ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ አንድ ታዳጊ ትምህርት ቤት ላይ በፈጸመው ጥቃት ተማሪዎችን እና መምህርን ገደለ
በአሜሪካ ኦሪገን ግዛት አንድ የ16 ዓመት ታዳጊ በመጀመርያ ደረጃ ትምሀርት ቤት ላይ ተኩስ ከፍቶ ሦስት ተማሪዎችን እና አንድ መምህርን ከገደለ በኋላ በአካባቢው በነበረ ግለሰብ መገደሉን ፖሊስ አስታወቀ።
ማንነቱ ያልተገለጸው ተጠርጣሪ ሐሙስ ከሰዓት ወደ ሲልቨር ሬይል የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት በማቅናት የተዘጋ በር ላይ የተኩስ እሩምታ መክፈቱን የፖሊስ አዛዡ ማይክ ክራንዝ ተናግረዋል።
በአካባቢው የነበረ ሌላ ግለሰብ የታዳጊውን ጥቃት ለማስቆም ካባረረው በኋላ ተኩሶ መግደሉን ፖሊስ ጨምሮ አስታውቋል።
የተገደሉት ሕጻናት የአምስት፣ የስምንት እና የአስራ አንድ ዓመት መሆናቸው ተገልጿል። አንድ የሰባት ዓመት ሕጻን እና የ54 ዓመት ጎልማሳ ደግሞ በጽኑ በመጎዳታቸው ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ክራንዝ ተናግረዋል።
ጥቃት አድራሹ ከትምህርት ቤቱ ጋር ስላላው ግንኙነት እስካሁን ድረስ የታወቀ ነገር የለም።
የአካባቢው አስተዳደር ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ስቲቨን ኩክ "በደረሰው አሳዛኝ ሁኔታ ደንግጠናል፤ ልባችን ተሰብሯል" ሲሉ ተናግረዋል።
"ማኅበረሰባችን ስላጋጠመው ሐዘን በበቂ ሁኔታ መግለጽ የሚችል ቃል የለም።"
ፖሊስ ጥቃት ፈጻሚው በአካባቢው የሚኖር የ16 ዓመት ልጅ እንደሆነ ቢናገርም፣ ስለ እሱ ወይም ስለ ተጎጂዎቹ ማንነት ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ይፋ አላደረገም።
ፖሊስ በትምህርት ቤቱ ላይ ጥቃት ስለመከፈቱ መረጃ ደርሶት ወደ አካባቢው ባመራበት ቅጽበት ተጠርጣሪው ወደ ትምህርት ቤቱ ጥሶ ገብቷል ተብሏል።
ፖሊስ ተጠርጣሪው ወደ ትመህርት ቤቱ ለመግባት የተዘጋውን በር ቁልፍ በጥይት መትቶ መገንጠሉን ተናግሯል።
በአካባቢው እየተንቀሳቀሰ የነበረ ሌላ ግለሰብ ታዳጊው ጥቃቱን ሲፈጽም ከተመለከተ በኋላ አባርሮ ተኩሶ እንደገደለው ፖሊስ ጨምሮ አስታውቋል።
ከሦስት ደቂቃ በኋላ ፖሊስ በስፍራው ሲደርስ አጥቂው መገደሉን ያረጋገጠ ሲሆን ትምህርት ቤቱ ላይ የደህንነት ፍተሻ አካሄዷል።
450 ተማሪዎች እና 40 ሠራተኞች ያሉት ትምህርት ቤቱ ለጊዜው መዘጋቱን ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2025 ብቻ በአሜሪካ በሚገኙ ትምሀርት ቤቶች ላይ በጦር መሣሪያ የታገዙ 235 ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን በ2026 ደግሞ 140 ተከስተዋል።