የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያውያን ላይ የጣለውን የቪዛ ገደብ አነሳ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአውሮፓ ኅብረት ከሁለት ዓመት በፊት በኢትዮጵያውያን ላይ የጣለውን የቪዛ ገደብ ማንሳቱን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሕገ ወጥ መንገድ በአውሮፓ የሚኖሩ ዜጎቹን ለመቀበል ያሳየው ተባባሪነት አናሳ ነው በሚል በኢትዮጵያውያን ላይ የቪዛ ገደብ ተጥሎ ቆይቷል።

የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ፤ በኅብረቱ አባል አገራት ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በመለየት እና ወደ አገራቸው በመመለስ ረገድ መሻሻሎች ስለታዩ ገደቡ እንዲነሳ ተወስኗል።

በአውሮፓ አገራት በሕገ መጥ መንገድ የሚኖሩ ስደተኞችን አገሮቻቸው የማይቀበሏቸው ከሆነ ወይም አገራቱ ለመተባበር ፈቃደኛ ካልሆኑ የቪዛ እገዳን እንደ ጫና ማሳደሪያ መንገድ ይጠቀምበታል።

የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት፤ በአውሮፓ ኅብረት ሕግ ሥር ያሉና ለኢትዮጵያውያን ቪዛ ለመስጠት ይውሉ የነበሩ አሠራሮች ላይ ገደብ ማድረጉን ያስታወቀው ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ. ም. ነበር።

በአውሮፓ በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በመለየት፣ የጉዞ ሰነድ በማዘጋጀት እና ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ረገድ ያለው አሠራር መሻሻሉን ምክር ቤቱ ትናንት ማክሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2018 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለው "ሁለንተናዊ ግንኙነት መሻሻል ማሳየቱም" ተጠቅሷል።

የአውሮፓ ኅብረት ጥሎት በነበረው እግድ ምክንያት የኅብረቱ አባል አገራት ኢትዮጵያውያን በሚያቀርቧቸው ማስረጃዎች መሠረት ቪዛ ሲጠይቁ የሚያስፈልጓቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ማንሳት (waiving requirements) አይችሉም።

ኢትዮጵያውያን ከአንድ ጊዜ በላይ ወደ አውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ገብተው መውጣት የሚችሉበት ቪዛም (multiple entry) በእገዳው ተካትቶ ነበር።

የዲፕሎማት እና የመንግሥት ሠራተኞች/ባለሥልጣናት ፓስፖርት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ያለ ክፍያ ቪዛ እንዳያገኙ ተደርጎ ቆይቷል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ቪዛ ለማግኘት የሚጠብቁት ጊዜ ከ15 የሥራ ቀናት ወደ 45 የሥራ ቀናት ከፍ እንዲል ተወስኖም ነበር።

የቪዛ እገዳው በተጣለበት ወቅት የአውሮፓ ኅብረት ውሳኔውን "ዳግመኛ እንዲያጤን" ኢትዮጵያ ጠይቃ እንደነበር ይታወሳል።

ምክር ቤቱ በድረ ገጹ ትናንት ባወጣው መግለጫ "በአባል አገራቱ ግዛት በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ለመቀበል ያለው ተነሳሽነት ላይ መሻሻል ታይቷል" ብሏል።

በዚህ ምክንያትም እገዳውን በዘላቂነት ማስቀጠል አስፈላጊ እንዳልሆነ ገልጿል።