የፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል ጦርነቱ መጠናቀቁን ገልጾ የባለአደራ አስተዳደር መመሥረቱን አስታወቀ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በትግራይ ክልል ላለፉት ሦስት ሳምንታት የተካሄደው ጦርነት መጠናቀቁን ገልጾ ባለአደራ አስተዳደር መመስረቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የፌዴራል መንግሥቱ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ መሠረት መመስረቱን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ስለ አዲሱ አስተዳደር ዛሬ ዓርብ ጥቅምት 6/2019 በማኅበራዊ የትስስር ገፁ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በዚህ መሠረት የተቋቋመው የትግራይ ክልል የፊዴራል መንግሥት ባለአደራ አስተዳደር፣ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ትግራይን ያስተዳድራል ተብሏል።

ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ትግራይ በጊዜያዊ አስተዳደር ስትመራ የቆየች ሲሆን፤ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ወዲህ ደግሞ የህወሓት መሪዎች ጊዜያዊ አስተዳደሩን አስወግደው ከጦርነቱ በፊት የነበረውን አስተዳደር ወደ ሥልጣን መመለሳቸው ይታወሳል።

በዚህም ሳቢያ በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መሪዎች መካከል ለስድስት ወራት የቆየው ፍጥጫ ወደ ጦርነት ተሸጋግሮ የመከላከያ ሠራዊት እና አጋሩ የትግራይ ሰላም ኃይሎች አብዛኛውን የትግራይ አካባቢዎች ተቆጣጥረዋል።

ዛሬ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ይፋ ያደረገው ባለአደራ አስተዳደር አምስት ዋና አስፈጻሚዎች ያሉት ሲሆን፣ አቶ አሰፋ አብርሃ ሐጎስ የአስተዳደር እና የሕዝብ አገልግሎት ዋና አስፈጻሚ ሆነው ተሾመዋል።

⁠ዶክተር ቴዎድሮስ አረጋይ ወልደ ሥላሴ ደግሞ የኢኮኖሚ እና መልሶ ግንባታ ዋና አስፈጻሚ ሲሆኑ፣ ⁠ብርጋዴር ጄኔራል ገብረ እግዚአብሔር በየነ ኃይሉ የጸጥታና ሰላም ዋና አስፈጻሚ በመሆን ለስድስት ወራት እንዲያገለግሉ ሹመት ተሰጥቷቸዋል።

በተጨማሪም ⁠አቶ ረዳኢ ኃለፎም ወ/ሥላሴ የፖለቲካ እና ሕዝብ አደረጃጀት ዋና አስፈጻሚ፣ ⁠ዶክተር ሽሻይ አማረ ደግሞ የመቐለ ከተማ ከንቲባ በመሆኑ የተሾሙ ሌሎች ባለሥልጣናት ናቸው።

እነዚህ አምስት ተሿሚዎች በበላይነት የሚመሩት የክልሉ ባለአደራ አስተዳደር፣ በስድስት ወራት ውስጥ ይካሔዳል በተባለው ምርጫ መሠረት የክልሉ ቋሚ መንግሥት እስኪመሰረት ድረስ የፌዴራል መንግሥቱ መመርያ እና አቅጣጫ እየሰጣቸው ክልሉን የሚመሩ ይሆናል።

የትግራይ ባለአደራ አስተዳደር የተመሠረተው፣ የፕሪቶሪያው በዘላቂነት ግጭትን የማቆም ስምምነት ፈርሶ በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት መካከል ጦርነት ዳግም ከተቀሰቀሰ በኋላ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው።

ግጭቱ ባለፈው ወር መስከረም 13/2019 ዓ.ም ዳግም ከተቀሰቀሰ በኋላ ባሉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የፌዴራሉ መከላከያ ሠራዊት እና ከሠራዊቱ ጋር የተሰለፈው "የትግራይ ሰላም ኃይል" አብዛኛውን የትግራይ ክልል ተቆጣጥረዋል።

የህወሓት መሪዎች መቀለን ጨምሮ ከበርካታ የትግራይ ከተሞች ለቅቀው ከወጡ በኋላ ክልሉ በፌደራል መንግሥቱ ኮማንድ ፖስት ሥር እንደሚቆይ እና በትግራይ ምርጫ እንደሚካሄድ አቶ ጌታቸው ረዳ ባለፈው ሳምንት ተናግረው ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በዛሬው መግለጫው፣ ጦርነቱ "በህወሓት ሽንፈት" መጠናቀቁን አስታውቋል።

"ሰላምን ያልፈለገው የህወሓት አመራር ለአራተኛ ጊዜ የጀመረው አውዳሚ ጦርነት ለአራተኛ ጊዜ በህወሓት ሽንፈት ተጠናቋል" ሲል ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል።

ይህን ተከትሎ የተመሠረተው ባለአደራ አስተዳደር ያከናውናቸዋል ከተባሉ ዋና ዋና ተግባራት መካከል፣ በትግራይ ክልል ውስጥ ተፈጥሮ ያለውን የሰላምና የመረጋጋት ችግር በፍጥነት በመፍታት የተረጋጋ ሁኔታን መፍጠር ቀዳሚው ነው።

የፈረሱ የመንግሥት መዋቅሮችን መልሶ በመዘርጋት ሕዝቡ የመደበኛ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር፤ እንዲሁም በጦርነት ምክንያት የተጎዱ መሠረተ ልማቶችን በመጠገንና ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ኃላፊነትም ተሰጥቶታል።

ይኸው አስተዳደር በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደየቀያቸው መመለስ፤ በክልሉ ውስጥ ተቋርጠው የነበሩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ ማድረግ ይጠበቅበታል።

የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ ተፈጥሮ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ "ነጻና ግልጽ ምርጫ" ተከናውኖ ትግራይ የፌዴሬሽኑ አካል የምትሆንበትን ሁኔታ ማመቻቸትም የአስተዳደሩ ተግባር ይሆናል።

ከፌዴራል እና ከትግራይ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ከክልል እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር ውስጥ የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠር፣ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን በማስረከብ ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱና ተሐድሶ እንዲያደርጉ ሁኔታውን ማመቻቸት፣ የክልሉን የጸጥታ መዋቅር እንደ አዲስ ማዋቀር ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል ናቸው።

በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት መፍታት ያልተቻለው የትግራይ ግጭት

በትግራይ ክልል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት ለመፍታት የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት "በህወሓት ዕንቅፋትነት የተነሣ ሳይሳካ ቀርቷል" የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ብሏል።

መንግሥት የትግራይ ክልልን "የሚያጸና" ያለውን ውሳኔ የወሰነው፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕግ በተሰጠው ሥልጣን አግባብ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ውሳኔ አስተላልፎ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰጠው ሥልጣን መሠረት መሆኑ ተገልጿል።

የፕሪቶሪያው ስምምነት መፍረሱን በይፋ ያወጀው ህወሓት፣ ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ በፌደራል መንግሥቱ የተቋቋመውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን ከሥልጣን በማስወገድ የክልሉን አመራርነት ተቆጣጥሮ ነበር።

የፌዴራሉ መንግሥት በበኩሉ የፕሪቶሪያው ስምምነት መፍረሱን በይፋ ባይገልፅም፣ ዛሬ ይፋ የሆነው የባለአደራ አስተዳደር ስምምነቱ ከተግባር ውጭ መሆኑን የሚያመለክት ነው።

የፕሪቶሪያው ስምምነት አንቀፅ 10፣ በትግራይ ክልል ምርጫ እስኪደረግ ድረስ በፌዴራሉ መንግሥት እና በህወት መካከል በሚደረግ ፖለቲካዊ ንግግር ሁሉን አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚመሰረት ይደነግጋል።

ይሁን እንጂ መንግሥት ዛሬ ይፋ ያደረገውን ባለአደራ አስተዳደር የመሠረተው በአገሪቱ ሕጎች መሠረት እንደሆነ ነው የገለፀው።

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመመለስ ይልቅ፣ የፌዴራሉ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) እና የፌዴራል መንግስት በክልሎች ጣልቃ ሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው ዐዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 14/2/ለ/ መሠረት ነው ባለአደራ አስተዳደር መመስረቱን ይፋ ያደረገው።

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) ማንኛውም ክልል ይህን ሕገ መንግሥት በመጣስ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ያዛል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በክልሎች ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ የወጣው ዐዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 14 ደግሞ፣ ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታን ለማስወገድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚያሳልፈውን ውሳኔ ተከትሎ የፌዴራሉ መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎች የሚደነግግ ነው።

የአንቀጹ ንዑስ አንቀጽ 2/ለ፣ የፌዴራሉ መንግሥት የክልሉን ምክር ቤት እና የክልሉን ከፍተና የሕግ አስፈጻሚ አካል በማገድ ለፌዴራል መንግሥቱ ተጠሪ የሆነ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም የመወሰን ሥልጣን ይሰጣል።

በዚህ መሠረት የተቋቋመው የባለአደራ አስተዳደር በሚያከናውናቸው ሁሉም ተግባራት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች፣ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት፣ የትግራይ ሕዝብን መሠረታዊ ጥቅሞች መሠረት ማድረግ እንዳለበት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

አስተዳደሩ፣ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እስከሚቋቋም ድረስ የክልሉን የዕለት ተዕለት አገልግሎቶች ከማቅረብና ለቀጣይ ምርጫ አስቻይ ሁኔታዎችን ከመፍጠር በዘለለ ረዘም ያለ ስትራቴጂያዊ አንድምታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ እንቅስቃሴ እንደማይኖረውም ተገልጿል።

በተጨማሪም ባለአደራው አስተዳደር ተግባሩን ከፌዴራል መንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫ እና መመሪያ መሠረት እንደሚያከናውን የተገለፀ ሲሆን፣ የፌዴራሉ መንግሥት ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግለት ተመልክቷል።