ለሳምንታት የዘለቀ ተቃውሞ ያጋጠማቸው የቦሊቪያ ፕሬዝዳንት አገሪቱ "አፋፍ ላይ ደርሳለች" ሲሉ አስጠነቀቁ

የቦሊቪያ ተቃዋሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ቦሊቪያ ውስጥ ሰባት ሰዎች የሞቱበት እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የታሰሩበት ተቃውሞ ለአንድ ወር መቀጠሉን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ ሮድሪጎ ፓዝ አገሪቱ "አፋፍ ላይ ደርሳለች" ሲሉ አስጠነቀቁ

የሠራተኛ ማኅበራት እና ነባር ማኅበረሰቦችን በወከሉ ቡድኖች በሚመራው ተቃውሞ በመላው ቦሊቪያ የሚገኙ መንገዶች ተዘግተዋል። ይህ እርምጃም ከፍተኛ የመሠረታዊው ሸቀጦች እጥረት እንዲፈጠር እና በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል እንቅስቃሴ እንዳይኖር አድርጓል።

ተቃውሞውን የሚመሩት ቡድኖች የነዳጅ ዋጋ ላይ ይደረግ የነበረው ድጎማ እንዲመለስ፣ የመንግሥትን ወጪ ለመቀነስ የተወሰዱ ተከታታይ እርምጃዎች እንዲቀለበሱ እንዲሁም ፕሬዝዳንቱ ሥልጣን እንዲለቅቁ ጠይቀዋል።

በአሜሪካ የሚደገፉት ፕሬዝዳንት ሮድሪጎ ፓዝ ከስድስት ወር በፊት ወደ ሥልጣን የመጡት አገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ እያለች ነው።

ፕሬዝዳንቱ "አገሪቱን ማውደም የሚፈልግ" ማንኛውም አካል እሳቸውን እና የሕገ መንግሥቱን ሙሉ ኃይል መጋፈጥ እንደሚኖርበት በመግለጽ ተቃዋሚዎችን አስጠንቅቀዋል።

ፓዝ በሚከተሉት ፖሊሲ ምክንያት ቁጣ ሲቀሰቀስባቸው ቆይተዋል። የአሁኑ ተቃውሞ የተነሳው ሚያዝያ ላይ የመሬት ሕግን ለማሻሻል ዕቅድ ካቅረቡ በኋላ ነው።

አነስተኛ መሬት ያላቸው አርሶ አደሮች አዲሱ እርምጃ፤ ትላልቅ መሬቶችን ያየዙ ባለሀብቶች አነስተኛ ይዞታዎችን በቀላሉ እንዲገዙ ያስችላል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል።

የአገሪቱ መንግሥት ግን የመሬት ሽያጩ በፈቃድ የሚካሄድ መሆኑን በአጽንኦት አንስቷል። አነስተኛ አርሶ አደሮችን የሚወክሉት ከፍተኛ ተጽዕኖ ያላቸው ድርጅቶች ግን የመንግሥት ቃል አላሳመናቸውም።

በተቃውሞም የአገሪቱን ዋና ዋና አውራ ጎዳናዎችን ዘግተዋል። ይህንን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ የመሬት ማሻሻያ እቅዱን ቢሰርዙም፤ ቅሬታ ያለባቸው ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ተቀላቅለዋቸዋል።

በተጨማሪም የቦሊቪያ መንግሥት በአቅርቦት እጥረት እና የዋጋ ግሽበት ምክንያት ለረጅም ጊዜ የቆየውን የነዳጅ ድጎማ አቋርጧል። ይህ እርምጃ የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር እና አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል እንዲቆጣ ምክንያት ሆኗል።

ተቃዋሚዎች መንገዶችን መዝጋታቸውም የነዳጅ እጥረቱን ይበልጥ በማባባስ የችግር አዙሪት ፈጥሯል።

ንግግር እንዲደረግ በድጋሚ ጥሪ ያቀረቡት የቦሊቪያው መሪ፤ አገሪቱን የሚያስፈልጋት ሥርዓት እንደሆነ አጥብቀው ተናግረዋል።

ይህም ቢሆን ግን የተዘጉ መንገዶችን ለማስከፈት "ሕገ መንግሥታዊ መሣሪያዎችን" ከመጠቀም ወደ ኋላ እንደማይሉ ገልጸዋል።

የቦሊቪያ ኮንግረስ ማክሰኞ ዕለት ፕሬዝዳንቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጁ እና መልሰው ለመቆጣጠር ሠራዊቱን እንዲጠቀሙ የሚያስችል ሕግ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።

ይህንን ሕግ የደገፉት ሕግ አውጪዎች፤ "አመጸኛ" ቡድኖች የተመረጠ መንግሥትን እርምጃ ሊወስኑ አይገባም በማለት ይከራከራሉ። ሕጉን የተቃወሙት በአንጻሩ እርምጃው ማኅበራዊ ውጥረቱን እንደሚያባብስ አስጠንቅቀዋል።