ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ህወሓት በመቀለ አየር ማረፊያ "እንቅስቃሴ እንዳይደረግ" ሲያስጠነቅቅ፣ ጌታቸው ረዳ ቡድኑ "ሲቪል አውሮፕላኖችን እንደሚመታ መናገሩን" አወገዙ
የትግራይ ክልል መንግሥትን ተቆጣጥሮ የነበረው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አስተዳደር፣ በመቀለ አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ "ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳይደረግ" አስጠነቀቀ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሆኑት ጌታቸው ረዳ፣ ህወሓት በዚህ መግለጫው "ወደ መቀለ የሚበሩ የሲቪል አውሮፕላኖችን መትቶ እንደሚጥል" መናገሩ "የተለመዱ የአሸባሪነት ታክቲኮች ለመጠቀም መወሰኑን" እንደሚያሳይ በመጥቀስ ከስሰዋል።
የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት አስተዳደር ትናንት አርብ ጥቅምት 6/2019 ዓ.ም. ያወጣው መግለጫ ሦስት የተለያዩ ማስጠንቂያዎችን ይዟል። ከማስጠንቀቂያዎቹ አንዱ ከሦስት ሳምንት በፊት ውጊያ ሲጀመር በትግራይ ኃይሎች ተይዘው ከነበሩት ሦስት የክልሉ አየር ማረፊያዎች አንዱ ከሆነው የመቀለው አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ ጋር ይያያዛል።
የትግራይ ኃይሎች የመቀለ፣ ሽረ እና አክሱም አየር ማረፊያዎችን ተቆጣጥረው የነበረ ቢሆንም፣ የፌደራል መንግሥት እና አጋሩ የሆነው የትግራይ ሠላም ኃይል የተባለው ታጣቂ ዋና ዋና ከተማዎችን መያዛቸውን ተከትሎ፣ አየር ማረፊያዎቹም ተመልሰው በመንግሥት እጅ ገብተዋል።
የትግራይ ኃይሎች አየር መንገዶችን መቆጣጠራቸው ከአፍሪካ እና አውሮፓ ኅብረት እንዲሁም ከዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ተቃውሞ ተነስቶበት ነበር።
የአሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ በፌደራል መንግሥት ሥር ከሆነ በኋላ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቋርጦት የነበረው ወደ መቀለ ከተማ የሚደረግ መደበኛ በረራ ካለፈው ሳምንት እሑድ አንስቶ በድጋሚ ጀምሯል።
የህወሓት አስተዳደር ባወጣው መግለጫ፣ የመቀለው አየር ማረፊያ "ከሲቪላዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ወጥቷል" ሲል ከስሷል። የፌደራሉ መንግሥት "በጥምረት ለኅልውና ኃይሎች የተዘጋበትን መንገድ ለማካካስ" አየር ማረፊያውን "ወታደራዊ የሰው ኃይል እና ሎጂስቲክስ ለማመላለስ እየተጠቀመበት እንዳለ ተረጋግጧል" ሲል በመግለጫው አስፍሯል።
አክሎም "ስለሆነም በአውሮፕላን ማረፊያው ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳይደረግ በጥብቅ እናሳስባለን" ሲል አስጠንቅቋል።
በተጨማሪም በክልሉ በየትኛውም እርከን የሚገኙ መዋቅሮች ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት ትግራይን እንዲያስተዳድር በፌደራል መንግሥት ከተመሠረተው ባለአደራ አስተዳደር ጋር እንዳይተባበሩ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ትናንት አርብ ይፋ ያደረገው ባለአደራ አስተዳደር የክልሉን "የዕለት ተዕለት አገልግሎቶች የማቅረብ እና ለቀጣይ ምርጫ አስቻይ ሁኔታዎችን" የማመቻቸት ኃላፊነት እንደሚኖረው ተገልጿል።
በትግራይ ክልል የተረጋጋ ሁኔታን መፍጠር፣ የፈረሱ የመንግሥት መዋቅሮችን መልሶ መዘርጋት እንዲሁም የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ወደየቀያቸው መመለስ የሚሉትም ከኃላፊነቶቹ መካከል ናቸው።
"በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እስከሚቋቋም ድረስ" የሚቆየው ይህ አስተዳደር "ከፌዴራል መንግሥት በሚሰጠው አቅጣጫ እና መመሪያ" እንደሚንቀሳቀስ እንዲሁም "ረዘም ያለ ስትራቴጂያዊ አንድምታ ባላቸው ጉዳዮች ላይ" እንደማይሠራ ተገልጿል።
ህወሓት ባወጣው መግለጫ ባለአደራ አስተዳደሩን "በትግራይ ሕዝብ ላይ የተጀመረውን የዘር ማጥፋት ፖሊሲ በባንዳዎች ተደግፎ ለማጠናቀቅ የሚያስችል" ሲል አጣጥሎታል። "በየትኛውም እርከን 'በባለአደራ አስተዳደር' ስም የሚሰጥ ማንኛውም ውሳኔ ሕጋዊነትም ሆነ ተፈጻሚነት እንደሌለው መላው ሕዝባችን ሊያውቅ ይገባል" ብሏል።
አክሎም "የወረራ መሣሪያ" ሲል ከጠራው ባለአደራ አስተዳደር ጋር በመተባበር እንቅስቃሴ የሚያደርግ ማንኛውም ተቋም፣ "እንደ ብልጽግና አካል ታይቶ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ሊታወቅ ይገባል" ሲል አስጠንቅቋል።
በህወሓት አስተዳደር የወጣው መግለጫ የትግራይ ኃይሎች ወደሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይም ገደብ ጥሏል። "የተለያዩ ቅጥረኞች እና ባንዳዎችን አነስተኛ ተሽከርካሪዎች" በመጠቀም እንዲሁም "የተለያዩ መገናኛዎችን" ይዘው "የስለላ ሥራዎችን እያካሄዱ" መሆኑን "ከተያዙ ባንዳዎች ማረጋገጥ ተችሏል" ብሏል።
ይህ ተግባር እየተከናወነ ያለው "ከከተሞች ወደ ገጠር አካባቢዎች" በሚመላለሱ ሰዎች መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፣ "ፈቃድ" የሌላቸው ግለሰቦች የትግራይ ኃይሎች ወደሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች እንዳይንቀሳቀሱ አሳስቧል።
"ማንኛውም ሰው ከትግራይ መንግሥት ሕጋዊ አስተዳደር እና ከትግራይ ሠራዊት ፈቃድ ውጪ ማንኛውንም ተሽከርካሪ ተጠቅሞ ሠራዊታችን ወደሚንቀሳቀስበት ቦታ መመላለስ እንደማይፈቀድ እናሳውቃለን" ሲል አስጠንቅቋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐበይ አሕመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት ጌታቸው ረዳ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ በህወሓት የተሰጡትን ማስጠንቀቂያዎች አውግዘዋል። ጌታቸው "የከሰመው የህወሓት አመራር የተለመዱ የአሸባሪነት ታክቲኮች ለመጠቀም መወሰኑን በይፋ አምኗል" ብለዋል።
ጌታቸው፣ የህወሓት አመራር ሊፈጽም "ከሚፈልጋቸው አሰቃቂ ወንጀሎች" መከካል በማለት የጠቀሱት በአሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ነው። "ወደ መቀለ የሚበሩ የሲቪል አውሮፕላኖችን መትተው እንደሚጥሉ እየነገሩን ነው" ሲሉ ወንጅለዋል።