'ወራጅ አለ'፡ የአሜሪካዊቷ ሙዚቀኛ የኢትዮጵያ ትዝታዎች

የፎቶው ባለመብት, Peggy Bevan
የኢትዮጵያን ሙዚቃ ማጣጣም ከጀመረች ከ20 ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። አዲስ አበባ ደግሞ 11 ዓመታት ኖራለች።
ኬታ ሆስታተር ትባላለች። ቫዮሊን ተጫዋች እንዲሁም ሙዚቃ አቀናባሪ ናት።
ከሰሞኑ 'ወራጅ አለ' የተሰኘውን የመጀመሪያ አልበሟን ለቅቃለች። ለእሷነቷ ቅርብ የሆነ፣ ለዓመታት ስትማር የቆየቻቸው ነገሮች መገለጫ እና ታላቅ የጥበብ ሥራዋ እንደሆነ ትገልጻለች።
ኒው ኦርላንድስ በሚገኘው 'ዶሚኖ ሳውንድ' የተለቀቀውን አልበም እንደ "ሙሉ ዑደት" ታየዋለች።
የአልበሙ የመጀመሪያ ሙዚቃ 'ሙዚቃዊ ስሌት' ነው። አስከትሎም ትዝታ፣ ልበይ፣ ሬጌ ከሚሴ፣ ጎንደር፣ ወይዘሪት ኢትዮጵያ እና በሎሚ በና ይደመጣሉ።
አብዛኞቹ ሙዚቃዎች የኢትዮጵያ ሙዚቃ "ወርቃማ ዘመን" ተብሎ ከሚሞካሸው ወቅት የተወሰዱ ናቸው። ሙዚቃዎቹ የቀደመ ግርማ ሞገሳቸው እንዳለ ሆኖ፣ በቫዮሊን ተከሽነው አድማጭ ጆሮ ይደርሳሉ።
ኬታ አሜሪካዊት ሙዚቀኛ ናት። ለዓመታት ከኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ጋር ተጣምራ ሠርታለች።
ቫዮሊን ከመሰንቆ፣ ቫዮሊን ከክራር ጋር ተሳስረው በሙዚቃዎቿ ይደመጣሉ።
'ወራጅ አለ' አልበም ውስጥ የተካተቱት የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች የቫዮሊን ብቻ ሳይሆን ኤሌክትሮኒክ ድምጽም አላቸው። እያንዳንዳቸው የየራሳቸውን ታሪክ የሚናገሩ ይመስላሉ።
ሙዚቃዎቹን "ኢትዮጵያ ቤቴ ሳለች ባሳለፍኳቸው ዓመታት የነበረው ድባብ፣ የሰዎች ምሥሎች እና የአላፊ ቅጽበቶች ስብስብ" ስትል ትገልጻቸዋለች።
"የዚህ አልበም መለቀቅ በጣም አስደሳች ስሜት የሚሰጥ ነው" ትላለች ኬታ። "የደስታ ጣሪያ" ብላ የምትገልጸውን ስሜት እንዳላበሳት ትገልጻለች።
ሙዚቃዎቹን የኢትዮጵያ ቆይታዋ አካል ለማለት ይቻላል። በእሷ አገላለጽ "ማለት የምትፈልገውን ያስተላለፈችባቸው" ናቸው።
እሷ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ያላትን ሚና እንዲሁም ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ያበረከቱላትን አስተዋጽኦ የገለጸችበት አልበም መሆኑን ትናገራለች።
ቅጽበቶችን ጨምሮ የገጠሟት ነገሮች በአንድ ተሰንደው እንደ ማስታወሻ እንደ ምስጋናም ነው።
ይሄንን ማስተላለፍ መቻል ደግሞ "በጣም ደስ የሚል ስሜት ይሰጣል" ትላለች።
ሰዎችን አግኝታ ስለ ኢትዮጵያ ሕይወቷ ከመንገር ይልቅ አልበሙን መጋበዝ ይቀላታል።
"ሰዎች የእኔን ታሪክ የሚሰሙበት፣ በምሉዕ ለመረዳት የሚችሉበት ነው" ስትል ትገልጸዋለች።
አልበሙን ከእሷ ጋር መነጋገር እንደሚቻልበት መንገድ ትወስደዋለች። ለዚህም ነው "ለሰዎች ኢትዮጵያ ስላለው ሕይወቴ ከምነግራቸው ይልቅ አልበሙን ገዝተው ታሪኬን ይሰማሉ" የምትለው።
ወደ ኢትዮጵያ ከመሄዷ በፊት ስላለው ሕይወቷ እና ኢትዮጵያ ከኖረች በኋላ ምን ዓይነት ሰው እንደሆነች በጥበብ ዐይን ማሳየት መቻሏ ያስደስታታል።

የፎቶው ባለመብት, Ryan Simpson
'ወራጅ አለ' የሚለውን አገላለጽ የአልበሟ መጠሪያ ያደረገችው ያለ ምክንያት አይደለም።
የውጭ ዜጎች ኢትዮጵያን ሲረግጡ ከሚማሯቸው የመጀመሪያዎቹ ቃላት ወይም አገላለጾች አንዱ መሆኑ ለኬታ ትርጉም አለው።
የአዲስ አበባን ታክሲዎች ያለ 'ወራጅ አለ' ማሰብ ይከብዳል። በተለይ ደግሞ ቋንቋውን የማይችል ሰው 'ወራጅ አለ'ን አጥብቆ ከመያዝ ውጭ አማራጭ አይኖረውም።
ኬታ እንደማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ መጀመሪያ የተማረችው ሐረግ 'ወራጅ አለ' እንደነበር ታስታውሳለች።
አልበሟንም እንደ ታክሲ ጉዞ እንውሰደው።
". . .ሚኒባሱ ውስጥ አብረን ነን። እዚያ ጋር ወራጅ አለ። ከዚያ ደግሞ ወደዚህ ቦታ ልውሰዳችሁ። በሙዚቃዬ ሥዕሉን ልሣልላችሁ። ከዚያ ወራጅ አለ። በድጋሚ ሚኒባሱን ተሳፍረን ደግሞ ወራጅ አለ። ከዚያ ደግሞ ወደ ቀጣዩ ቦታ ልወስዳችሁ ነው. . ."
ኬታ በሙዚቃዎቿ አድማጮቿን እያጓጓዘች ነው።
"ትዝታ፣ ቦታ እና ጊዜ ተደባልቀው ድርብርብ የቫዮሊን ሥነ ሕንጻ ሠርተዋል" ስትል ትገልጸዋለች።
ወራጅ አለ "መጀመሪያ ላይ ከተማርኳቸው እጅግ ጠቃሚ ሐረጎች አንዱ ነው" ትላለች።
በአንድ በኩል ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ረድቷታል። በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ ትንንሽ ታሪኮችን የያዘ አድርጋ ትወስደዋለች።
"ኬታ ኢትዮጵያን እንዴት ትመለከታለች የሚለውን አንድ ላይ ለማምጣትም ተጠቅሜበታለሁ።"
'ወራጅ አለ' የሚባለው ታክሲ ውስጥ ይሁን እንጂ የአዲስ አበባን ኑሮ፣ የኢትዮጵያን ኑሮ እና መጓጓዣን የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ትናገራለች።
"መድረስ የሚፈልጉበት ቦታ ለመድረስ 'ወራጅ አለ'ን ማወቅ ግድ ነው። በውስጡም ማጋራት የምፈልጋቸውን ትንንሽ ታሪኮች ይዟል።"
በአልበሟ የኢትዮጵያ "ወርቃማ ዘመን" ሙዚቃዎችን ለማካተት የመረጠችው አንድም በብዙኃኑ ዘንድ ተወዳጅ ስለሆኑ ነው።
"ለመጀመሪያው የኢትዮጵያ አልበሜ እነዚህን ሙዚቃዎች የመረጥኩት ሆነ ብዬ ነው። የኢትዮጵያን ሙዚቃ የሰሙ ሰዎች የዚህ ታሪክ አካል እንደሆኑ እንዲሰማቸው በሚል ነው።"
ብዙዎች እነዚህን ሙዚቃዎች ያውቋቸዋል፤ አንዳች ትስስርም አላቸው። እነዚህ ለብዙዎች ስሜት ቅርብ የሆኑ ጥንታዊ ሙዚቃዎች በኬታ ዘመነኛ "ቫዮሊናዊ ዕይታ" ቀርበዋል ልንል እንችላለን።
አድማጮቿ ይሄንን ሙዚቃ አውቀዋለሁ ብለው መስማት ከጀመሩ በኋላ ረቂቅ ከሆነው የአልበሙ ቅንብር ጋር ታስተዋውቃቸዋለች።
ሙዚቃዎቿ በጣም ረቂቅ እና ሩቅ እንዳይሆኑ "የቅርብ መስኮት" የከፈተችበት መንገድ እንደሆነ ትናገራለች።
የኢትዮጵያን ሙዚቃ "እጅግ የላቀ የጥበብ ውጤት፣ እጅግ እጅግ ድንቅ" በሚል ነው የምትገልጸው።
የድምጻውያኑ ቅላጼ፣ የሙዚቃ መሣሪያዎቹ፣ የሙዚቀኞቹ ክህሎት "በጣም የተለየ" እንደሆነ ታምናለች። "ግሩም እና ማራኪ ምት" ያለው ሙዚቃም ትለዋለች።
እንደ ቫዮሊን ተጫዋች እና ሙዚቃ አቀናባሪ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ስትገልጽ "የተነባበረ፣ አንዱ ከአንዱ የተሰናሰለ ምት ያለው" ብላ ነው። ወደ ቫዮሊኗ የምትወስደውም ይሄንን እንደሆነ ታስረዳለች።

የፎቶው ባለመብት, Kenny Allen
የኢትዮጵያን ሙዚቃ ስትገልጽ ድባቡን፣ እንግዳ ተቀባይነቱን፣ ልኅቀቱን እና ለሙከራ የተመቸ መሆኑን ሳታነሳ አታልፍም።
ምናልባት የውጭ አገር ሰዎች መጀመሪያ ላይ ላይረዱት ቢችሉም ስለ ቅኝቶቹ ቁልፍ ነገሮችን ካወቁ በኋላ እንደሚዋሀዳቸው ትናገራለች።
"ማሰማት ከምፈልገው ድምጼ ጋር አብሮ የሚሄድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።"
ቫዮሊንን ከሌሎች የሙዚቃ መሣሪያዎች አብልጬ ነው የምጫወተው የምትለው ኬታ፤ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከቫዮሊን ጋር ለማዋሀድ "የመጀመሪያው መሻገሪያዬ መሰንቆ እና ድምጽ ነው" ትላለች።
ቀጣዩ መሻገሪያዋ ደግሞ ሊድ ክራር ነው። በዚህ መንገድ እየተመራች ቫዮሊንን ከኢትዮጵያ ሙዚቃ ጋር እንደምታደባልቅም ትገልጻለች።
ከኢትዮጵያ ሙዚቃ ጋር ካስተዋወቋት አንደኛው፤ በተለይ በአውሮፓውያኑ 2000 መባቻ ከጓደኞቿ ጋር 'ኢትዮጲክስ' አልበሞችን መስማቷ ነው።
ከዚያም በጓደኛዋ አማካኝነት የአገሩን ሙዚቃ ለማወቅ እየሞከረ የነበረ ኢትዮጵያዊ ተዋወቀች። "ሰዋዊ የሆነ የመጀመሪያ የኢትዮጵያ ሙዚቃ የትስስር መስመሬ" ትለዋለች።
በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ አርአያ የምትላቸው አብረዋት ባንድ ውስጥ የሚጫወቱ ሙዚቀኞችን ነው።
"የማጠናው ከእነሱ ጋር ነው። እነሱን እከተላቸዋለሁ" ትላለች።
ሙዚቀኞቹ ሰላምነሽ ዘመነ (ድምጻዊት) እንድሪስ ሐሰን (መሰንቆ ተጫዋች)፣ ምሳሌ ለገሰ (ከበሮ ተጫዋች) እና አንተነህ ተክለማርያም (ቤዝ ክራር ተጫዋች) ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Kenny Allen
ኬታ፤ አልበሟን ካደመጡ ሰዎች ባገኘችው ምላሽ ደስተኛ መሆኗን ትናገራለች።
"እስካሁን ያገኘሁትን ምላሽ 10 ከ 10 ነው የምሰጠው። በጣም ደስተኛ ነኝ። የሰሙት ሰዎች ወደውታል፤ ደስ ብሏቸዋል። ኢትዮጵያዊ ያልሆኑትም በየቀኑ እየሰማነው ነው ብለውኛል። ብዙዎች 'ልዩ አልበም ነው' ማለታቸው ደስ አሰኝቶኛል።"
አሜሪካዊቷ ሙዚቀኛ ኢትዮጵያን በትውስታ ወደኋላ መለስ ብላ ስትቃኝ ጓደኝነትን፣ ሕይወትን፣ መሳቅን ታስባለች። "የማውቃቸው ሰዎች ሁላ የሕይወቴ ትልቅ አካል ሆነዋል" ትላለች።
ለኢትዮጵያ ሕይወቷ መነሻ የሆናት ከዓመታት በፊት 'ደቦ' የተባለው ባንዷ ወደ ኢትዮጵያ መጋበዙ ነበር።
"ከባንዱ ጋር ኢትዮጵያ ስሄድ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ሰማሁ። ከዚያም በጥልቀት ማወቅ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ" ስትል ታስታውሳለች።
የ11 ዓመት ቆይታዋ ማስታወሻ 'ወራጅ አለ' ቢሆንም ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ቁርኝት ብዙ መገለጫ አለው። ለቡና ያላት ፍቅር መቼም ሳይጠቀስ አይታለፍም።
"የምወደው የኢትዮጵያ ምግብ ደግሞ ጎመን በሥጋ፣ በትኩስ ጥቁር እንጀራ፣ ከጎኑ ከብዙ ሚጥሚጣ ጋር ነው። እኔም እሠራዋለሁ።"















