ቀጥታ, ትራምፕ በመንግሥታቱ ድርጅት ላይ ባደረጉት ንግግር ኢራንን “ለማጥፋት” ዛቱ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ተሰብሰቢዎች ኢራንን ዳግም ማጥቃት ወይም የሰላም ድርድሩን መቀጠል የሚሉ “ትልቅ ውሳኔዎችን” መጋፈጣቸውን ተናገሩ። ማክሰኞ ዕለት በኒው ዮርክ በተጀመረው የመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔ ላይ የተገኙት የኢራን ልዑክ አንድ ብቻ ናቸው። ትራምፕ ለጉባዔው ባደረጉት ንግግር ከኢራን ጋር የገቡበት ግጭት የማይፈታ ከሆነ እስላማዊ ሪፐብሊኳን “ሊያጠፏት” እንደሚችሉ ዝተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ከፍተኛ ባለሥልጣን በወሲባዊ ትንኮሳ ክስ ተመሰረተባቸው

    ሌተናል ጄነራል ሻድራክ ሲቢያ

    የፎቶው ባለመብት, Gallo Images via Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ሌተናል ጄነራል ሻድራክ ሲቢያ

    በደቡብ አፍሪካ ካሉት ከፍተኛ የፖሊስ መኮንኖች አንዱ ወሲባዊ ትንኮሳ በመፈጸም ተከስሰው በጆሃንስበርግ ሰሜን ምዕራብ በሚገኝ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

    ክሶቹ ሌተናል ጄኔራል ሻድራክ ሲቢያ የ16 ዓመት ልጅን ለጾታዊ ግንኙነት በማባበል እንዲሁም የ18 ዓመት ልጅን አስገድደው ደፍረዋል የሚሉ ናቸው።

    በተጨማሪም ጄነራሉ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ክስ የቀረበባቸው ሲሆን ይህም ሌሎች ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሊታሰሩ እንደሚችሉ ይጠቁማል።

    ሰኞ ዕለት የታሰሩት እና ከኃላፊነታቸው የታገዱት ምክትል የፖሊስ ኮሚሽነር ምንም አስተያየት አልሰጡም።

    የ59 ዓመቱ አዛውንት መስከረም 29 የዋስትና ጥያቄ ለማቅረብ ዳግም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    አቃቤ ሕግ ሲቢያ ከታሰሩበት እስር ቤት ለማስመለጥ የተዘጋጀ ዕቅድ መኖሩን ፍንጮች አሉ በማለት ወደ ሌላ ማረሚያ ቤት እንዲቀይሩ ጠይቋል።

    በከፍተኛ የፖሊስ መኮንኑ ላይ ክስ የተመሰረተው ፖሊስ በሙስና እና ከወንጀለኞች ጋር በመተባበር ተወንጅሎ የሕዝብ ተወካዮች ምርመራ እያካሄዱ ባለበት ወቅት ነው።

    የማድላንጋ ኮሚሽን በመባል የሚታወቀው ይህ ምርመራ ባለፉት ሳምንታት የተጀመረ ሲሆን ሲቢያ ፖሊስ ከለላ እንዲሰጥ በመስማማት '20 ኢምፓላዎች' ከተባለ የወንጀል መሪ ስጦታዎች ተቀብሏል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

    የአገሪቱ ፖሊስ ግን ክሱን ውድቅ አድርጎታል።

  2. ትራምፕ በመንግሥታቱ ድርጅት ላይ ባደረጉት ንግግር ኢራንን “ለማጥፋት” ዛቱ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ተሰብሰቢዎች ኢራንን ዳግም ማጥቃት ወይም የሰላም ድርድሩን መቀጠል የሚሉ “ትልቅ ውሳኔዎችን” መጋፈጣቸውን ተናገሩ።

    ማክሰኞ ዕለት በኒው ዮርክ በተጀመረው የመንግሥታቱ ድርጅት ጉባዔ ላይ የተገኙት የኢራን ልዑክ አንድ ብቻ ናቸው።

    ትራምፕ ለጉባዔው ባደረጉት ንግግር ከኢራን ጋር የገቡበት ግጭት የማይፈታ ከሆነ እስላማዊ ሪፐብሊኳን “ሊያጠፏት” እንደሚችሉ ዝተዋል።

    ትራምፕ በመንግሥታቱ ድርጅት አዳራሽ ለተሰበሰቡት የዓለም መንግሥታት ንግግር ሲያደርጉ “የዓለም አቀፉ መንግሥታት” የሚለውን ሃሳብ ውድቅ አድርገው በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ሰላምን ለማምጣት እንደሚያሸማግሉ እንዲሁም አሜሪካ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፉክክሩን በበላይነት እንደምታጠናቅቅ ተናግረዋል።

    ፕሬዚዳንቱ ይህንን የተናገሩት ከፍተኛ የአሜሪካ እና የኢራን ዲፕሎማቶች ከተወያዩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

    በመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት እያካሄዱ ያሉት ትራምፕ ከጉባዔው ጎን ለጎን በርካታ የዓለም መሪዎችን አግኝተው አነጋግረዋል።

    ፕሬዚዳንት ትራምፕ ንግግራቸውን የጀመሩት በምጣኔ ሃብት፣ በስደተኞች፣ በድንበር እና ወንጀልን በመቆጣጠር ረገድ ያስመዘገቧቸውን ስኬቶች በመዘርዘር ነው።

    ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው ባለፈው ዓመት በየካቲት ወር ከእስራኤል ጋር በመሆን የጀመሩትን እና የዓለም ነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ ያስከተለውን የኢራን ጦርነት ትክክለኛነት ለማስረዳት ጥረዋል።

    የፕሬዚዳንቱ ንግግር የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የዓለም ሕዝብ “እርስ በእርሱ የተሳሰረ” መሆኑን፤ ነገር ግን ዓለም አቀፍ መንግሥታት ልዩነታቸው እየሰፋ መሆኑን መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩትን የተቃረነ ነው።

    የትራምፕ ንግግር ጦርነቱ ቴህራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ማድረግ የቻለ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

    "ከኢራን ጋር፣ አገራቸውን ዳግም እንዲገነቡና ከምንጊዜውም በበለጠ ታላቅ አገር እንዲፈጥሩ የሚያስችላቸው ስምምነት ይደረግ ይሆን?" ሲሉ የተናገሩት ትራምፕ ቀጥለውም "ወይስ ይህን የእስላማዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በፍጥነት አጥፍቼ ሰዎችንና አገራትን እንደገና የመግደልና የማውደም ዕድል ፈጽሞ እንዳያገኙ አደርጋለሁ? ወደ ገሃነምስ እወረውራቸዋለሁ?" ሲሉ በንግግራቸው ላይ ጥያቄ አቅርበዋል።

    ትራምፕ እስካሁን ሳይሳካ የቆየው ከኢራን ጋር የሚደረገው የሰላም ድርድር ከኅዳሩ ምርጫ በኋላ ይሳካል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

    ይህ አስተያየታቸው ድርድሮችን ክፍት እያደረጉ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይልን በመጠቀም ማስፈራራትን የሚያካትተውን የእርሳቸውን የውጭ ፖሊሲ ስትራቴጂ የሚያንፀባርቅ ነው።

    ትራምፕ ከንግግራቸው በኋላ ለጋዜጠኞች የአሜሪካ ባለሥልጣናት ከተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ከኢራን ልዑክ ጋር "እጅግ ውጤታማ" የሆነ ሦስት ሰዓት የፈጀ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ በመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ከሆኑት ስቲቨ ዊትኮፍ ጋር መገናኘታቸውን ዘግበዋል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ ንግግሩ በአደራዳሪዋ ኳታር በኩል መደረጉን መናገራቸውን ኢርና ዘግቧል።

    ቴህራን የቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች አሜሪካ በሁሉም ግንባሮች የምታካሄደውን ጦርነት ማቆም ጨምሮ የሚጠይቅ መሆኑን የመገናኛ ብዙኃኑ ዘግቧል።

    ቢቢሲ ዊትኮፍን ስለ ስብሰባው ጠይቆ በአውራ ጣታቸውን በጥሩ ሁኔታ ሄዷል የሚል ምልክት በመስጠት መልሰዋል።

    ዊትኮፍ በኋላ ላይ በኤክስ ገጻቸው ላይ ንግግሩ “ቀኑን በሙሉ በሁለቱ ወገኖች መካከል መልዕክቶችን ሲያለዋውጡ በነበሩ አደራዳሪዎች” በኩል መካሄዱን አስታውቀዋል።

    ዊትኮፍ አከለውም "ገንቢ እና ተስፋ ሰጪ ይሆናሉ ብለን ተስፋ ያደረግነውን የአንድ ዙር ውይይት በተሳካ ሁኔታ አጠናቀናል" ሲሉ ተናግረው "አደራዳሪዎቹም ሥራቸውን ይቀጥላሉ" ብለዋል።

  3. ትራምፕ የተመድ በጀት በ15 በመቶ መቀነሱን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞቹ መሰናበታቸውን ተናገሩ

    ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር ሲያደርጉ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ መንግሥታቸው ከሌሎች በርካታ አገራት ጋር በመተባበር በመንግሥታቱ ድርጅት ታሪክ እጅግ ሰፊ የሆነ ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቁ።

    ትራምፕ ዛሬ በተጀመረው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር የድርጅቱ በጀት በዘንድሮው የአውሮፓውያኑ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ 15 በመቶ መቀነሱን እና ከ4000 በላይ ሰራተኞቹም እንደተሰናበቱ ተናግረዋል።

    ድርጅቱ "አስደናቂ አቅም" እንዳለው የጠቀሱት ፕሬዚደንቱ፣ ነገር ግን የግራ ዘመሞችን "አጀንዳ መሸከም" ማቆም አለበት ብለዋል።

    ትራምፕ በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው ትላልቅ እርምጃዎችን የወሰዱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አሜሪካን ከበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አባልነት ማስወጣት ይገኝበታል።

    የፕሬዚደንቱ እርምጃ ካረፈባቸው 66 ተቋማት መካከል ግማሽ ያህሉ ከመንግሥታቱ ድርጅት ጋር የተገናኙ ናቸው።

    በወቅቱ ዋይት ሃውስ በሰጠው መግለጫ እርምጃው የተወሰደው ተቋማቱ "ለአሜሪካ ጥቅም የሚሰሩ" ባለመሆናቸው እና "ውጤታማ ያልሆኑ ወይም ድብቅ አጀንዳዎችን ስለሚያራምዱ" እንደሆነ ገልጿል።

  4. አፍሪካ በተመድ የጸጥታ ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ዋና ጸሐፊው ጠየቁ

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አፍሪካ በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ጠየቁ።

    ዋና ፀሐፊው ይህን ያሉት ዛሬ በተጀመረው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።

    ጉቴሬዝ በንግግራቸው አፍሪካ ቢያንስ አንድ ቋሚ መቀመጫ ሊሰጣት እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

    “ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ቋሚ ውክልና አለመኖር ኢ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ ያልሆነ ነው” ሲሉ መቀየር እንዳለበት አሳስበዋል።

    ዋና ፀሐፊው ባለፈው ዓመትም “ከ1945 በኋላ ብዙ የዓለም እውነታ ተቀይሯል፤ ይሁን እንጂ የፀጥታው ምክር ቤት ስብጥር ጉልህ ለውጥ ሳያሳይ እንደቀጠለ ነው” ሲሉ ተመሳሳይ ጥሪ አቅርበው ነበር።

    የፀጥታው ምክር ቤት አራት ቋሚ አባላት ያሉት ሲሆን እነዚህም ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩሲያ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ ናቸው።

    በዚህም የአፍሪካ ክፍል በቅኝ ግዛት ሥር በነበረበት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የነበረውን እውነታ አሁንም ያንፀባርቃል በሚል ምክር ቤቱ ለረዥም ጊዜ ሲተች ቆይቷል።

    ምክር ቤቱ የተለያዩ የዓለም ቀጣናዎችን የሚወክሉ አስር ቋሚ ያልሆኑ አባላት ቢኖሩትም እንደ አምስቱ ቋሚ መቀመጫ እንዳላቸው አገራት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት የላቸውም።

    የአፍሪካ ሕብረት በምክር ቤቱ ውስጥ ሁለት ቋሚ ተወካዮች እና ተጨማሪ ሁለት ቋሚ ያልሆኑ ተወካዮች እንዲኖሩት ለረዥም ጊዜ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል።

    የፀጥታው ምክር ቤት አገራት፣ ተቋማት እና ግለሰቦች ላይ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦችን መጣል፣ የሰላም ማስከበር ስምሪቶችን መፍቀድ፣ እንዲሁም ለግጭቶች ተመድ ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት አለበት የሚለውን የመወሰን ሥልጣን አለው።

  5. ሳዑዲ በየመን በፈፀመችው ጥቃት ከ20 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው እና መቁሰላቸው ተገለጸ

    መሣሪያ ይዞ ጀልባ ላይ የተቀመጠ የሁቲ ታጣቂ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የምስሉ መግለጫ, ከቅርብ ቀናት ወዲህ ሁቲዎች ሳዑዲ በየመን በርካታ የአየር ድብደባዎችን ፈጽማለች ሲሉ ይከስሳሉ

    ሳዑዲ አረቢያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በየመን በፈፀመችው ጥቃት ከ20 በላይ ሰላማዊ ሰዎች እንደተገደሉ እና ጉዳት እንደደረሰባቸው የየመን ሁቲዎች እና ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ያለው ሚዲያ አስታወቁ።

    የሁቲ ጦር ቃል አቀባይ ሳዑዲ አረቢያ ግጭቱ ከተባባሰ ወዲህ ከ900 በላይ የአየር እና የሚሳዔል ጥቃቶችን በይዞታቸው ላይ መፈፀሟን ተናግረዋል።

    በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ እውቅና ያለው የየመን መንግሥት በበኩሉ ቡድኑ ለተፈፀመበት ጥቃት አፀፋ ለመስጠት በላህጂ ግዛት በገበያ ሥፍራ ላይ በፈፀመው ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች ተጎድተዋል ሲል ከስሷል።

    ሁቲዎች ግን የሳዑዲ ጥቃት የየመን ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረገ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ የሚፈፀመው ጥቃት መባባሱን ገልጸዋል።

    ታጣቂ ቡድኑን የምትደግፈው ኢራንም ሳዑዲ አረቢያ በሁቲ ግዛቶች ላይ የምትፈፅማቸውን ጥቃቶች እንድትታቆም አሳስባለች።

  6. አሜሪካ ከኢራን ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተናገሩ

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በኒው ዮርክ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ።

    ሩቢዮ "አሁን ላይ ምንም ነገር የታቀደ አይመስለኝም ፤ ነገር ግን ለእንዲህ ዓይነት ውይይት በእርግጠኝነት ዝግጁ ነን። በተለይ ተገናኝቶ መነጋገሩ አዎንታዊ ውጤት ካመጣ እና በመጨረሻም ዋናውን ዓላማ የማሳካት ተስፋ ካለ” ብለዋል።

    ሚኒስትሩ ዋና ዓላማ ሲሉ የገለጹት ኢራን የኒውክሌር የጦር መሣሪያ መታጠቅ እንዳትችል ማረድግን ነው።

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ ሰኞ ዕለት ጀመርው በኒው ዮርክ የሚገኙ ሲሆን ማስዑድ ፔዝሽኪያንም ለጠቅላላ ጉባኤው ወደ ኒውዮርክ ተጉዘዋል።

    ከሁለት ቀናት በፊት ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራኑ ፕሬዚደንት ማስዑድ ፔዝሽኪያን ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውን ለፎክስ ኒውስ ተናግረው ነበር።

    ጠቅላላ ጉባኤው ዛሬ የተጀመረ ሲሆን የኢራን ተወካዮች ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

  7. በቱርክ በትምህርት ቤት አቅራቢያ በተፈፀመ ጥቃት 11 ሰዎች ተጎዱ

    ክስተቱ ያጋጠመበት አካባቢ የቆመ የፖሊስ መኪና

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በቱርክ በትምህርት ቤት አቅራቢያ በተከፈተ ተኩስ 11 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ።

    ማክሰኞ ጠዋት ላይ አንድ መሣሪያ የታጠቀ ግለሰብ በከፈተው ተኩስ ከተጎዱት መካከል ሁለቱ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው ተገልጿል።

    ጥቃቱ የተፈፀመው በምዕራባዊ ማኒሳ ግዛት በሚገኝ ኢንሲ ኡዝሜዝ በተባለ የሙያ እና የቴክኒክ ትምህርት ቤት አቅራቢያ ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸው ሁሉም ተማሪዎች ናቸው ተብሏል።

    ጥቃቱን በመፈፀም የተጠረጠረው የ15 ዓመት ታዳጊ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ፖሊስ ገልጿል።

    ተጠርጣሪው የጦር መሣሪያ ይዞ ጭር ባለ መንገድ ወደ ትምህርት ቤቱ ሲራመድ እና ተመልሶ በሩጫ ሲያመልጥ ከደኅንነት ካሜራ የተገኙ ተንቃሰቃሽ ምሥሎች አሳተይዋል።

    የተጠርጣሪው እናት፣ አባት እና የመሣሪያው ባለቤት እንደሆኑ የተገለፁት አያትም ከክስተቱ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአገሪቷ የፍትሕ ሚኒስትር አኪን ጉርሌክ ተናግረዋል።

    የጥቃቱ ዓላማ ምን እንደሆነ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

    የአገሪቷ የትምህርት ሚኒስቴር “ክስተቱ አገራችንን በተለይም የትምህርት ማኅበረሰቡን እጅግ ያሳዘነ ነው” ብሏል።

    ሚኒስቴሩ ጨምሮም ሦስት ብሔራዊ መርማሪዎች ወደ ማኒሳ ግዛት መላካቸውን ገልጿል።

    በቱርክ በዚህ ዓመት ብቻ በትምህርት ቤት ላይ ጥቃት ሲፈፀም ይህ ሦስተኛው ነው።

    የአሁኑ ጥቃት የተፈፀመው መንግሥት እየጨመረ የመጣውን መሰል ጥቃት ለማስቆም እየታገለ ባለበት ወቅት ነው።

  8. የአሜሪካ ዋነኛ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለትራምፕ እንቅስቃሴ ሽፋን መስጠታቸውን አቋረጡ

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሲኤንኤን፣ ፖለቲኮ እና ኤምኤስ ናው መገናኛ ብዙኃን ዋይት ሐውስ ገብተው እንዳይዘግቡ የጣሉትን ዕገዳ በመቃወም ዋነኛ የአሜሪካ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለፕሬዝዳንቱ የሚሰጡትን ሽፋን አቋረጡ።

    ትራምፕ አርብ ዕለት እገዳውን ሲያሳውቁ፣ መገናኛ ብዙኃኑ ስለ አስተዳደራቸው “የፈጠራ ወይም የውሸት” ዘገባዎችን እያቀረቡ ነው ሲሉ ከስሰዋል። የዜና ተቋማቱ በበኩላቸው፣ ዘጋቢዎቻቸው ቅዳሜ ዕለት ወደ ዋይት ሐውስ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ገልጸዋል።

    ሦስቱ የአሜሪካ የዜና ተቋማት በመቀጠል፣ “መንግሥት ፕሬሱ ምን እንደሚዘግብ አይወስንም የሚለውን መርኅ ለማስከበር” በትራምፕ አስተዳደር ላይ ክስ እንደሚመሠርቱ አስታውቀዋል።

    ዋነኞቹ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለትራምፕ ሽፋን ላለመስጠት መወሰናቸውን ተከትሎ የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት “ትራምፕ ቲቪ” የተባለ የራሱን በኢንተርኔት የሚተላለፍ ቻናል ጀምሯል፤ ይህም ስለ ፕሬዝዳንቱ ያለማቋረጥ ለ24 ሰዓታት ቪዲዮዎችን የሚያስተላልፍ ነው።

    ሌሎችም በርካታ የአሜሪካ የዜና ተቋማት በጋራ በሚደረጉ የፕሬዝዳንቱ ዘገባዎች ላይ እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል። ከእነዚህ መካከል ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ እና ዘ ዋሽንግተን ፖስት ከትራምፕ ዝግጅቶች የሚገኙ ፎቶዎችን እንደማያጋሩ አሳውቀዋል።

    በዚህ ምክንያት ትራምፕ በፕሬዝዳንታዊ አውሮፕላናቸው ሲሳፈሩ ወይም በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ለመሳተፍ ኒው ዮርክ ሲደርሱ የሚያሳይ ምንም ቪዲዮ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች አልቀረበም።

    ትራምፕ በዋይት ሐውስ ደቡባዊ መስክ ላይ በተገነባው አዲስ ሄሊኮፕተር ማረፊያ ምረቃ ላይ የተገኙ ሲሆን፣ ዝግጅቱ በአዲሱ የዋይት ሐውስ ድረ-ገጽ ላይ በቀጥታ ተላልፏል፣ ሆኖም የፕሬዝዳንቱ ንግግር በግልጽ አልተሰማም።

  9. የግንባታ ሠራተኞች በቆረጡት ኬብል ምክንያት በአሜሪካ ውስጥ በረራዎች ተስተጓጎሉ

    አውሮፕላኖች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በአሜሪካ ውስጥ የግንባታ ሠራተኞች ለአየር ትራፊክ ቁጥጥር አስፈላጊ የሆነ ኬብል በስህተት በመቁረጣቸው በአገሪቱ በሚገኙ ዋና ዋና አየር ማረፊያዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ በረራዎች እንዲዘገዩ ምክንያት ሆነ።

    በዚህም የተነሳ ሰኞ ከሰዓት በኋላ በኒው ዮርክ፣ ፔንስልቬኒያ፣ ኒው ጀርሲ እና ማሳቹሴትስ በሚገኙ አየር ማረፊያዎች ውስጥ የሚካሄዱ በረራዎች ዘግይተዋል።

    የአሜሪካ ትራንስፖርት ሚኒስትር ሴን ዳፊ ኬብሉ መጠገኑን እና አየር ማረፊያዎቹ ወደ መደበኛ ሥራቸውን እንደሚመለሱ የገለጹ ቢሆንም፣ አሁንም መዘግየቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

    ይህ በአሜሪካ ምሥራቃዊ ክፍል የተፈጠረው ከፍተኛ የበረራ መስተጓጎል ዛሬ ማክሰኞ በኒው ዮርክ ከሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ አስቀድሞ የተፈጠረ ሲሆን፣ ለጉባኤው በርካታ የዓለም መሪዎች በከተማዋ አካባቢ ወዳሉ አየር ማረፊያዎች ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የአሜሪካ የትራንስፖርት ባለሥልጣናት እንዳሉት፣ የተቆረጠረው ኬብል የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓትን ጎድቶታል። ይህ ሥርዓት አውሮፕላኖችን በሚነሱበት እና በሚያርፉበት ጊዜ ደኅንነታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ለመምራት ይጠቅማል።

    የኒው ጀርሲ የሕዝብ ማመላለሻ ተቋም የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ እንደገለጸው፣ በቁፋሮ ቦታው የነበሩ ምልክቶች በተሳሳተ ሁኔታ ተቀምጠው ስለነበረ የግንባታ ሠራተኞቹ መስመሩን በስህተት ቆርጠውታል።

  10. ዩኬ ለሳዑዲ አረቢያ “ወታደራዊ ድጋፍ” እንደምትሰጥ አስታወቀች

    የዩኬ አውሮፕላን

    የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር አንዲ ቡርንሀም አገራቸው ለሳዑዲ አረቢያ ወታደራዊ ድጋፍ እንደምትሰጥ አስታወቁ።

    በኢራን በሚደገፉት የሁቲ አማጽያን ጥቃት የተሰነዘረባትን ሳዑዲ ለመርዳት በበረራ ላይ ላሉ አውሮፕላኖች ነዳጅ የመሙላት አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

    ወታደራዊ ድጋፉ በቀጣይ ቀናት እንደሚጀመር ተገልጿል። በቆጵሮስ በሚገኘው ራፍ የዩኬ የጦር ሰፈር የሚገኝ አንድ የእንግሊዝ አውሮፕላን በወታደራዊ ድጋፉ እንደሚካተትም ተመልክቷል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ሳዑዲ አረቢያ ወታደራዊ ድጋፍ እንዲደረግላት ጠይቃለች። ከመከላከያ ሚኒስትሩ ዌስ ስተርሊንግ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኤድ ሚሊባንድ በተሰጣቸው ምክር መሠረት ጥያቄውን ለመቀበል መወሰናቸውን ተናግረዋል።

    ወታደራዊ ድጋፉ “ለሳምንታት” ሊዘልቅ እንደሚችል ተገልጿል።

  11. ኢራን ሁቲዎችን “ማስታጠቅ እና መደገፍ” እንድታቆም የቡድን ሰባት አገራት አሳሰቡ

    ሁቲዎች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ኢራን ሁቲዎችን “ማስታጠቅ እና መደገፍ” ማቆም አለባት ሲሉ የቡድን ሰባት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ ባወጡት መግለጫ አሳሰቡ።

    በየመን ሁቲ ታጣቂዎች በሳዑዲ አረቢያ ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን “እጅግ እናወግዛለን” ሲሉም በመግለጫው አቋማቸውን አስታውቀዋል።

    በየመን በሳዑዲ ከሚደገፉ የመንግሥት ኃይሎች ጋር በቅርቡ እየተባባሰ የመጣው ውጊያ ለቀጣናው እንዲሁም ለዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦት ዘርፍም አስጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

    በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች በቀይ ባሕር አቅራቢያ ግዛቶችን መያዛቸውን ተከትሎ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ከየመን ሸሽተው ወጥተዋል።

    የቡድን ሰባት አገራት መግለጫውን ያወጡት በኒው ዮርክ ከሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ አስቀድሞ ነው። በጉባዔው የኢራን ተወካዮች ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

    የዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ጃፓን እና አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጋራ ባወጡት መግለጫ “ሁቲዎች በአፋጣኝ ሁሉንም ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ እንጠይቃለን” ብለዋል።

    “የመርከብ ጉዞዎች ላይ የሚደርስ ጥቃት እና ዛቻ እንዲገታ እና ወደ ፖለቲካዊ የንግግር ሒደት መመለስ እንዲቻል” ሲሉም አሳስበዋል።

  12. ቱርክ፣ ኢራቅ እና ጆርጂያ የኢራን አየር መንገዶች በግዛታቸው በረራ እንዳያካሂዱ አገዱ

    የኢራን አውሮፕላን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በቀጣይ ቀናት ውስጥ ሁሉም የኢራን አየር መንገዶች ዓለም አቀፍ በረራ ማከናወን እንደማይችሉ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሳንት መግለጻቸውን ተከትሎ ቱርክ፣ ኢራቅ እና ጆርጂያ የኢራን አየር መንገዶች ወደ ግዛታቸው እንዳይገቡ አግደዋል።

    የኢራኑ ማህን ኤር አየር መንገድ እንዳለው ወደ ቱርክ በረራ እንዳያካሂድ ታግዷል።

    ኤኤፍፒ ያነጋገራቸው ሁለት ምንጮች ኢራቅ የኢራን አየር መንገዶችን በረራ መሰረዟን አስታውቀዋል። ጆርጂያም ተመሳሳይ እርምጃ ወስዳለች።

    ከሁለት ሳምንት በፊት የአሜሪካ ግምጃ ቤት 27 የኢራን አየር መንገዶች ላይ ማዕቀብ ጥሏል።

    የአሜሪካ መንግሥት ኢራን ላይ የምጣኔ ሃብት ጫና ለማሳደር ባንኮች፣ የንግድ ተቋማት፣ የቴክኖሎጂ እና በረራ ዘርፎች ላይ ማዕቀብ እንደሚጥል ከሳምንታትበፊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሳንት በኢራን አየር መንገዶች ላይ የተጣለው ዓለም አቀፍ እገዳ በቀጣይ ሁለት ቀናት እንደሚተገበር ለሲኤንቢኢ ተናግረዋል።

    የኢራን አየር መንገዶች በመላው ዓለም ማንኛውንም ዓይነት እንቅስቃሴ ለማድረግ እንደማይችሉ አስታውቀዋል።

    የኢራን ንብረት የሆኑ አውሮፕላኖች “በአየር መንገዳችሁ ቢያርፉ ነዳጅ መስጠት አትችሉም፤ የአየር መንገድ አገልግሎት ልትሰጧቸውም አትችሉም፤ ትኬት መሸጥም ክልክል ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ይህንን የሚጥሱ አገራት “ከዶላር ግብይት ሥርዓት ውጪ እንደሚደረጉም” አስታውቀዋል።

    የኢራን አየር መንገዶች በአሜሪካ በተጣለባቸው እገዳ ምክንያት ለዓመታት ሲፈተኑ ቆይተዋል። አውሮፕላኖች እንዲሁም መለዋወጫዎች የመግዛት እና ጥገና የማድረግ አቅማቸው ተገድቧል።

    ባለፉት ጥቂት ወራት ወደ ኢራን የሚደረጉ የውጭ አገራት በረራዎች ተሰርዘዋል።

    ከኢራን ጋር የሚደረገው ውጊያ እስከመቼ እንደሚቀጥል እንደማያውቁ የተናገሩት የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ፤ ማዕቀቡን በተመለከተ ከቻይና ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።

    የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንግፒንግ ከአንድ ቀን በኋላ ወደ አሜሪካ ተጉዘው በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ይመክራሉ።

    የሁለቱ አገራት መሪዎች ኢራን ላይ ስለተጣለው ማዕቀብ እንዲወያዩ ለማመቻቸት የቻይና ምክትል ፕሬዝዳንት ዋንግ ይ እና የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሳንት እንደሚነጋገሩ ተገልጿል።

  13. በጃፓን በተከሰተ አውሎ ንፋስ ምክንያት 2 ሚሊዮን ሰዎች ከአካባቢያቸው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተሰጠ

    በጃፓን የተከሰተው አውሎ ንፋስ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በጃፓን በተከሰተ ከባድ አውሎ ንፋስ ምክንያት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከሚኖሩበት አካባቢ ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተላለፈ።

    ዱጁዋን የተባለው ዝናብ የቀላቀለው ከባድ አውሎ ንፋስ በተለያዩ የጃፓን ግዛቶች ጉዳት እንደሚያስከትል ተገልጿል።

    የጃፓን የሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ከባዱ አውሎ ንፋስ “ሕይወትን አደጋ ላይ እንደሚጥል” አስታውቋል። በተለያዩ አካባቢዎች የተሰጠው ማስጠንቀቂያ እየለዘበ ቢመጣም በኦሺማ ከተማ አውሎ ንፋሱ ለሰዎች ሕይወት አስጊ ነው ተብሏል።

    ከፍተኛ መጠን ያለው ንፋስ በመነሳቱ ከ50,000 በላይ ሰዎች መብራት ተቋርጦባቸዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ በረራዎች እና የባቡር ጉዞዎችም ተሰርዘዋል።

    በጃፓን የተከሰተው አውሎ ንፋስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አውሎ ንፋሱ በከፍተኛ ኤል ኒኖ ምክንያት እንደተነሳ እና የንፋሱ ፍጥነት በሰዓት እስከ 130 ኪሎሜትር እንደሚደርስ ተገልጿል።

    ከፍተኛ ዝናብ እንዲሁም የመሬት መንሸራተት እንደሚከሰት ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥተዋል።

    ዱጁዋን በጃፓን ዘንድሮ የተከሰተ 25ኛው አውሎ ንፋስ ነው። በርካታ መሰናዶዎች እንዲሰረዙም ምክንያት ሆኗል።

  14. አሜሪካ አደንዛዥ ዕፅ ጭነዋል ባለቻቸው ጀልባዎች ላይ ያደረሰችው ጥቃት ሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን ተመድ ገለጸ

    አሜሪካ ጀልባዎች ላይ ያደረሰችው ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ አደንዛዥ ዕፅ ጭነዋል ባለቻቸው ጀልባዎች ላይ ያደረሰችው የአየር ጥቃት ዓለም አቀፍ ሕግን እንደሚጥስ እና ሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ተደርጎ እንደሚቆጠር የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ።

    የተመድ ልዩ ልዑክ ቤን ሳውል ያዘጋጁት ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ ካለፈው ዓመት መስከረም ጀምሮ በካሪቢያን እና በፓስፊክ ውቅያኖስ አሜሪካ ቢያንስ 68 ጥቃቶች ፈጽማለች።

    አሜሪካ ከግዛቷ ውጭ በሆኑት አካባቢዎች ባደረሰችው ጥቃት ከ220 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

    የተመድ ባለሙያ እንደተናገሩት፤ ዒላማ የተደረጉት ሰዎች የአሸባሪ ቡድን አባላት ናቸው በሚል የተለዩ ቢሆንም እንኳን በአሜሪካ ላይ ጥቃት አልፈጸሙም። ስለዚህም አሜሪካ በዓለም አቀፍ ሕግ ሥር ራሷን የመከላከል መብቷን መተግበር አትችልም።

    ከሁለት ቀናት በፊት የአሜሪካ ጦር በካሪቢያን በሚጓዝ ጀልባ ላይ ባደረሰው ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል።

    በቀጣናው የአሜሪካን ኃይሎች የሚመራው ሳውዝኮም “ጀልባዎቹ አደንዛዥ ዕፅ እያዘዋወሩ እንደነበር የተረጋገጠ የደኅንነት መረጃ ይጠቁማል” ብሏል።

    የተመድ የሰብአዊ መብቶች ካውንስል በበኩሉ “እንዲህ ያሉ ጥቃቶች ከሕግ ውጭ ከሚፈጸሙ ግድያዎች ጋር ይስተካከላሉ” ብሏል።

    “በዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት፣ በዓለም አቀፍ ራስን የመከላከል መብት፣ በዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ፣ በፀረ አደንዛዥ ዕፅ ድንጋጌ እና በዓለም አቀፍ ፀረ ሽብር ሕግ ተቀባይነት ስለሌላቸው በሕይወት የመኖር መብትን ይጋፋሉ” ሲልም አክሏል።

    አሜሪካ ባደረሰቻቸው 68 ጥቃቶች 223 ሰዎች መገደላቸው “በዓለም አቀፍ ሕግ ሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል” እንደሆነ የተመድ ሪፖርት ይጠቁማል።

    ቢቢሲ ከዋይት ሀውስ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ጠይቋል።

  15. በሁሉም የኢራን አየር መንገዶች ላይ የተጣለው ማዕቀብ ከነገ ጀምሮ እንደሚተገበር ተገለጸ

    ስኮት ቤሳንት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሳንት ከነገ ጀምሮ “ሁሉም የኢራን አየር መንገዶች በረራ ማከናወን አይችሉም” ሲሉ አስታወቁ።

    ከሁለት ሳምንት በፊት የአሜሪካ ግምጃ ቤት 27 የኢራን አየር መንገዶች ላይ ማዕቀብ መጣሉ ይታወሳል።

    ከኢራን ጋር የሚደረገው ውጊያ እስከመቼ እንደሚቀጥል እንደማያውቁ የተናገሩት ኃላፊው፤ ማዕቀቡን በተመለከተ ከቻይና ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል።

    የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንግፒንግ ከሁለት ቀናት በኋላ ወደ አሜሪካ ተጉዘው በተለያዩ ጉዳዮች ዙርያ ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ይመክራሉ።

    የሁለቱ አገራት መሪዎች ኢራን ላይ ስለተጣለው ማዕቀብ እንዲወያዩ ለማመቻቸት የቻይና ምክትል ፕሬዝዳንት ዋንግ ይ እና የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሳንት እንደሚነጋገሩ ተገልጿል።

    የአሜሪካ መንግሥት ኢራን ላይ የምጣኔ ሃብት ጫና ለማሳደር ባንኮች፣ የንግድ ተቋማት፣ የቴክኖሎጂ እና በረራ ዘርፎች ላይ ማዕቀብ እንደሚጥል ከሳምንታት በፊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

    የኢራን አየር መንገድ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

  16. ትራምፕ ወደ ዋይት ሀውስ እንዳይገቡ ያገዷቸው መገናኛ ብዙኃን ክስ ሊመሠርቱ ነው

    ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሀውስ እንዳይገቡ ያገዷቸው መገናኛ ብዙኃን ክስ እንደሚመሠርቱ አስታወቁ።

    ሲኤንኤን፣ ፖለቲኮ እና ኤምኤስ ናው ወደ ዋይት ሀውስ እንዳይገቡ በፕሬዝዳንቱ የታገዱት ባለፈው ሳምንት አርብ ነበር።

    ትራምፕ መገናኛ ብዙኃኑ ስለ አስተዳደራቸው “የፈጠራ እና ሐሰተኛ” መረጃ አውጥተዋል ሲሉ ወንጅለዋል።

    ቅዳሜ ዕለት ጋዜጠኞች ወደ ዋይት ሀውስ ለመግባት ሲሞክሩ እንዳልተፈቀደላቸው እና የይለፍ ካርዳቸውን እንደተነጠቁ መገናኛ ብዙኃኑ ገልጸዋል።

    ሦስቱ መገናኛ ብዙኃን ዛሬ በጋራ ባወጡት መግለጫ “የመጀመሪያው አንቀጽ የሚሰጠንን መብት ለማግኘት እና ይህ መንግሥት ጋዜጠኞች ምን እንደሚዘግቡ እንደማይወስን ለማሳየት ክስ እንከፍታለን” ብለዋል።

    የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የመጀመሪያ አንቀጽ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃንን ነጻነት እንዳያፍን ያግዳል።

    መገናኛ ብዙኃን በዘገባቸው ምክንያት መድልዎ እንዳይደርስባቸውም ከለላ ይሰጣል።

    መገናኛ ብዙኃኑ ባወጡት መግለጫ “ያለ ማስጠንቀቂያ ወይም ሒደቱን ሳይከተል ዋይት ሀውስ የጋዜጠኞቻችን ፈቃድ ሰርዟል” ብለዋል።

    አክለውም “ዝም ከተባለ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነት እና ሕዝብ ነጻ መረጃ የማግኘት መብቱ በመንግሥት ይጣሳል” ብለዋል።

    ቢቢሲ ከዋይት ሀውስ ምላሽ ጠይቋል።

  17. በምዕራብ ወለጋ በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ አሽከርካሪዎች መለቀቃቸውን ማኅበሩ ገለፀ

    በጥቃቱ የወደሙ የነዳጅ መጫኛ ከባድ ተሽከርካሪዎች በከፊል
    የምስሉ መግለጫ, በጥቃቱ የወደሙ የነዳጅ መጫኛ ከባድ ተሽከርካሪዎች በከፊል

    በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጊምቢ ከተማ አቅራቢያ በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች መለቀቃቸውን ማኅበሩ ለቢቢሲ ገለፀ።

    የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ዘውዱ፣ እሑድ ጳጉሜ 1/2018 ዓ.ም. በተፈፀመው ጥቃት የታገቱ አሽከርካሪዎች መለቀቃቸውን ስለማረጋገጠቻው ተናግረዋል። የተለቀቁት የማኅበሩ አባላት የነበሩት የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ዘጠኝ መሆናቸውን አቶ ሰለሞን ገልፀዋል።

    የማኅበሩን አባላት ጨምሮ በወቅቱ የታገቱት አጠቃላይ ታጋቾች ቁጥር ከ13 እስከ 14 እንደሚደርስ አስታውሰው ሁሉም ስለመለቀቃቸው መረጃ የደረሳቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

    ታጋቾቹ እንዴት ሊለቀቁ እንደቻሉ ወይም ለታጣቂዎች ገንዘብ ተከፍሎ እንደሆነ የጠየቅናቸው አቶ ሰለሞን፣ ስለዚህ ጉዳይ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

    ታጣቂዎች ከሁለት ሳምንት በፊት ፈፀሙት በተባለው የምዕራብ ወለጋው ጥቃት ከዘጠኝ ያላነሱ ነዳጅ ጫኝ ከባድ ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መቃጠላቸውን ቢቢሲ ከምንጮች እና ከሳተላይት ምሥል አረጋግጧል።

    ታጣቂዎቹ መኪኖቹን በተኩስ አስቁመው አሽከርካሪዎቹን አፍነው እንደወሰዷቸው እና ተሽከርካሪዎቹን በእሳት እንዳቀጣጠሉ ምንጮቻችን ገልፀዋል።

    የታገቱት አሽከርካሪዎች ከሁለት ሳምንታት ያህል እገታ በኋላ ከሦስት ቀናት በፊት ዓርብ መስከረም 8/2019 ዓ.ም መለቀቃቸውን ነው የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማኅበርፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ዘውዱ የተናገሩት።

    አካባቢው “የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እንዲሁም በይፋ የሚታወቅ ስም የሌላቸው በቡድን የተደራጁ ታጣቂዎች” የሚንቀሳቀሱበት እንደሆነ አንድ የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣን የገለፁ ሲሆን፣ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ አካል ግን የለም።

  18. የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የትግራይ ቴሌቪዥንን ማገዱን አስታወቀ

    የትግራይ ቴሌቪዥን

    የፎቶው ባለመብት, TIGRAY TV

    የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የትግራይ ቴሌቪዥን “የአገርን እና የሕዝብን ደኅንነት”፣ “ብሔራዊ ጥቅምን አደጋ ላይ የሚጥሉ”፣ “ወደ ግጭት የሚገፋፉ” እንዲሁም “ጽንፈኝነትን የሚያበረታቱ መልዕክቶች” እያስተላለፈ መሆኑን በመግለጽ ማገዱን አስታወቀ።

    ባለሥልጣኑ ሰኞ መስከረም 11/2019 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከዚህ በፊት የቴሌቪዥን ጣቢያው ታግዶ እንደነበር አስታውሶ፣ ህወሓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የተፈራረመውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ እገዳው ተነስቶለት እንደነበር ገልጿል።

    የትግራይ ቴሌቪዥን ላይ የተጣለው እገዳ ላልተወሰነ ጊዜ መሆኑን ጨምሮ አስታውቋል።

    ባለሥልጣኑ አክሎም የትግራይ ቴሌቪዥንን እንደ መረጃ ምንጭ መጠቀምም ሆነ የሚያሰራጫቸውን ዘገባዎች ማሰራጨት "በጥብቅ የተከለከለ" መሆኑን ጨምሮ ገልጿል።

    ህወሓት እና ሌሎች በአገሪቱ ስድስት ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በዕሁድ ዕለት “ትብብር ለኅልውና” የሚል ጥምረት መመሥረታቸው ይታወሳል።

    የትብብሩ ምሥረታን በሚመለከት ሰብሳቢው ዘመነ ካሴ መግለጫውን በትግራይ መገናኛ ብዙኃን ላይ አንብቧል።

    ትብብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥትን በመጣል "በሽግግር ቻርተር የሚመራ አካታች የሽግግር መንግሥት" ለመመሥረት ዓላማ እንዳለውም አስረድተዋል።

    የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከዚህ ቀደም የአዲስ ስታንዳርድ እና የዋዜማ ሬዲዮን የምዝገባ ፈቃዶች የሰረዘ ሲሆን፣ የሮይተርስ ጋዜጠኞች የዘገባ ፈቃድም ከሰረዘ በኋላ በቅርቡ መልሶ ሰጥቷል።

  19. ኤምኤስኤፍ በጋምቤላ ውስጥ በርካታ የቆሰሉ ሰዎች ወደ ጤና ጣቢያው መምጣታቸውን አስታወቀ

    ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ)

    የፎቶው ባለመብት, MSF

    መንግሥታዊ ያልሆነው ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) በጋምቤላ ክልል ውስጥ በሚገኘው ኩሌ ጤና ጣቢያ በርካታ የቆሰሉ ሰዎችን እያከመ መሆኑን ገለጸ።

    ባለፈው አርብ መስከረም 8/2019 ዓ.ም. በክልሉ ኢታንግ ልዩ ወረዳ ውስጥ የተፈጸመ ጥቃትን ተከትሎ የተጎዱ ሰዎች ናቸው ወደ ጤና ጣቢያው የመጡት።

    ጤና ጣቢያው በጥቃቱ የተጎዱ 88 ሰዎችን የተቀበለ ሲሆን፣ ከመካከላቸውም ስምንቱ የሞቱ ሲሆን ሌሎች አራት ሰዎች ወደ ጤና ጣቢያው ከሄዱ በኋላ በሕክምናው ቡድን ሕይወታቸውን ለማትረፍ ጥረት ቢደረግም መትረፍ አለመቻላቸውን ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን አስታውቋል።

    ከከባድ እስከ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው የቀሩት ተጎጂዎች ሕክምና ማግኘታቸውን እና 13 ሰዎች ለተጨማሪ የሕክምና ድጋፍ ወደ ጋምቤላ ሆስፒታል መላካቸውን ቡድኑ ገልጿል።

    ናይሮቢ ኬንያ የሚገኙት የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን የኢትዮጵያ ኃላፊ ጉል ባድሻህ “እኛ በዋናነት ቅድሚያ የምንሰጠው የተጎጂዎችን ማንነት ከግምት ውስጥ ሳናስገባ ለማንኛውም ሰው የሚያስፈልገውን የሕክምና ድጋፍ ነው" በማለት "የግጭቱ ተሳታፊዎች ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ እንዲያደርጉ" ጥሪ አቅርበዋል።

  20. ኢራን በቴህራን የሚገኝ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ማዕከልን መዝጋቷን ተከትሎ ፈረንሳይ የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ ዛተች

    በቴህራን የሚገኘው የፈረንሳይኛ ቋንቋ ትምህርት ቤት

    የፎቶው ባለመብት, DW

    የምስሉ መግለጫ, በቴህራን የሚገኘው የፈረንሳይኛ ቋንቋ ትምህርት ቤት

    ፈረንሳይ በቴህራን የሚገኘው የቋንቋ ትምህርት ቤቷ መዘጋቱን ተከትሎ የኢራንን አምባሳደር ጠርታ እንደምታነጋግር አስታወቀች።

    የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፓስካል ኮንፋቭሩክስ “ይህ ፈረንሳይ በኢራን ባላት የባሕል ማዕከል ላይ የተቃጣ ጥቃት በሐምሌ ወር በሁለት የኤምባሲ ሠራተኞቻችን ላይ ከተፈጸመው የቀጠለ ሲሆን ምክንያት እና ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለዋል።

    እሁድ ዕለት የኢራን ባለሥልጣናት በቴህራን የሚገኝ የፈረንሳይ የቋንቋ ማዕከል በአቃቤ ሕግ ትዕዛዝ መሠረት መዘጋቱን አስታውቀዋል።

    ከኢራን የፍትህ ተቋማት ጋር በቅርበት የሚሰራው ሚዛን የዜና ወኪል “በቴህራን ከሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር ግንኙነት ያለው እና በማስተማር ሽፋን ለዓመታት ሲንቀሳቀስ የነበረው ሕገወጥ ማዕከል ተዘግቷል” ሲል ዘግቧል።

    የኢራን የፍትህ አካላት “ከዲፕሎማሲ ስምምነት ውጪ ያፈነገጠ ሕገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርቷል” ሲል ወንጅሎታል።

    አክሎም ማዕከሉ "የቋንቋ ማሰልጠኛ ተቋምነቱን አላግባብ ተጠቅሟል" እንዲሁም "የአገሪቱን ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በመለየትና በመካከላቸው ትስስር በመፍጠር፣ ከአገር እንዲወጡም አመቻችቷል" ሲል ከስሷል።

    ፈረንሳይ የቀረቡባትን ውንጀላዎች ውድቅ አድርጋ ከቅርብ ወራት ወዲህ ተደጋጋሚ ትንኮሳዎች እንዳጋጠሟት አስታውቃለች።

    ከቅርብ ወራት ወዲህ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት እየተባባሰ መጥቷል።

    ባለፈው ወር ፈረንሳይ ወደ ኢራን ያቀኑ ሁለት ዲፕሎማቶቿ ለአጭር ጊዜ መታሰራቸውንና እንቅስቃሴያቸው መገደቡን ተከትሎ ሁለት የኢራን ዲፕሎማቶችን ከአገሯ አስወጥታለች።

    ቴህራን ዲፕሎማቶቹን በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ወንጅላቸዋለች።