ፓኪስታን በድርድሩ ኢራን መሳተፏ እንዳልተረጋገጠ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ሁለተኛ ዙር ንግግር ቴህራን እንደምትሳተፍ እስካሁን በይፋ አለማሳወቋን የአሸማጋይዋ አገር ፓኪስታን ገለጸች።
የፓኪስታን መረጃ እና ብሮድካስት ሚኒስትር አቱላህ ታራር እንደተናገሩት ፓኪስታን እንደ አሸማጋይ አገርነቷ “ከኢራን ጋር ያልተቋረጠ ግንኙነት” እያደረገች እንዲሁም "የዲፕሎማሲ እና የንግግር መንገድን እየተከተለች” ነው።
አሜሪካ እና ኢራን የደረሱት የሁለት ሳምንት ተኩስ አቁም በነገው ዕለት የሚጠናቀቅ ሲሆን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተደራዳሪ ቡድናቸውን ወደ ፓኪስታን እንደሚልኩ አስታውቀዋል።
የተኩስ አቁሙ ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት ኢራን በድርድሩ እንደምትሳተፍ ውሳኔ ማሳለፏ “ወሳኝ” መሆኑን የፓኪስታኑ ሚኒስትር ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ባወጡት መግለጫ፤ “ፓኪስታን የኢራን አመራሮች በሁለተኛው ዙር ድርድር እንዲሳተፉ ለማሳመን ከልብ የመነጨ ጥረት አድርጋለች፤ ይህ ጥረትም አሁንም ቀጥሏል" ብለዋል።
ሁለተኛው ዙር ድርድር የመካሄዱ ነገር ካለው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ እንጥልጥል ላይ የሚገኝ ሲሆን አሁን ፓኪስታን የሰጠችው መግለጫ ንግግሩ የመካሄዱ ጉዳይ በኢራን እጅ እንደሚገኝ እውቅና የሰጠ ነው። ፓኪስታን፤ ኢራን የመሳተፏ ነገር አለመረጋገጡን በይፋ ስታሳውቅ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።


















