ወደ ትግራይ የተጓዙት የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ምን አሉ?

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

እሁድ ዕለት ለሁለት ሳምንት ያህል ተቋርጦ የነበረው የመቀለ በረራ ሲጀመር የፌደራል ባለሥልጣናት እና ሌሎች የትግራይ ሰላም ኃይሎች መሪዎች ወደ ትግራይ አምርተዋል።

የቀድሞው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ዳይሬክተሩ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽነር የሆኑት ዶ/ር አብርሃም በላይ ወደ ክልሉ ካቀኑት ባለሥልጣናት መካከል ናቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብተው ሥልጣናቸውን በመልቀቅ ወደ አዲስ አበባ ካቀኑ ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በኋላ እሑድ ጥቅምት 01/2019 ዓ. ም. ወደ መቀለ ገብተዋል።

ባለሥልጣናቱ በመቀለ እና አዲግራት ነዋሪዎችን አግኝተው ማነጋገራቸውን በመግለጽ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ መልዕክታቸውን አስፍረዋል።

አቶ ጌታቸው በትግርኛ ባሰፈሩት ጽሁፍ ከ18 ወራት በኋላ ወደ መቀለ መመለሳቸውን ከአጭር ተንቀሳቃሽ ምሥል ጋር አጋርተዋል።

"ከ18 ወራት በኋላ ዛሬ ጥቅምት መጀመርያ ላይ ወደ መቀለ ተመልሰናል" ያሉት አቶ ጌታቸው መጋቢት 2017 ዓ.ም. "ተገድደን ወጥተናል" በማለት የነበረውን ሁኔታ አስታውሰዋል።

አቶ ጌታቸው አዲግራት መሄዳቸውን ከገለጹ በኋላ "ቀጣይ አድዋ፣ አክሱም፣ ሽረ፣ ማይጨው አላማጣ ይልቁኑስ በትግራይ ገጠሮች እና ከተሞች እንደርሳለን" ሲሉ የክልሉን ሕዝብ ተንቀሳቅሰው በማግኘት እንደሚያነጋግሩ ጠቁመዋል።

አቶ ጌታቸው ወደ መቀለ ከመሄዳቸው በፊት በትግርኛ ለቲቢኤስ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለምልልስ ለስድስት ወራት ያህል ትግራይ በፌዴራል ኮማንድ ፖስት ስር እንደምትቆይና ከዚያ በኋላ ክልላዊ ምርጫ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው በቃለ ምልልሳቸው እንደተናገሩት፣ የኮማንድ ፖስቱ ዋነኛ ተግባር ክልሉን ለአስተዳደር ሥራ ምቹ ማድረግ፣ ፀጥታን ማስከበር እንዲሁም መልሶ ማቋቋምና ማገገምን ማመቻቸት ነው።

እንደ አቶ ጌታቸው ማብራሪያ፣ የፌዴራል ኃይል እና አጋሮቹ እያንዳንዱን ከተማ ሲቆጣጠሩ ሰብአዊ እርዳታ የሚቀርብ ሲሆን፣ የፀጥታ ጥበቃው በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በትግራይ ሰላም ኃይል ይከናወናል።

ዶ/ር አብርሃም በላይ በበኩላቸው በይፋዊ ፌስቡክ ገጻቸው ላይ "ሰላም የተጠማው ሕዝባችን ጎበኘነው። በዘላቂነትም ከሕዝቡ ጎን ሆነን እናረጋግጥለታለን!" ሲሉ በመቀለ እና አዲግራት ስለነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

ጥቅምት 1 ቀን 2019 ዓ.ም. ከመቀለ እስከ አዲግራት ነዋሪዎችን እያነጋገሩ መሄዳቸውን የጠቀሱት ዶ/ር አብርሃም፣ "ከተሞቻችን እና አዋሳኝ ከባቢዎች ያሉበት ነባራዊ ሁኔታ ታዘብኩ፤ . . . የሕዝባችን የሰላም ናፍቆት እና ፍላጎት ጥልቀትም ለማየት ዕድል አገኘሁ" ብለዋል።

"ሕዝቤ ሰላም ናፍቋል፥ ተስፋ ሰንቋል" ያሉት የኒውክሌር ኮሚሽን ኮሚሽነሩ፣ "በእርግጠኝነት ይህን መሻቱን እንደምንፈጽም እምነቴን ይበልጥ አጽንቼ ብርታት ሰንቄአለሁ" ብለዋል።

ዶ/ር አብርሃም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ያሳየው "ሕዝባዊነት እና የዲሲፕሊን ልዕልና ወደር የሌለው" መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም "ሕዝብ ሰላም ይፈልጋል፣ ወጣት ልማትና እድገት ይሻል፣ አገር ዘላቂ ሰላም እና ሥልጣኔ ይመኛል፤ በተግባር እንተገብረዋለን!!" ሲሉ ጽሁፋቸውን አጠናቅቀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው "ሕዝባችን ወደ ቀየው እንዲመለስ፣ ትግራይ በሙሉ ሰላም እንድታጣጥም የግድ ነው፤ ይህም ይሆናል" ሲሉ መልዕክታቸውን አጠናቅቀዋል።

መስከረም 13/2019 ዓ.ም. ህወሓት በትግራይ ክልል የሚገኙ ሦስት አውሮፕላን ማረፊያዎችን በቁጥጥሩ ስር ማዋሉን ካስታወቀ በኋላ ክልሉን ከአማራ እና ከአፋር ጋር በሚያዋስኑ ሥፍራዎች ጦርነት ተቀስቅሷል።

ጦርነቱ በተጀመረ በጥቂት ቀናት የክልሉን መዲና መቀለን ለቅቆ የወጣው የህወሓት ታጣቂ በሌሎች አካባቢዎች ውጊያ ሲያደርግ ቆይቷል።

በህወሓት ኃይሎች እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት መካከል ይፋዊ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ የኤርትራ ወታደሮች ተሳታፊ መሆናቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ተናግሯል።

የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ያሉ ታጣቂዎችን በመርዳት የአገሪቱን ሰላም ለማናጋት እየጣረ መሆኑን በመግለጽ ቢከስም፣ የኤርትራ መንግሥት ግን ክሱ በአገር ውስጥ ያለውን ችግር አቅጣጫ ለማስቀየር ነው በሚል ውድቅ ያደርጋል።

የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ የትግራይ ሰላም ኃይል ወደ አዲግራት እና ሽረ ከተማ መግባታቸውን ዘግቧል።

ከኤርትራ ድንበር 35 ኪሎ ሜትር በምትርቀው አዲግራት የኤርትራ ወታደሮች ገብተው እንደነበር ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸው ነበር።

በከተማዋ በጭነት መኪኖች በመሆን ሲንቀሳቀስ የነበረ የኤርትራ ጦር ላይ የድሮን ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ምንጮችን እና ግጭትን የሚከታተል ተቋምን ጠቅሶ ኤኤፍፒ ዘግቧል።

የህወሓት ተዋጊዎች ሽረን ለቅቀው የወጡት ረቡዕ ዕለት መሆኑን የዘገበው ኤኤፍፒ በከተማው ዘረፋ ተፈጽሟል ብሏል።

በሽረ ከተማ የሚኖሩ እና የእርዳታ ሠራተኞችን ያነጋገረው የዜና ወኪሉ ለዘረፋ በተሰማሩ ሰዎች እና በነዋሪዎች መካከል በነበረው የተኩስ ልውውጥ አራት ሰዎች መገደላቸውን እና 11 መቁሰላቸውን ዘግቧል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው በመቀለ እና አዲግራት በነበራቸው ቆይታ "አዲስ መንፈስ፣ የተለየ ድባብ፣ እና የተለየ የለውጥ ንፋስ" መመልከታቸውን ተናግረዋል።

"ጥልቅ የሰላም ጥማት" ማየታቸውን በእንግሊዘኛ እና በአማርኛ ባጋሩት ጽሑፍ ላይ የገለጹት የደኅንነት ባለሥልጣኑ ይህ በመላው ትግራይ ላይ የሚታይ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም "ወሰን የሌለው የመሰማት ፍላጎት፣ እንዲሁም ለእውነተኛ መግባባት፣ ለዕርቅ እና ለተሻለ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ጥልቅ ናፍቆት አለ" ሲሉ በጉብኝታቸው ወቅት ታዘብኩ ያሉትን በጽሑፋቸው ላይ አስፍረዋል።

የመከላከያ ሠራዊትን ሥነምግባር በጽሁፋቸው ላይ ያወደሱት የደኅንነት ኃላፊው "የአዛውንቱ ስስት፣ የወጣቱ ጉጉት ብቻ ትግራይ ላይ የሆነ አዲስ መንፈስ፣ አዲስ ድባብ፣ የሚስተጋባ የተለየ ንፋስ ታዝቤያለሁ" ብለዋል።

ለዓመታት በክልሉ ታይቷል ካሉት "ከፍተኛ ስቃይ፣ መሰላቸት እና እርግጠኛ አለመሆን" በኋላ "ይህ አዲስ ተስፋ በእርግጥ እውን ሊሆን ይችል ይሆን ከሚል ስጋት ጋር የተቀላቀለ የእፎይታ ስሜት እየተፈጠረ ነው" ሲሉ አክለዋል።

የትግራይ ሕዝብ በስሙ "ከፍተኛ መከራ፣ ብዝበዛ" መፈጸሙን ጠቅሰው በዚህም የተነሳ ለረዥም ጊዜ መስዋዕትነት ሲከፍል መቆየቱን ጽፈዋል።

ሆኖም፣ ካሳለፉት ነገሮች ሁሉ አንጻር "ለሰላም፣ ለክብር፣ ለፍትህ እና ለነጻነት ያላቸው ፍላጎት አሁንም ጠንካራ ሆኖ ይቀጥላል" ሲሉም ጠቅሰዋል።

የደኅንነት ኃላፊው በዚሁ ጽሑፋቸው በመቀለ እና በአዲግራት "ለአዲስ ጅማሮ ከፍተኛ ፍላጎት" ስለመኖሩ ማስተዋላቸውን ተናግረዋል።

"እውነት፣ ፍትህ፣ እና እውነተኛ ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲሰፍን ከተደረገ የትግራይ ሕዝብ በስተመጨረሻ በነጻነት እና በክብር መኖር፣የራሱን ምርጫ ማድረግ እና የወደፊት ዕጣ ፈንታውን መወሰን ይችላል።"

አክለውም ይህ በጊዜያዊ ስሜት የመጣ ምኞት ብቻ አለመሆኑን ገልጸው "ለዓመታት በዘለቀ ስቃይ እና ለተሻለ ነገ ባለው የማይበገር ተስፋ የተቃኘ ጥልቅ ፍላጎት ነው" ብለዋል።

ይህ አዲስ ፍላጎት "መጠበቅ አለበት" ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የሕዝቡን ምኞት የሚያዳክም ወይም ዘላቂ ሰላም የመፍጠር ዕድልን የሚያጠፋ ምንም ዓይነት "የፖለቲካ ጨዋታ፣ ማታለል፣ ሰበብ ወይም ራስ ወዳድነት የተሞላበት ምኞት ሊፈቀድ አይገባም" ብለዋል።

ጨምረውም የትግራይ ሕዝብ "የሰላም ፍላጎት ሊደመጥ ይገባዋል፣ ክብራቸው ሊከበር እና ለመጪው ጊዜ ያላቸው ተስፋ እውን እንዲሆን እውነተኛ ዕድል ሊሰጠው ይገባል።"

"በሸፍጥ ይህን አዲስ ተስፋ ማጨለም ለማንም በምንም ሊፈቀድለት አይገባም" ያሉት አምባሳደር ሬድዋን በትግራይ እየተፈጠረ ነው ያሉት "አዲስ መንፈስ"፤ "መዳከም ሳይሆን መጎልበት፣ መበዝበዝ ሳይሆን መጠበቅ፣ እንዲሁም ለሁሉም ዘላቂ ሰላም፣ ነፃነት እና ክብር ወደሚሆን ነገር መለወጥ አለበት" ብለዋል።