
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ተሰብሰቢዎች ኢራንን ዳግም ማጥቃት ወይም የሰላም
ድርድሩን መቀጠል የሚሉ “ትልቅ ውሳኔዎችን” መጋፈጣቸውን ተናገሩ።
ማክሰኞ ዕለት በኒው ዮርክ በተጀመረው የመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔ ላይ የተገኙት የኢራን ልዑክ አንድ ብቻ ናቸው።
ትራምፕ ለጉባዔው ባደረጉት ንግግር ከኢራን ጋር የገቡበት ግጭት የማይፈታ ከሆነ እስላማዊ ሪፐብሊኳን “ሊያጠፏት” እንደሚችሉ
ዝተዋል።
ትራምፕ በመንግሥታቱ ድርጅት አዳራሽ ለተሰበሰቡት የዓለም መንግሥታት ንግግር ሲያደርጉ “የዓለም አቀፉ መንግሥታት” የሚለውን
ሃሳብ ውድቅ አድርገው በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ሰላምን ለማምጣት እንደሚያሸማግሉ እንዲሁም አሜሪካ የሰው ሠራሽ አስተውሎት
ፉክክሩን በበላይነት እንደምታጠናቅቅ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩት ከፍተኛ የአሜሪካ እና የኢራን ዲፕሎማቶች ከተወያዩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት እያካሄዱ ያሉት ትራምፕ ከጉባዔው ጎን ለጎን በርካታ የዓለም መሪዎችን አግኝተው አነጋግረዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ንግግራቸውን የጀመሩት በምጣኔ ሃብት፣ በስደተኞች፣ በድንበር እና ወንጀልን በመቆጣጠር ረገድ ያስመዘገቧቸውን
ስኬቶች በመዘርዘር ነው።
ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ባለፈው ዓመት በየካቲት ወር ከእስራኤል ጋር በመሆን የጀመሩትን እና የዓለም ነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ
ያስከተለውን የኢራን ጦርነት ትክክለኛነት ለማስረዳት ጥረዋል።
የፕሬዚዳንቱ ንግግር የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የዓለም ሕዝብ “እርስ በእርሱ የተሳሰረ” መሆኑን፤ ነገር ግን ዓለም አቀፍ መንግሥታት ልዩነታቸው እየሰፋ መሆኑን መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩትን የተቃረነ ነው።
የትራምፕ ንግግር ጦርነቱ ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ማድረግ የቻለ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
"ከኢራን ጋር፣ አገራቸውን ዳግም እንዲገነቡና ከምንጊዜውም በበለጠ ታላቅ አገር እንዲፈጥሩ የሚያስችላቸው ስምምነት
ይደረግ ይሆን?" ሲሉ የተናገሩት ትራምፕ ቀጥለውም "ወይስ ይህን የእስላማዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በፍጥነት አጥፍቼ
ሰዎችንና አገራትን እንደገና የመግደልና የማውደም ዕድል ፈጽሞ እንዳያገኙ አደርጋለሁ? ወደ ገሃነምስ እወረውራቸዋለሁ?" ሲሉ
በንግግራቸው ላይ ጥያቄ አቅርበዋል።
ትራምፕ እስካሁን ሳይሳካ የቆየው ከኢራን ጋር የሚደረገው የሰላም ድርድር ከኅዳሩ ምርጫ በኋላ ይሳካል ብለው እንደሚያምኑ
ተናግረዋል።
ይህ አስተያየታቸው ድርድሮችን ክፍት እያደረጉ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይልን በመጠቀም ማስፈራራትን የሚያካትተውን የእርሳቸውን
የውጭ ፖሊሲ ስትራቴጂ የሚያንፀባርቅ ነው።
ትራምፕ ከንግግራቸው በኋላ ለጋዜጠኞች የአሜሪካ ባለሥልጣናት
ከተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ከኢራን ልዑክ ጋር "እጅግ ውጤታማ" የሆነ ሦስት ሰዓት የፈጀ ውይይት
ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
የኢራን መገናኛ ብዙኃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ከሆኑት ስቲቨ
ዊትኮፍ ጋር መገናኘታቸውን ዘግበዋል።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ንግግሩ በአደራዳሪዋ ኳታር በኩል መደረጉን መናገራቸውን ኢርና
ዘግቧል።
ቴህራን የቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች አሜሪካ በሁሉም ግንባሮች የምታካሄደውን ጦርነት ማቆም ጨምሮ የሚጠይቅ መሆኑን የመገናኛ
ብዙኃኑ ዘግቧል።
ቢቢሲ ዊትኮፍን ስለ ስብሰባው ጠይቆ በአውራ ጣታቸውን በጥሩ ሁኔታ ሄዷል የሚል ምልክት በመስጠት መልሰዋል።
ዊትኮፍ በኋላ ላይ በኤክስ ገጻቸው ላይ ንግግሩ “ቀኑን በሙሉ በሁለቱ ወገኖች መካከል መልዕክቶችን ሲያለዋውጡ በነበሩ
አደራዳሪዎች” በኩል መካሄዱን አስታውቀዋል።
ዊትኮፍ አከለውም "ገንቢ እና ተስፋ ሰጪ ይሆናሉ ብለን ተስፋ ያደረግነውን የአንድ ዙር ውይይት በተሳካ ሁኔታ
አጠናቀናል" ሲሉ ተናግረው "አደራዳሪዎቹም ሥራቸውን ይቀጥላሉ" ብለዋል።