አሜሪካ የኢራንን ወደቦች ለመዝጋት ስትዘጋጅ የዓለም ነዳጅ ዋጋ ዳግም አሻቀበ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረገው ውይይት ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራንን ወደቦች እንደሚዘጉ ከዛቱ በኋላ የነዳጅ ዋጋ በርሜል ከ100 ዶላር በላይ አሻቀበ።
የዓለም ነዳጅ ዋጋን የሚተምነው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በ7.3 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 102.30 ዶላር ተሸጧል።
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የተደረገው ድርድር አለመሳካቱ የዓለም የኃይል ቀውስ እየተባባሰ ሊሄድ ይችላል የሚል ስጋትን አስነስቷል።
ባለፈው ረቡዕ ዋሽንግተን እና ቴህራን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ የንግድ መተላለፊያን ለመክፈት የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ከ100 ዶላር በታች ወርዶ ነበር።
የዓለም አንድ አምስተኛ የነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ ጭነቶች የሚያልፉበት የባህር ወሽመጥ፣ ቴህራን በአሜሪካ እና በእስራኤል የተከፈተባትን ጦርነት ተከትሎ ከዘጋች በኋላ የዓለም የኢነርጂ አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ ተስተጓጉሏል።
ግጭቱ ከተጀመረበት የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በወሽመጡ የሚተላለፉ መርከቦች ቆመዋል።
ይሁን እንጂ እንደ ሕንድ እና ማሌዥያ ያሉ አንዳንድ አገሮች መርከቦቻቸው መስመሩን እንዲጠቀሙ በመደራደር ማሳለፍ ችለዋል።
የአሜሪካ እና የኢራን ድርድር በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በኩል የሚደረጉ የነዳጅ መርከብ ጉዞዎች መስተጓጎል ያስቀራል በሚል በበርካቶች ዘንድ በጉጉት ተጠብቆ እንደነበር በሲንጋፖር ናንያንግ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ኃብት ባለሙያ የሆኑት ቹዋ ዬው ህዊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የነዳጅ ዋጋ እንደጨመረ የመቀጠል ዕድሉ ከፍተኛ ነው፤ ምክንያቱም አሁን የሚጠበቀው እገዳው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆን አለመሆኑ፣ የመርከብ መስተጓጎሎች መቀጠል አለመቀጠላቸው እና የዲፕሎማሲ ጥረቱ እንደገና መጀመሩ ላይ የተመሰረተ ነው" ብለዋል።
በእስያ የሚገኙ ዋና ዋና የአክሲዮን ገበያዎች ሰኞ ዕለት ጠዋት ላይ ቀንሰው ታይተዋል።
በጃፓን የሚገኘው ኒኬይ 225 በ1 በመቶ ቀንሷል፣ የደቡብ ኮሪያው ኮስፒ ደግሞ በ0.8 በመቶ ቅናሽ አስዘመዝግቧል።
በእስያ የሚገኙ አገሮች በተለይ ከመካከለኛው ምሥራቅ በሚመጣው ነዳጅ ላይ ከፍተኛ ጥገኛ በመሆናቸው የኢራን ጦርነት ያስከተለውን መዘዝ ተከትሎ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የአሜሪካ አክሲዮንም ቅናሽ ያሳያል ተብሎ ይገመታል።
የአክሲዮን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው ባለሀብቶች አንድን ንብረት ወደፊት በተወሰነ ጊዜ በተወሰነ ዋጋ ለመግዛት ወይም ለመሸጥ በሚደረግ ስምምነት ሲሆን ይህም የዓለም የገበያ አቅጣጫን ሊያመለክት ይችላል።
ባለሀብቶች በግጭቱ ውስጥ ለተከሰቱት ለውጦች ምላሽ ሲሰጡ ባለፉት ሳምንታት በዓለም ዙሪያ ያሉ የኢነርጂ ዋጋዎች እና የፋይናንስ ገበያዎች ከፍተኛ ለውጦች አሳይተዋል።
አሜሪካ እና ኢራን ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ካደረጉ በኋላ፣ የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ እአአ ሚያዝያ 8 ቀን በበርሜል ወደ 90 ዶላር ዝቅ ብሎ ነበር።
ትራምፕ እሁድ ዕለት "ማንኛውም መርከብ ወደ ሆርሙዝ ወሽመጥ እንዳይገባ እና እንዳይወጣ ይዘጋል" ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ከጻፉ በኋላ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ዳግም ለውጥ አሳይቷል።
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በበኩሉ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ መግባት እና መውጣቶች ሰኞ ዕለት ከ11 ሰዓት ጀምሮ (14:00 GMT) እንደሚዘጋ አስታውቋል።
ሴንቴኮም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በለጠፈው ጽሑፍ "ከኢራን ወደቦች እና የባህር ዳርቻ አካባቢዎች የሚገቡ ወይም የሚወጡ የሁሉም አገራት መርከቦች ላይ ያለአድልዎ ተፈጻሚ ይሆናል" ብሏል።
ሴንኮም በተጨማሪም በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ "ከኢራን ወደቦች ውጭ የሚመጡም ሆነ የሚሄዱ መርከቦች" ማለፍ እንደሚፈቀድላቸው አስታውቋል።
ቴህራን በፓኪስታን ያደረገችውን ድርድር የመሩት የኢራን የፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሃመድ ባገር ጋሊባፍ፣ አገሪቱ "ለማንኛውም ስጋት አትንበረከክም" ሲሉ ለአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ወደ ባህረ ሰላጤው የሚጠጉ ማናቸውም የጦር መርከቦች በዋሽንግተን እና ቴህራን መካከል የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነትን እንደጣሱ እንደሚቆጠር እና "ከባድ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው" ተናግሯል።















