ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቻይና የድንጋይ ከሰል ማውጫ ውስጥ በደረሰ ፍንዳታ ቢያንስ 90 ሰዎች ሞቱ
በሰሜናዊ ቻይና በሚገኝ የድንጋይ ከሰል ማውጫ ውስጥ በተከሰተ ፍንዳታ ቢያንስ 90 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።
የቻይና ብሔራዊ ጣቢያ እንደዘገበው 'ሊይሻንዩ ኮል ማይን' በተባለ የድንጋይ ከሰል ማውጫ አካባቢ የጋዝ ፍንዳታ ተከስቷል።
በሻንዢ ግዛት የሚገኘውን የድንጋይ ከሰል ማውጫ የሚያስተዳድረው ቶንግዡ የተባለ ኩባንያ ሲሆን፤ ፍንዳታውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በሥፍራው መድረሳቸው ተገልጿል።
የቻይና ብሔራዊ ጣቢያ ያስተላለፈው ተንቀሳቃሽ ምሥል በሥፍራው የሕክምና ባለሙያዎች እና አምቡላንሶች ተሰብስበው ያሳያል። የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች ሥራቸውን ሲያከናውኑም ታይቷል።
ፍንዳታው በተከሰተበት ወቅት በማዕድን ቁፋሮ ሥፍራ ውስጥ 247 ሠራተኞች እንደነበሩ ተዘግቧል።
የቻይና ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ሠራተኞችን በሕይወት ለማትረፍ እና የተጎዱትን ለማከም ሁሉም አካል እንዲረባረብ ጠይቀዋል።
የፍንዳታውን መንስዔ መንግሥት እንዲመረምር እና ተጠያቂነት እንዲሰፍንም አሳስበዋል።
የድንጋይ ከሰል ማውጫው አመራሮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የቻይና ብሔራዊ ጣቢያ ዘግቧል።
የጋዝ ፍንዳታው መንስዔ እስካሁን ድረስ በውል አልታወቀም።
ሆኖም ግን በማዕድን ማውጫ ሥፍራ ያለው የካርቦን ሞኖኦክሳይድ መጠን "ከልክ በላይ" መሆኑ እንደተገለጸ የአገሪቱ ብሔራዊ ጣቢያ ዘገባ ያመለክታል።
ካርቦን ሞኖኦክሳይድ ሽታ አልባ የሆነ አደገኛ ጋዝ ነው።
የቻይና የአደጋ መከላከል መሥሪያ ቤት ባወጣው መረጃ መሠረት ከስድስት የድንገተኛ ዘርፍ ሠራተኞች የተውጣጡ 345 ባለሙያዎች ወደ ሥፍራው ተልከዋል።
በአውሮፓውያኑ በ2000 መባቻ አካባቢ በቻይና ማዕድን ቁፋሮ ሥፍራዎች አደጋዎች በተደጋጋሚ ይከሰቱ ነበር።
ባለፉት ዓመታት ግን የደኅንነት እርምጃዎች በመጠናከራቸው የአደጋዎች ቁጥር ቀንሷል።
በአውሮፓውያኑ 2023 በነዳጅ ከሰል ማውጫ በደረሰ የመደርመስ አደጋ 53 ሰዎች ሞተዋል።
በ2009 ደግሞ በሂሊሎንግጂንግ ግዛት በደረሰ ፍንዳታ ከ100 በላይ ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።