ቀጥታ, አሜሪካ እና ኢራን ሊያበቃ የተቃረበውን የተኩስ አቁም በመጣስ እየተካሰሱ ነው

የአሜሪካ ኃይሎች የኢራንን መርከብ ከተቆጣጠሩ በኋላ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የተኩስ አቁሙን “ለበርካታ ጊዜያት” እየጣሰች ነው ሲሉ፣ ኢራን በበኩሏ አሜሪካ “የባሕር ላይ ውንብድና” እየፈጸመች ነው በማለት ከስሳለች።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ፓኪስታን በድርድሩ ኢራን መሳተፏ እንዳልተረጋገጠ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ገለጸች

    ፓኪስታን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው ሁለተኛ ዙር ንግግር ቴህራን እንደምትሳተፍ እስካሁን በይፋ አለማሳወቋን የአሸማጋይዋ አገር ፓኪስታን ገለጸች።

    የፓኪስታን መረጃ እና ብሮድካስት ሚኒስትር አቱላህ ታራር እንደተናገሩት ፓኪስታን እንደ አሸማጋይ አገርነቷ “ከኢራን ጋር ያልተቋረጠ ግንኙነት” እያደረገች እንዲሁም "የዲፕሎማሲ እና የንግግር መንገድን እየተከተለች” ነው።

    አሜሪካ እና ኢራን የደረሱት የሁለት ሳምንት ተኩስ አቁም በነገው ዕለት የሚጠናቀቅ ሲሆን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተደራዳሪ ቡድናቸውን ወደ ፓኪስታን እንደሚልኩ አስታውቀዋል።

    የተኩስ አቁሙ ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት ኢራን በድርድሩ እንደምትሳተፍ ውሳኔ ማሳለፏ “ወሳኝ” መሆኑን የፓኪስታኑ ሚኒስትር ተናግረዋል።

    ሚኒስትሩ በኤክስ ገጻቸው ባወጡት መግለጫ፤ “ፓኪስታን የኢራን አመራሮች በሁለተኛው ዙር ድርድር እንዲሳተፉ ለማሳመን ከልብ የመነጨ ጥረት አድርጋለች፤ ይህ ጥረትም አሁንም ቀጥሏል" ብለዋል።

    ሁለተኛው ዙር ድርድር የመካሄዱ ነገር ካለው ሳምንት መጨረሻ አንስቶ እንጥልጥል ላይ የሚገኝ ሲሆን አሁን ፓኪስታን የሰጠችው መግለጫ ንግግሩ የመካሄዱ ጉዳይ በኢራን እጅ እንደሚገኝ እውቅና የሰጠ ነው። ፓኪስታን፤ ኢራን የመሳተፏ ነገር አለመረጋገጡን በይፋ ስታሳውቅ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

  2. ኢራን ድርድር ውስጥ ከገባች “እጇ ከቃታው ላይ” እንደማይነሳ የመንግሥት ቃል አቀባይ ተናገሩ

    የኢራን ባንዲራ የያዙ ሰልፈኞች

    የፎቶው ባለመብት, Morteza Nikoubazl/NurPhoto via Getty Images

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር ድርድር የምታደርግ ከሆነ ንግግር ውስጥ የምትገባው “እጇን ቃታው ላይ” አድርጋ እንደሚሆን እና መከላከያ ኃይሏ “ሙሉ ዝግጁነት” እንደሚኖረው የአገሪቱ መንግሥት ቃል አቀባይ ተናገሩ።

    ከመንግሥታዊው ዜና ወኪል ‘ኢርና’ ጋር ቆይታ ያደረጉት ቃል አቀባይዋ ፋጤሜህ ሞሃጄራኒ ኢራን በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ በሚካሄደው ቀጣይ ዙር ድርድር ትሳተፍ እንደሆነ ማረጋገጫም ይሁን ማስተባበያ አልሰጡም።

    “ከፊት ለፊታችን ሁለት ስትራቴጂዎች አሉ። የመጀመሪያው የጦርነት ስትራቴጂ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ የዲፕሎማሲ ስትራቴጂ ነው” ሲሉ ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።

    የኢራን ተደራደሪ ቡድን “በብሔራዊ ጥቅም ላይ ቅንጣት እንኳ አያመቻምችም” ብለዋል።

    ቃል አቀባይዋ ይህንን የአገሪቱ መንግሥት አቋም የገለጹት ሁለተኛ ዙር ድርድር ይካሄድ እንደሆነ ማረጋገጫ ባልተገኘበት ሁኔታ ውስጥ ነው።

    ተደራዳሪ ልዑካቸውን ወደ ዛሬ ፓኪስታን እንደሚልኩ ያስታወቁት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ተደራዳሪዎቿን ወደ ፓኪስታን “ከመላክ ውጪ አማራጭ የላትም” ብለዋል።

    በነገው ዕለት የሚጠናቀቀውን የሁለት ሳምንት ተኩስ አቁም የማራዘም ፍላጎት እንደሌላቸውም አስታውቀዋል።

  3. ትራምፕ፤ ኢራን ተደራዳሪዎቿን ወደ ፓኪስታን “ከመላክ ውጪ አማራጭ የላትም” አሉ

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ከአሜሪካ ጋር ለሚደረገው ድርድር ልዑካኗን ወደ ፓኪስታን “ከመላክ ውጪ አማራጭ የላትም” በማለት ተናገሩ።

    በምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የሚመራው የአሜሪካ ልዑክ ከኢራን ጋር ለሚደረግ ንግግር ዛሬ ወደ ፓኪስታን የሚጓዝ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ቴህራን ተደራዳሪዎቿን እንደምትልክ ማረጋገጫ አልሰጠችም።

    ከአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲኤንቢሲ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ የሚደረገው ድርድር “ከታላቅ ስምምነት ጋር ይጠናቀቃል” የሚል መተማመን እንዳላቸው ተናግረዋል።

    አሜሪካ “እየተጋፈጠች ያለችው ከጥሩ ሰዎች ጋር አይደለም” ያሉት ትራምፕ፤ ነገር ግን “ስኬታማ” ተግባር እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል። አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ የጣለችውንም እገዳ “ታላቅ ስኬት” ሲሉ ጠርተውታል።

    አሜሪካ እና ኢራን ለሁለት ሳምንት እንዲቆይ የተስማሙት ተኩስ አቁም ነገ ረቡዕ ይጠናቀቃል። ከኢራን ጋር የሚደረገው ድርድር በጥሩ ሁኔታ የሚሄድ ከሆነ ተኩስ አቁሙን ያራዝሙት እንደሆነ የተጠየቁት ትራምፕ፤ “ያንን ማድረግ አልፈልግም” ሲሉ አቋማቸውን አሳውቀዋል።

    “የቦንብ ድብደባ እንደሚኖር እጠብቃለሁ፤ ምክንያቱም ጥሩ ባህሪ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

    ስምምነት ላይ ለመድረስ “ብዙ ጊዜ” እንደሌለ የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ ኢራኖች ከአሜሪካ ጋር የሚስማሙ ከሆነ “እጅግ ጥሩ ስፍራ ላይ ያርፋሉ” ብለዋል።

  4. አሜሪካ እና ኢራን ሊያበቃ የተቃረበውን የተኩስ አቁም በመጣስ እየተካሰሱ ነው

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ጋሊባፍ እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ጋሊባፍ እና ፕሬዝዳንት ትራምፕ

    አሜሪካ እና ኢራንን ለሁለት ሳምንታት የደረሱት የተኩስ አቁም ሊጠናቀቅ በተቃረበበት በአሁኑ ጊዜ ሁለቱ አገራት ተኩስ አቁሙን በመጣስ እየተካሰሱ ነው።

    የአሜሪካ ኃይሎች የኢራንን መርከብ ከተቆጣጠሩ በኋላ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን የተኩስ አቁሙን “ለበርካታ ጊዜያት” እየጣሰች ነው ሲሉ፣ ኢራን በበኩሏ አሜሪካ “የባሕር ላይ ውንብድና” እየፈጸመች ነው ብላለች።

    ፕሬዝዳንቱ በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ አሜሪካ የምትፈጽመውን ጥቃት ያስቆመውን የተኩስ አቁም ኢራን በተደጋጋሚ ጥሳለች ሲሉ ከስሰዋል።

    ነገር ግን ትራምፕ ለዚህ ክሳቸው ምንም ዓይነት ማብራሪያም ሆነ ማጠናከሪያ አልሰጡም።

    ኢራንም በበኩሏ አሜሪካ የተደረሰውን የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም በተደጋጋሚ ጥሳለች ስትል ስከስስ ቆይታለች።

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ዕቀባን ሲጥሉ እና ሲያነሱ የቆዩት ሁለቱ አገራት በአካባቢው ያላቸውን የበላይነት ለማሳየት እየጣሩ ነው።

    የአሜሪካ ባሕር ኃይል በሆርሙዝ ላይ የተጣለውን እገዳ የጣሰ ነው ባሉት የኢራን መርከብ ላይ መተኮሳቸውን ተከትሎ የኢራን ጦር ኃይል ለአሜሪካ “ወደታራዊ የባሕር ላይ ውንብድና” ለላው ጥቃት አጸፋ እንደሚመለስ ዝቷል።

    ጨምሮም አሜሪካ በሆርመዝ ወሽመጥ ላይ በኢራን መርከቦች ላይ እየወሰደችው ያለው እርምጃ “የተኩስ አቁም ስምምነቱን የሚጥስ ነው” በማለት ከስሷል።

  5. ጦርነት እና የኢንተርኔት መቋረጥ የጎዳቸው ኢራናውያን

    ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በኢራን የምግብ ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል

    የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock

    የምስሉ መግለጫ, ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በኢራን የምግብ ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል

    በኢራን ውስጥ የእስላማዊ ሪፐብሊኩ ደጋፊዎች ሳይቀር ለማይቀረው የምጣኔ ኃባት ፈተና ቀበቷቸውን እያጠበቁ ነው።

    ጥያቄው የኢራን መንግሥት የሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቶ የሚቀጥል ከሆነ ለሠራተኞቹ ደመወዝ መክፈል ይችላል? የሚለው ነው። ቴህራን ከውይይት መድረክ ራሷን አርቃስ መቆየት ትችላለች?

    ከጦርነቱ በፊት የኢራንን ምጣኔ ኃብት ማዕቀብ፣ የዋጋ ግሽበት እንዲሁም የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም ፈትኖታል።

    ቤተሰቦች አቅማቸው ተሟጥጦ መሠረታዊ ነገሮች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ሆነዋል።

    አሁን በጦርነቱ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱ ንግዶች ከፔትሮኬሚካል፣ ስቲል እና አሉሚኒየም ኢንዱስትሪዎች መውደም ጋር ተያይዞ የምጣኔ ኃብት ቀውሱ ጫና ተባብሷል።

    ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በኢራን የምግብ ዋጋ በእጥፍ ጨምሯል፤ በተጨማሪም ወደ ውጪ የሚላኩ ምርቶችም ቀንሰዋል።

    የኢራን የገንዘብ ምንዛሬ በመውደቁም ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት ተከስቷል።

    የኢራን ባለሥልጣናት እስራኤል እና አሜሪካ በአገሪቱ ላይ የከፈቱትን ጦርነት ተከትሎ የደረሰውን የምጣኔ ኃበት ጫና 270 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት አስታውቀዋል።

    የምጣኔ ኃብቱ ጫና በተለይ አነስተኛ የኦንላየን ንግዶችን የሚሰሩ ሴቶች ላይ የበረታ ነው።

    የኢንተርኔት መቋረጥ የእደ ጥበብ ውጤቶችን እየሰሩ በማኅበራዊ ሚዲያ እና ኦንላየን የሚሸጡ በርካታ ሴቶችን ከገበያ በማስወጣት እነርሱን እና ቤተሰቦቻቸውን ባዶ እጃቸውን አስቀርቷል።

    ጦርነት እና የኢንተርኔት መቋረጥ የመሠረተ ልማት ውድመት ብቻ ሳይሆን በመላው ኢራን የበርካቶችን ቤት ያንኳኳ ችግር አስከትሏል።

  6. “በእግድ ውስጥ ያለ እግድ”- አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የጣለችው የመርከቦች እንቅስቃሴ ክልከላ

    ነዳጅ ጫኝ መርከቦች

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚደረገውን የመርከቦች እንቅስቃሴ ከጦርነት በፊት ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረገው ጥረት እንዲሁም ከኢራንን ጥቃት እና ቁጥጥር ጋር የሚደረገው ትግል የአሜሪካ ቀዳሚ ተግባር ነው።

    የቀድሞው የብሪታኒያ ባሕር ኃይል አዛዥ ኮማንደር ቶም ሻርፕ ኢራን በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የራሷን ገደቦች ጥላ እያለ፣ አሜሪካ ደግሞ ወደ ቴህራን ወደቦች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን መከልከሏን በመጥቀስ፣ እየተከተለች ያለውን ስልት “በእግድ ላይ እግድ” ሲሉ ገልጸውታል።

    ዋይት ሐውስ ኢራን ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንድትመጣ ለማድረግ “በቂ ጉዳት” ለመፍጠር እየተሞከረ ነው ሲሉ ይናገራሉ።

    “የኢራንን የነዳጅ ምርት ከኢራን እንዳይወጣ በመከላከል ጉዳቱ ወደ ድርድር ጠረጴዛ ላይ እንዲመጡ እንዲያደርጋቸው ነው? የጉዳቱ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ለማየት አስቸጋሪ ነው፤ እያየነው ያለን አይመስለኝም” ብለዋል።

    ሻርፕ የኢራን አገዛዝ ከፍተኛውን ጉዳት ተቀብሎ ለማስተናገድ ፈቃደኛ መሆኑን እያሳየ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

    "ከእስላማዊ ሪፐብሊክ ርዕዮተ ዓለም የበለጠ አንድም ግለሰብ፣ መንግሥት፣ ኢኮኖሚ፣ ወይም ጠቃሚ መሠረተ ልማት የለም፤ እና ይህ ከዩኤስ ጋር ያለው ፍጥጫ ገና ከጅምሩ ሲዘጋጅበት የነበረው ነው።"

    ከዚያም ባሻገር የኢራን ባለሥልጣናት በሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ ላይ ያላቸውን “ሉዓላዊነት” እውቅና ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አጥብቀው ይጠይቃሉ።

    ዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያዎችን የማስተጓጎል ችሎታቸው ጠንካራ ስልት እንደሆነ እና እንዲያውም ትርፋማ መንገድ መሆኑን ተምረዋል የሚሉት ቶም ሻርፕ፣ መርከቦች ደህንነታቸው ተጠብቆ ለማለፍ ቀረጦችን ለማስከፈል ወስነዋል ይላሉ።

    እንደ ባሕር ኃይሉ ገለጻ ከሆነ ያንን ስልት ለመተው ፈቃደኛ የሆነ ማንኛውም የኢራን ተደራዳሪዎች ማየት ከባድ ነው።

  7. ቻይና ኢዝላማባድ የአሜሪካ እና ኢራን ውይይትን ለማመቻቸት የምታደርገውን ጥረት “ሙሉ በሙሉ እንደምትደግፍ” ገለጸች

    የፓኪስታን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢስሃቅ ዳር በፓኪስታን የቻይና አምባሳደር ጂያንግ ዛይዶንግ ጋር ሲወያዩ

    የፎቶው ባለመብት, Pakistan Ministry of Foreign Affairs via X

    የምስሉ መግለጫ, የፓኪስታን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢስሃቅ ዳር በፓኪስታን የቻይና አምባሳደር ጂያንግ ዛይዶንግ ጋር ሲወያዩ

    በፓኪስታን የቻይና አምባሳደር ኢዝላማባድ፣ አሜሪካ እና ኢራን ወደ ውይይት ጠረጴዛ እንዲመጡ የምታደርገውን ጥረት ቤይጂንግ “ሙሉ በሙሉ እንደምትደግፍ” ገለፁ።

    የፓኪስታን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢስሃቅ ዳር ከጂያንግ ዛይዶንግ ጋር በአካባቢው ስላለው ሁኔታ መወያየታቸው ተገልጿል።

    በስብሰባው ወቅት፣ ዛይዶንግ ፓኪስታን በዩናይትድ ስቴትስ እና በኢራን መካከል "በቀጣናው እና ከዚያም ባሻገር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ" ፓኪስታን የምታደርገውን ቀጣይ ጥረት ማድነቃቸውን የፓኪስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

  8. የቴህራን መገናኛ ብዙኃን ከኢራን ወደ ፓኪስታን የሄደ ልዑካን ቡድን እንደሌለ ዘገቡ

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን በቴሌግራም ገጻቸው ላይ እስካሁን ድረስ ከአሜሪካ ጋር ለሚደረገው ድርድር ወደ ኢዝላማባድ የሄደ ልዑክ አለመኖሩን አስታወቁ።

    መገናኛ ብዙኃኑ “ዋነኞቹም ሆኑ ወይም በሁለተኛ ደረጃ ያሉት አልያም የመጀመርያውም ሆነ ተከታይ ቡድን እስካሁን ድረስ ወደ ኢዝላማባድ የሄደ የልዑካን ቡድን የለም” ብለዋል።

    ከዚህ በተጨማሪ በቴሌግራም ገጹ ልጥፍ ላይ የልዑካን ቡድኑ መነሳት ወይም መድረስን አስመልክቶ “በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እና የቀጣናው ምንጮች” የተናፈሰው “ወሬ” ውድቅ ተደርጓል።

    የመገናኛ ብዙኃኑ ዘገባ በፓርላማ አፈ ጉባዔ ሞሐመድ ባጋር ጋሊባፍ እንዲሁም ሌሎች የኢራን ባለሥልጣናት የተባለውን ዳግም በማስተጋባት ቴህራን “በስጋት ጥላ ውስጥ ሆና ድርድርን አትቀበልም” ብለዋል።

  9. ትራምፕ ከኢራን ወደቦች የሚንቀሳቀሱ መርከቦች ላይ የጣሉትን እገዳ መቼ ያነሳሉ?

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ የለቀቀው የኢራን መርከብ ምስል

    የፎቶው ባለመብት, US Central Command/X

    አሜሪካ ከቴህራን ጋር ስምምነት እስኪደረስ ድረስ በኢራን ወደቦች ላይ የጣለችውን እገዳ እንደማታነሳ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታወቁ።

    ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት ጦርነቱን ለማስቆም ያስችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ሁለተኛ ዙር ድርድር ስለመካሄዱ እርግጠኛ መሆን ባልተቻለበት ወቅት ነው።

    ትራምፕ ከአንድ ሳምንት በፊት ጀምሮ ተግባራዊ ያደረጉት እገዳ "ኢራንን ሙሉ በሙሉ እያወደመ ነው" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

    ትራምፕ አክለውም አገራቸው ጦርነቱን "በብዙ መልኩ እያሸነፈች ነው" ብለዋል።

    ይህ የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተያየት የተሰማው አሜሪካ እና ኢራን ያደረጉት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ሊጠናቀቅ ሁለት ቀናት ብቻ በቀሩበት ወቅት ነው።

    ነገር ግን በፓኪስታን ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ሁለተኛ ዙር የሰላም ድርድር ስለመካሄዱ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም።

  10. ትራምፕ ኢራን ያበለጸገችውን ዩራኒየም ማስወገድ ”ረዥም እና አስቸጋሪ” ሂደት ነው አሉ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን የበለጸገውን ዩራኒየም ማውጣት ከባድ መሆኑን በማኅበራዊ ሚደያ ገጻቸው ላይ ተናገሩ።

    “ዘመቻ ሚድናየት ሃመር የተሟላ እና ሙሉ በሙሉ የኢራንን አቧራማ የኒውክሌር ተቋማት ያወደመ ነበር። ስለዚህ ቆፍሮ ማውጣት ረዥም እና አስቸጋሪ ሂደት ነው” ሲሉ ጽፈዋል።

    ዘመቻ ሚድ ናይት ሐመር አሜሪካ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር በኢራን ላይ የፈጸመችው ድብደባ መጠሪያ ሲሆን 125 የአሜሪካ ጦር አውሮፕላኖች ተሳትፈውበታል።

    የአሜሪካ ጦር አውሮፕላኖች የደበደቧቸው ሦስት የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ፎርዶ፣ ናታንዝ እና ኢስፋሃን ናቸው።

    ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው ላይ “ሐሰተኛው ሲኤንኤን እና ሌሎች ብልሹ የመገናኛ ብዙኃኖች የጦር አውሮፕላን አብራሪዎቻችን የሚገባቸውን ክብር ሳይሰጧቸው ቀርተዋል፤ ሁልጊዜም ማንኳሰስ እና ማንቋሸሽ- ተሸናፊዎች።”

  11. አሜሪካ እና ኢራን ለሁለተኛው ዙር ድርድር ስለመገናኘታቸው እርግጠኛ መሆን ያልተቻለው ለምንድን ነው?

    የፓኪስታን ጎዳናዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    አሜሪካ እና ኢራን በኢዝላማባድ ለሚያደርጉት ውይይት ዝግጅቶች ተጠናቅቀዋል።

    በዋና ከተማው ውስጥ መኪኖች ሲንቀሳቀሱ ይፈተሻሉ። በጎዳናዎቹ ግራ እና ቀኝ "ኢዝላማባድ ቶክስ” የሚሉ ፖስተሮች ተለጥፈዋል። ነገር ግን በሁለቱ አገራት መካከል ንግግሩ ስለመካሄዱ ማንም እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይችልም።

    ዋይት ሐውስ በጄዲ ቫንስ የሚመራ የአሜሪካ ልዑክ ወደ ፓኪስታን እንደሚሄድ ቢናገርም፣ ጊዜው ግን ግልጽ አልተደረገም።

    የልዑካን ቡድኑ ኢዝላማባድ መድረስ ቢኖርበትም ሰኞ ዕለት ግን ከዋሽንግተን እንዳልተንቀሳቀሰ ማወቅ ተችሏል።

    በትክክል እየሆነ ያለውን በግልጽ ማወቅ ያልተቻለው ኢራን መሳተፏን በይፋ ማሳወቅ ስላልፈለገች ይመስላል።

    በምትኩ በመግለጫቸው ውስጥ አሁንም ቁጣና እልህ አለ።

    የኢራንን ልዑክ ይመራሉ ተብለው የሚጠበቁት የአገሪቱ የፓርላማ አፈ ጉባኤ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ ኢራን “በማስፈራራት ጥላ ስር ሆና ድርድርን አትቀበልም” ሲሉ ተናግረዋል።

    ዶናልድ ትራምፕንም “ከበባ በመክፈት እና የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ” ከስሰዋል።

    አፈ ጉባዔው እየጠቀሱ ያሉት በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የተፈጠሩ ክስተቶችን ነው። አሜሪካ የኢራንን ባንዲራ የሚያውለበልብ የጭነት መርከብ በቁጥጥር ስር ማዋሏን እንዲሁም የኢራንን ወደቦች መዝጋቷን እየተቃወሙ ይገኛሉ።

    በኢራን ውስጥ ያሉ ወታደራዊ አመራሮች ጋሊባፍን ከዲፕሎማሲ ይልቅ ጦርነትን እንዲመርጡ ግፊት እያደረጉ ይገኛሉ።

    ከመጋረጃ ጀርባ ደግሞ በኢራን ውስጥ የሚደረግ የሥልጣን ሽኩቻ ለመዘግየቱ የሚጠቀስ ሌላ ምክንያት ነው።

    በርካቶች ጉምቱ አመራሮቿ የተገደሉባት ኢራን ውስጥ የአገሪቱን ሥልጣን በበላይነት ለመቆጣጠር በሚፈልጉ የተለያዩ አካላት ሽኩቻ መፈጠሩ አይቀሬ ነው።

    በይፋ የምንሰማው አብዛኛው ነገር የፖለቲካ ድንፋታ ሊሆን ይችላል። እናም ባለሥልጣናት የሚሉት ምንም ይሁን ምን ኢራን ወደ ኢዝላማባድ ለመጓዝ እየተዘጋጀች ሊሆን ይችላል።

    ነገር ግን ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው የተኩስ አቁም ከማብቃቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ መሆኑ የበለጠ አሳሳቢ ያደርዋል።

    ስለዚህ የሰላም ውይይቱ በእርግጥ ይካሄድ እንደሆነ ማወወቅ ለማንም አዳጋች ነው።

  12. የቻይናው ፕሬዚዳንት በሆርሙዝ ወሽመጥ መደበኛው እንቅስቃሴ መመለስ አለበት አሉ

    ዢ ጂንፒንግ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ በሆርሙዝ ወሽመጥ የሚደረግ የመርከቦች "መደበኛ እንቅስቃሴ"፤ "መመለስ ይኖርበታል" አሉ።

    ፕሬዚዳንቱ ይህንን ያሉት ከሳዑዲ አረቢያው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሳልማን ጋር ሰኞ ዕለት በስልክ በተወያዩበት ወቅት ነው።

    ትራምፕ እና ዢ በቻይና በግንቦት ወር አጋማሽ ላይ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘዋል።

    ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች ለመገናኘት ቀን ከቆረጡ በኋላ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተነሳ ወደ ግንቦት አራዝመውታል።

  13. ኢራን ለውጊያው “አዲስ ስልት” እያዘጋጀች መሆን ገለጸች

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ በኤክስ ገጸቸው ላይ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ኢራን “በውጊያ ሜዳ ላይ አዲስ ስልት ለማሳየት እየተዘጋጀች ነው” በማለት “በስጋት ጥላ ስር ሆነን ድርድርን አንቀበለም” አሉ።

    ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ከኢራን ጋር ከስምምነት ለመድረስ ጫና ውስጥ አለመሆናቸውን በመግለጽ አስተባብለዋል።

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ማክሰኞ ዕለት ወደ ፓኪስታን ይሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ትራምፕ ከኢራን ጋር የተደረሰው እና ረቡዕ ዕለት የሚያበቃው የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም የመቀጠል ዕድሉ በጣም ጠባብ መሆኑን ጨምረው አስታወቀዋል።

    አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የኢራንን ወደቦች መዝጋቷን የቀጠለች ሲሆን እሁድ ዕለት የአገሪቱን ባንዲራ የሚያውለበልብ የጭነት መርከብን በቁጥጥር ስር ካዋለች ወዲህ ሁለቱም አገራት እርስ በእርስ የተኩስ አቁሙን በመጣስ ተወነጃጅዋል።

    በእስራኤል እና በሊባኖስ መካከል የሚደረገው ሁለተኛ ዙር ውይይት ሐሙስ ዕለት እንደሚጀመር የአሜሪካ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

  14. ትራምፕ የተኩስ አቁሙ ከማብቃቱ በፊት ከስምምነት ላይ ለመድረስ “ጫና ውስጥ” ናቸው መባሉን አስተባበሉ

    ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ዶናልድ ትራምፕ የቀደሙት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ካደረጓቸው ስምምነቶች “በእጅጉ የተሻለ” ስምምነት ከኢራን ጋር ሊያደርጉ መሆኑን ተናገሩ።

    ከኢራን ጋር “በአንጻራዊነት በፍጥነት” ከስምምነት ላይ እንደሚደርሱ የተናገሩት ትራምፕ፣ የተኩስ አቁሙ ከማብቃቱ በፊት ስምምነት ለመፈረም “ጫና ውሰጥ” ናቸው የሚለውን አስተባብለዋል።

    ፕሬዚደንት ትራምፕ አሜሪካ፣ ዩኬ፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ሩሲያ አና ጀርመን እአአ በ2015 ከኢራን ጋር የደረሱትን ስምምነት በተደጋጋሚ በመተቸት ይታወቃሉ።

    ትራምፕ ይህንን “ከአገራችን ደህንነት ጋር ግንኙነት ካላቸው በጣም መጥፎ ስምምነቶች ውስጥ አንዱ ነው” ሲሉ ከተቹ በኋላ “የተረጋገጠ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ መንገድ ነው” በማለት “የማይሆን፤ ሊሆን የማይችል ነው” ሲሉ አጣጥለውታል።

    ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ዘመናቸው አሜሪካን ከስምምነቱ አስወጥተዋል።

    ውሉን ባያቋርጡ ኖሮ "በእስራኤል እና በመላው መካከለኛው ምሥራቅ" የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር ተናግረዋል።

    በሌላ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው ላይ ደግሞ ከኢራን ጋር “በአንጻራዊት በፍጥነት” ከስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ተናግረዋል።

    አክለውም ከስምምነት ለመድረስ “ጫና ውስጥ” አለመሆናቸውን “ያ ስህተት ነው” በማለት አስተባብለዋል።

  15. የቴህራን ሁለት አውሮፕላን ማረፊያዎች መንገደኞችን ማስተናገድ ጀመሩ

    የቴህራን መህራባድ አውሮፕላን ማረፊያ ከኢማም ኻሜኒ አውሮፕላን ማረፊያ ጋር መንገደኞችን እነዲያስተናግድ ፈቃድ ተሰጥቶታል።

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሁለት የቴህራን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች መንገደኞችን እንዲያስተናግዱ ፈቃድ ተሰጣቸው።

    ኢማም ኾሜኒ እና መህራባድ አውሮፕላን ማረፊያዎች ከዛሬ ጀምሮ መንገደኞችን እንዲያስተናግዱ መፈቀዱን የገለጸው የአገሪቱ ሲቪል አቪየሽን ነው።

    መህራባድ አውሮፕላን ማረፊያ በቅርቡ በተደረገው ጦርነት ጥቃት የደረሰበት ሲሆን እስራኤል በርካታ አውሮፕላኖችን "ማውደሟን” ገልጻ ነበር።

    የአገሪቱ ሲቪል አቪየሽን ሌሎች አስር አውሮፕላን ማረፊያዎች ከቅዳሜ ጀምሮ መንገደኞችን ማስተናገድ እንደሚችሉ ተናግሯል።

  16. የኢራኑ ፕሬዚዳንት 'ኢራን ለኃይል አትንበረከክም' አሉ

    የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን አገራቸው ከአሜሪካ ጋር በሁለተኛው ዙር ድርድር መሳተፏ ባልተረጋገጠበት ወቅት “ኢራናውያን ለኃይል አይንበረከኩም” አሉ።

    ኢራን በአሜሪካ መንግሥት ላይ "ጥልቅ ታሪካዊ አለመተማመን" እንዳላት የገለፁት ፕሬዚዳንቱ "የተገቡ ቃሎችን ማክበር"፤ “ትርጉም ላለውውይይት መሠረት መሆን አለበት” ብለዋል።

    ፔዜሽኪያን በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት "ከአሜሪካ ባለሥልጣናት የሚመጡ ገንቢ ያልሆኑ እና የሚቃረኑ ምልክቶች መራራ መልእክት ያስተላልፋሉ፤ ኢራን እጇን እንድትሰጥ ይፈልጋሉ" ብለዋል።

  17. አሜሪካ በሆርሙዝ እገዳ ከጣለች ጊዜ ጀምሮ 27 መርከቦችን መከለከሏን አስታወቀች

    በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚገኘው የኢራን ወደብ የሳተላይት ምስል

    የፎቶው ባለመብት, EUROPEAN UNION/COPERNICUS SENTINEL-2/Handout via Reuters

    የአሜሪካ ጦር በሆርሙዝ ላይ እገዳውን ከጣለ ጊዜ ጀምሮ 27 መርከቦች ወደ ኢራን ወደብ እንዳይሄዱ ወይንም እንዲመለሱ ማድረጉን አስታወቀ።

    የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ በኤክስ ገጹ ለይ ባሰፈረው ቪዲዮ ግዙፍ መርከቦች ክልከላው ወደታጠለበት የውሃ ክልል መግባታቸውን ሲነገራቸው ይደመጣል።

    በዚህ ወር መጀመርያ ላይ የአሜሪካ ባህር ኃይል ቴህራን ከነዳጅ ሽያጭ የምታገኘውን ትርፍ ለማስቆም በሚል ወደ ወደቦቿ የሚገቡም ሆነ ከወደቦቿ የሚወጡ መርከቦች ላይ እግድ እንደሚጥል አስታውቆ ነበር።

  18. የሊባኖሱ ፕሬዚዳንት ከእስራኤል ጋር የሚኖረው ድርድር ከአሜሪካ እና ኢራን ውይይት “የተለየ” መሆኑን ተናገሩ

    የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ አውን ከእስራኤል ጋር የሚደረጉ ድርድሮች ከአሜሪካ እና ኢራን የሰላም ድርድር "የተለዩ” መሆናቸውን ገለጹ።

    አውን በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ሊባኖስ በቀጣይ በሚኖሩ ውይይቶች በአሜሪካ የቀድሞ የሊባኖስ አምባሳደር በነበሩት ሲሞን ካራም በሚመራ ልዑካን ቡድን እንደምትወከል ተናግረዋል።

    ከዚህ ቡድን ውጪ አገሪቱን የሚወክል ሌላ ተደራዳሪ እንደሌለ እንዲሁም በሌላ እንደማይተካ ጨምረው አብራርተዋል።

    የውይይቱ ዓላማዎች "ጥቃቶችን ማስቆም"፣ እስራኤል "በደቡባዊ ሊባኖስ አካባቢዎች የምትፈጽመውን ወረራ" ማስቆም እንዲሁም የሊባኖስን ጦር "በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባለው የአገሪቱ ደቡባዊ ድንበር" ላይ ማሰማራት እንደሆነ ተናግረዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሊባኖስን ጥያቄዎች "ሙሉ በሙሉ መረዳታቸውን" ገልጸዋል ያሉት አውን፣ እንዲሁም በቅርቡ የሚደረጉ ድርድሮችን በማመቻቸት ረገድ እገዛ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

    በተጨማሪም “ሊባኖስን ማዳን እንደምንችል ተስፋ አለኝ” ሲሉ ተናግረዋል።

    በሁለቱ አገራት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት መደረጉ ቢገለጽም ቤንያሚን ኔታንያሁ የእስራኤል ወታደሮች ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ 10 ኪ.ሜ. ዘልቀው በመግባት እንደሚቆዩ ተናግረዋል።

  19. በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉት ሁለት የተኩስ አቁሞች ምን ይመስላሉ?

    በደቡባዊ ቤይሩት በፈረሰ ሕንጻ አጠገብ የምታልፍ ሴት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    በአሁኑ ሰዓት በመካከለኛው ምሥራቅ ሁለት የተኩስ አቁሞች አሉ። አንዱ ሊባኖስ እና እስራኤል መካከል የተደረሰ ሲሆን ሌላው ደግሞ አሜሪካ ከኢራን ጋር የገባችው የተኩስ አቁም ነው።

    ኢራን እና አሜሪካ

    ለሁለት ሳምንት ያህል እንደሚቆይ የተገለጸው ይህ የተኩስ አቁም የሚያበቃው ረቡዕ ዕለት ነው።

    የዩናይትድ ስቴትስ ባህር ኃይል በኦማን ሰላጤ ላይ የኢራንን ባንዲራ በምታውለበልብ መርከብ ላይ ተኩስ ከፍቶ በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ የኢራን ጦር አሜሪካን “በተኩስ አቁም ጥሰት” ወንጅሏታል።

    ዛሬ በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢዝላማባድ በሁለቱ አገራት መካከል ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ሁለተኛ ዙር ውይይት እስካሁን ድረስ ስለመካሄዱ በእርግጠኝነት መናገር አልተቻለም።

    የአሜሪካ ልዑካን ቡድንን የሚመሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጄዲ ቫንስ ሲሆኑ የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ግን በድርድሩ ላይ ለመሳተፍ “እቅድ የለንም” ብለዋል።

    ሊባኖስ እና እስራኤል

    በሁለቱ አገራት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊ መሆን የጀመረው አርብ ዕለት ሲሆን ለአስር ቀን የሚቆይ ነው።

    ስምምነቱ የተደረሰው በሊባኖሱ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ አውን እና በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚነሲእትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መካከል ነው።

    ሁለቱ አገራት አሜሪካ ተጨማሪ የቀጥታ ድርድሮችን እንድታመቻች መጠየቃቸው ተገልጿል።

    የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው ዝርዝር መረጃ ሊባኖስ ሄዝቦላህ እና ሌሎች ”ከመንግሥት ውጭ የሆኑ ታጣቂ ቡድኖች” በእስራኤል በሚገኙ ዒላማዎች ላይ ጥቃት እንዳይፈጽሙ ለማድረግ “ተጨባጭ እርምጃዎችን” መውሰድ አለባት።

    ሄዝቦላህ የተኩስ አቁሙን ለማክበር ፈቃደኛ መሆኑን የገለጸ ቢሆንም “የእስራኤል ወታደሮች እንዳይንቀሳቀሱ” የሚለው በስምምነቱ ውስጥ መካተት አለበት ሲል ጠይቋል።

  20. የኢራን ፕሬዝዳንት "ውጥረትን ለመቀነስ እያንዳንዱ የዲፕሎማሲ መንገድ ጥቅም ላይ መዋል አለበት" አሉ

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን "ጦርነት ለማንም አይጠቅምም፤ ምንም እንኳን ከሚደርሰው ማስፈራሪያ በተቃራኒ በጽናት ብንቆምም፣ እያንዳንዱ ምክንያታዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ውጥረትን ለመቀነስ ጥቅም ላይ መዋል አለበት" አሉ።

    ፔዜሽኪያን ዛሬ የአገራቸውን ፍትህ ሚኒስቴር በጎበኙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ኢራናውያን "ስለ አገሪቱ እውነታዎች መረጃ ማግኘት አለባቸው" ያሉ ሲሆን "የተሳሳቱ መረጃዎችን ወይም ከእውነታው የራቁ ተስፋዎችን መስጠት ችግሮችን ለመፍታት እንዳንችል ማድረግ ብቻ ሳይሆን የሕዝብን እምነትም ያሳጣል" ብለዋል።

    "ስኬቶቹም ሆኑ ተግዳሮቶቹ ለሕዝብ በሐቅ መነገር አለባቸው" ሲሉ ፔዜሽኪያን ተናግረዋል።

    ቀደም ሲል የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቴህራን በሚቀጥለው ዙር ውይይት ላይ ለመገኘት "ምንም ዓይነት እቅድ እንደሌለ" ተናግረው ነበር።