕ መተግበርን ያካትታሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
BBC News Amharic የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናላችንን ይቀላቀሉ!
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሆኖም ተፈራሚዎቹ በስምምነቱ ነጥቦች ላይ ጥሰት በመፈፀም እርስ በርስ ይካሰሳሉ። ታዛቢዎች በበኩላቸው፣ ችግሩ በስምምነቱ አፈጻጸም ሂደት ውስጥ የተካተቱ በርካታ ቁልፍ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ አልተፈፀሙም ይላሉ።

የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ለገዢው ፓርቲ ቅርብ ለሆነው ፋና ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ "የስምምነቱ ቀዳሚ ጉዳይ ግጭት ማቆም ነው፤ ይህ እስከ አሁን ሙሉ በሙሉ የፈጸምነው ነው። ሁለተኛው ማኅበራዊ አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ አድርገናል። ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ የፌደራል መንግሥት ሥራ ብቻ ሳይሆን የጋራ ሥራ ነው" ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ከወልቃይት የተፈናቀሉ ዜጎች ይመለሱ ቢባልም ህወሓት ግን "እንዲቆዩ እና የፖለቲካ አጀንዳ ማፈስጸሚያ እንዲሆኑ" ማድረጉን በመጥቀስ ከስሰዋል።

አክለውም "እኛ መሠረታዊ ሥራዎችን ሠርተናል፤ በእነሱ በኩል ግን ምንም አልሠሩም ማለት ይቻላል። አንደኛው ግጭት የሚቀሰቅስ ነገር አለማረድግ ነው፤ በተደጋጋሚ ትንኮሳ ነበር። ወደ ሰላም ከመምጣት ይልቅ ሠራዊት ሲያሰለጥኑ፣ ትጥቅ ሲያስገቡ፣ ከአገር ውስጥ ግጭት ፈጣሪዎች ብቻ ሳይሆን ከባዕዳን ጋር ሲሠሩ ስምምነቱን በየቀኑ ሲፈያርሱት ነበር" ብለዋል።

የህወሓት መሪዎች በበኩላቸው፣ የፌዴራል መንግሥት ለክልሉ የሚመደበውን በጀት በመቀነስ፣ በክልሉ ላይ የኢኮኖሚ ጫና በመፍጠር፣ እንደ ጤና እና የትምህርት የመሳሰሉ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማስተጓጎል እንዲሁም የውኃ አቅርቦት እጥረት በመፍጠር ለከፍተኛ ችግር በማጋለጥ የፕሪቶሪያ ስምምነቱን ጥሷል ሲሉ ይከሳሉ።

የትሪኢስቴ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ፌዴሪኮ ዶኔሊ ስምምነቱ በትግራይ ከፍተኛ ውድመት ያስከተለውን ጦርነት በማስቆም ውጤት አምጥቷል ይላሉ።

"ነገር ግን ስምምነቱ በራሱ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ መፍትሔ አልነበረም። ትግበራውም ሰፊ የፖለቲካ ሂደት እንዲጀመር አስፈላጊ ሁኔታን መፍጠር መቻል ነበረበት" ብለዋል።

አፍሪካውያን ለአፍሪካ ቀንድ በተባለ ድርጅት ውስጥ የሰላም እና ደኅንንት ባለሙያ የሆኑት ስቴላ ንዲራንጉ በበኩላቸው "ለተወሰነ ጊዜ የቆየው የስምምነቱ ዋነኛ መሠረት የሰላም ሁኔታው ነበር። ሌላው ወሳኝ ነጥብ እና አሁንም ዋነኛ ያለመግባባት ምንጭ የሆነው ጉዳይ ግን ከመከላከያ ሠራዊት ውጭ የሆኑ ኃይሎች ከትግራይ አለመውጣታቸው ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለሁለት ዓመት በተካሄደው ጦርነት የፌዴራል መንግሥቱን ለመደገፍ ወደ ትግራይ የገቡ ኃይሎች ከቦታው አለመውጣታቸውን በመጥቀስም "ጥሰቶችም ቀጥለዋል" ሲሉ ለቢቢሲ አብራርተዋል።

ባለሙያዋ አክለውም ስምምነቱ በጦርነቱ ወቅት የፌደራል መንግሥቱን ይደግፉ የነበሩ ሌሎች ኃይሎች ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ልዩነት እና መራራቅ ማድረጉን ይጠቅሳሉ።

እነዚህ ከመንግሥት ጋር ቅራኔ ውስጥ የገቡ ኃይሎች በሥልጣን ላይ ያለውን አስተዳደር ለማፍረስ በመስማማት "ትብብር ለኅልውና" የሚል ጥምረት መሥርተው በጋራ ለመቆም መንገድ ማግኘታቸውን አንስተዋል።

በትግራይ የመጀመሪያው ጦርነት ጦርነት ሲቀሰቀስ፣ የኤርትራ እና የአማራ ኃይሎች ከፌደራል መንግሥቱ ጎን ተሰልፈው ነበር። ደም አፋሳሹ ጦርነት በድርድር ከተቋጨ በኋላ የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ እንደተናገሩት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ወደ 600 ሺህ ገደማ እንደሚደርስ ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ውስጥ በሰላም፣ በግጭት አፈታት እና በሕግ ዙሪያ ከሦስት አሥርት ዓመታት ያገለጉት ባይሳ ዋቅወያ የፕሪቶሪያ ስምምነት በሚፈረምበት ወቅት በሁለቱ የስምምነቱ ፈራሚዎች መካከል ብዙም አከራካሪ ነገር ነበር ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ።

ይህንንም ሲያስረዱ "ስምምነቱ ወደ አንድ በኩል ያደላ ነበር። ህወሓት በስምምነቱ ያገኘው ነገር ቢቆጠር ጥቂት ነው፤ የፌደራል መንግሥቱ ያገኘው ይበዛል። ይህ የሚያመለክተው ሁለቱ ወገኖች በእኩል በሚያገኙት እና በሚሰጡት መካከል እኩል መግባባት አልረነበራቸውም ባይ ነኝ። ነገር ግን ሰላምን ማስፈን ከፈለጉ ስምምነቱ ሁለቱንም አይጎዳም" ብለዋል።

ታንክ

ስምምነቱ ለምን ፈረሰ?

ለስምምነቱ መፍረስ ከተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው አለመመለስ ባሻገር በለምነቱ የሚታወቀው ምዕራብ ትግራይ አንዱ አወዛጋቢ ጉዳይ ነው።

ይህ አካባቢ ጦርነቱ በተጀመረበት ጊዜ ከህወሓት ቁጥጥር ውጭ በመሆን በአማራ ኃይሎች እጅ ገብቷል።

በዚህም ምክንያት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ወደ ሌሎች የትግራይ አካባቢዎች እና ወደ ሱዳን ተሰደዋል።

ህወሓት ምዕራብ ትግራይ እንዲመለስ እና ተፈናቃዮችም ወደቀያቸው እንዲመለሱ ይፈልጋል። የፌደራል መንግሥቱ በበኩሉ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታዎች ዕጣ ፈንታ በሕዝበ ውሳኔ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ይላል።

ለተባባሪ ፕሮፌሰር ፌደሪኮ የፕሪቶሪያ ስምምነት "መዋቅራዊ ተጋላጭነት" አሉበት። የመጀመሪያው ጉዳይ በክትትል እና በማስፈጸም መካከል ያለው ልዩነት ነው።

ፌደሪኮ የአፍሪካ ኅብረት ስምምነቱ ተፈጻሚ እንዲሆን በመከታተል ረገድ ጠቃሚ ሚና መጫወቱ አያጠራጥርም ይላሉ። ሆኖም ተዋዋይ ወገኖች የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ ለማስገደድ ወይም ለማስፈጸም የሚያስችለው የፖለቲካ አቅም ግን ላይኖረው እንደሚችል ገልጸዋል።

ሁለተኛው መዋቅራዊ ተጋላጭነት ደግሞ "መተማመን" ነው። ስምምነቱ ውጊያውን አስቆመ፤ ነገር ግን ውጊያን ማቆም ብቻ በጦርነት ላይ ቆይተው በነበሩ ወገኖች መካከል መተማመንን አይገነባም። ይህ ነው የተፈጠረው ነገር ሲል ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በፕሮፌሰሩ እምነት ሦስተኛው ጉዳይ ደግሞ ቅደም ተከተል ጉዳይ ነው። የደኅንነት፣ የድንበር፣ የፖለቲካ ውክልና እና የተፈናቃዮች መመለስ እርስ በርስ የተነጣጠሉ ጉዳዮች አለመሆናቸውን ያስረዳሉ።

ሁሉም በተያያዘ መልኩ የተሳሰሩ ናቸው የሚለው ፌደሪኮ፣ በዚህም ምክንያት አንድ ዓይነት አዙሪት መፈጠሩን ይናገራሉ።

ያልተፈታ የፖለቲካ ጉዳይ የደኅንነት ስጋትን ሲያባብስ፣ ያልተፈታ የደኅንነት ጉዳይ ደግሞ የፖለቲካ መግባባትን የበለጠ አስቸጋሪ አድርጎታል ይላሉ።

ባለሙያው አራተኛው መዋቅራዊ ተጋላጭነት የሚሉት ተሳትፎ ነው። የፕሪቶሪያ ስምምነት ላይ ኤርትራ እና የአማራ ክልል ኃይሎች የስምምነቱ ፈራሚ አለመሆናቸውን በመጥቀስ "ሆኖም እነዚህ ኃይሎች የደኅንነት ሁኔታውን በመቅረጽ ረገድ ተጽዕኖ ነበራቸው። በመጨረሻም፣ እንደሚታየኝ ፕሪቶሪያ ስምምነት ከጦርነቱ መቆም በኋላም ቀጣይነት ባለው የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ ከፍተኛ ጥገኛ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ የፖለቲካ ምኅዳር እየተዳከመ ሲመጣ፣ ስምምነቱም እየተጋለጠ መጣ" ይላሉ።

በዚህ መልኩ፣ ፕሪቶሪያ ከጦርነቱ ማቆም በኋላም የቀጠለውን ጥልቅ የፖለቲካ አለመግባባት ለመፍታት ያለው አቅም ውስን እንደነበር ጨምረው አብራርተዋል።

ስምምነቱ ጸንቶ ባለመቀጠሉም በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ዳግም ተቀስቅሷል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተዋጊ ወገኖች አሰላለፍ ተቀይሯል።

በቀደምው ጦርነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን የነበሩት የኤርትራ እና የፋኖ ኃይሎች ከህወሓት ጎን ቆመዋል።

ከትግራይ ኃይሎች የወጡ ተዋጊዎች እና የህወሓት ባለሥልጣናት ደግሞ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ተሰልፈዋል።

ግጭቱ ወደ ቀጣናው ሊስፋፋ የሚችልበት ዕድል እንዳለም እየተነገረ ነው።

የሰላም እና ደኅንነት ባለሙያዋ ስቴላ በበኩላቸው "ግጭቱ ሊስፋፋ የሚችልበት ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው። ይህ በቀጠናው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚኖረው ጉዳይ ነው" ይላሉ።

የሱዳን ጦርነት አራተኛ ዓመቱ እየያዘ መሆኑን የሚያስረዱት ባለሙያዋ ሶማሊያም አለመረጋጋት ውስጥ መሆኗን ጨምረው ጠቅሰዋል።

ደቡብ ሱዳን በታኅሣሥ ከሚካሄደው "ወደ አንድ ወገን ያደላ ምርጫ" ጋር ተያይዞ ወደ ሌላ ግጭት ታመራለች ተብሎ እንደሚሰጋ ጨምረው ግለጸዋል።

"ስለዚህም ዓለም አቀፍ እና የቀጣናው ተዋናዮች በዚህ ግጭት ውስጥ የአስታራቂነት እና የአስማሚ ሚና መጫወት አለባቸው። በተለይም ሁሉም ወገኖች አገሪቱ አሁን ወዳለችበት ሁኔታ እንድትደርስ የየራሳቸውን ሚና እንደተጫወቱ መቀበላቸው ወሳኝ ነው።"

ይህንን ጦርነት ማስቆም የሚቻለው እንዴት ነው?

በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ ቀጣናው አገራት ሊስፋፋ ይችላል የሚለው ስጋት የበርካቶች ነው።

መስከረም 13/2019 ዓ.ም. በፌደራል መንግሥቱና በህወሓት መካከል በተጀመረው አዲስ ውጊያ የኤርትራ ጦር በቀጥታ መሳተፉን የፌደራል ከፍተኛ ባለሥልጣን እና የአፋር ክልል አስታውቋል።

የኤርትራ መንግሥት ግን ይህንን በተደጋጋሚ ሲያስተባብል ቆይቷል።

አቶ ባይሳ ግን ይህ ጦርነት ወደ ቀጣናው እንደማይስፋፋ ተስፋ አላቸው። አክለውም የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከትግራይ አልፎ የመሄድ ዕድሉ ጠባብ ነው።

"ያለኝ ብቸኛው ስጋት ኤርትራ ወደዚህ ጦርነት ልትገባ ትችላለች የሚለው ነው" የሚሉት አቶ ባይሳ "በዚህም ጦርነቱ ሊረዝም ይችላል፤ የሕዝቡም ስቃይ ሊቀጥል ይችላል። በመጨረሻ ግን ወደ ድርድር ጠረጴዛው ይመለሳሉ፤ ከዚያም 'ፕሪቶሪያ ሁለት' ይከተላል" ሲሉ ተናግረዋል።