ትራምፕ ለኢራን ያስቀመጡት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የፈጠረው አጣብቂኝ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ባለፉት አምስት ሳምንታት በአሜሪካ-እስራኤል እና በኢራን ጦርነት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተለያዩ የጊዜ ገደቦችን፣ ግዴታዎችን እና ማስፈራሪያዎችን አውጥተዋል። በአብዛኛው ግን እንዲህ ግልፅ ሆነው አያውቁም።

በኢራን ላይ ይከፈታል የተባለው አዲሱ ዙር ጥቃት አውዳሚ ይሆናል። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ድልድዮች እና የኃይል ማመንጫዎች ዶግ አመድ ይሆናሉ።

ትራምፕ ሠኞ ዕለት "በጣም ትንሽ ነው የሚተወው" በማለት ምን ያህል አውዳሚ ሊሆን እንደሚችል አመላክተዋል።

ይህን እጣ ፈንታ ለማምለጥ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን "ለእኔ ተቀባይነት ያለው" ስምምነት ላይ መድረስ አለባት ብለዋል። የዚህ ስምምነት አንዱ ክፍል በሆርሙዝ ሰርጥ "ነፃ የነዳጅ ዝውውር" ነው።

የመጨረሻው ሰዓት በተቃረበበት በዚህ ሰዓት ኢራን ለትራምፕ የግዴታ ውል ለመፈረም ዝግጁነቷን የሚያመላክት ትንሽ ፍንጭ እንኳ አላሳየችም። የቴህራን መሪዎች ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነትን ውድቅ በማድረግ በአሜሪካ ባለሥልጣናት "የተጋነነ" ያሉትን የግዴታ ዝርዝሮች ይፋ አድርገዋል።

ይህም የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ከባድ ሁኔታ ውስጥ ያስቀምጣቸዋል። ስምምነት የማይኖር ከሆነ ትራምፕ ለሦስት ሳምንታት እንዳደረጉት ሁሉ ለአራተኛ ጊዜ የሰጡትን ቀነ ገደብ ሊያራዝሙ ይችላሉ።

ሆኖም ከእንዲህ ዓይነት ዝርዝር ማስፈራሪያ ካመነቱ ጦርነቱ እየተባባሰ ሲሄድ ያላቸውን አመኔታ ይሸረሽራል።

ኢራን እና የተቀረው ዓለም ምንም እንኳ አሜሪካ በወታደራዊ ጡንቻ እና ስልት የተካነች ብትሆንም በግልፅ የጥንካሬ አቋም እየተደራደረች አይደለም የሚል መደምደሚያ ሊይዙ ይችላሉ።

ሠኞ ዕለት ትራምፕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "አሸንፈናል" ሲሉ አጥብቀው ተናግረዋል። "በወታደራዊ ኃይል ተሸንፈዋል። ብቸኛው ያላቸው ነገር ሥነ ልቦና [ነው]፤ ውሃ ላይ አንድ ሁለት ፈንጂዎችን እንጥላለን የሚል ነው" ብለዋል።

ትራምፕ የጠቀሱት "ሥነ ልቦና" በሆርሙዝ ወሽመጥ ነዳጅ እንዳይተላለፍ በድሮን፣ ሚሳኤል እና ፈንጂዎች ማጠር አሜሪካ እውቅና ለመስጠት ፍላጎት ያላሳየችበት የኢራን ሀብት ሊሆን ይችላል።

በሠኞው የትራምፕ ጋዜጣዊ መግለጫ ባለፈው ዓመት "ሚድናይት ሀመር" በሚል ስም የሚጠራውን በኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት፤ ባለፈው ጥር ደግሞ የቬንዙዌላውን ኒኮላስ ማዱሮን የተያዙበትን መንገድ እንዲሁም በሳምንቱ መገባደጃ የነበረውን የአሜሪካ ወታደሮች የሕይወት አድን ተልዕኮ በመጥቀስ የአሜሪካን ወታደራዊ ዒላማ መቺነት አድንቀዋል።

ትራምፕ እና የብሔራዊ ደኅንንት ቡድናቸው በቅርቡ የተካሄደውን ተልዕኮ ስኬት በደስታ አክብረዋል። የተወሰደው እርምጃ አስደናቂ ቢሆንም፤ የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት "አሳዛኝ" ክስተት ከመፈጠሩ በፊት ሁኔታውን ለመቆጣጠር የተደረገ ተልዕኮ መሆኑን ግን በተዘዋዋሪ ጠቁመዋል።

ምንም እንኳ አሳዛኙ ሁኔታ ቢወገድም ውዳሴ ያስተናገደው የሕይወት አድን ተልዕኮ የአሜሪካ ወታደሮች በኢራን የሚጠብቃቸውን አደጋ ያንፀባረቀ ነው። በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል ገደቦች እንዳሉት የተማሩበት ሊሆን ይችላል።

ሌላኛው አማራጭ ትራምፕ ዛቻቸውን እውን ማድረግ ነው። ሠኞ ዕለት በተለያዩ ሁኔታዎች ይህ መፈፀም የማይፈልጉት መንገድ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ምንም እንኳ ትራምፕ ኢራናዊያን የቀጠለውን የአሜሪካ ወታደራዊ ዘመቻ እንደሚችሉት ፍላጎት አላቸው ቢሉም አሜሪካ የምታወድመው ማንኛውንም ነገር መልሶ መገንባት ያለበት እና አሜሪካ በመልሶ ግንባታ ጥረቱ እንደምትሳተፍ ተናግረዋል።

"መሠረተ ልማታቸውን ማውደም እፈልጋለሁ? በፍፁም" ብለዋል። "አሁን ጥለን ዛሬ ብንወጣ አገሪቱን መልሶ ለመገንባት 20 ዓመታት ይወስድባቸዋል።"

የማውደም ዛቻቸውን ቢፈፅሙ የመልሶ ግንባታ ጥረቱ ክፍለ ዘመን እንደሚወስድም አክለው ተናግረዋል።

ኢራንን ወደ "ድንጋይ ዘመን" እንመልሳታለን ብለው የዛቱት ገሃዳዊ አይመስልም። ነገር ግን ኢራን በቀጣናው እወስደዋለሁ ያለችው "የውድመት" አፃፋዊ እርምጃ ይልቁንም አስከፊ እንደሚሆን እና የሰብዓዊ ቀውስ እንደሚያስከትል እሙን ነው።

በዚህ መጨረሻ ሰዓት እንኳ ትራምፕ ስምምነቱ ፍሬ እንደሚያፈራ ተስፋቸው እንደቀጠለ ነው።

"በዚያኛው ወገን ንቁ እና ለመሳተፍ የሚልጉ ተሳታፊዎች አሉን" ያሉት ትራምፕ፤ ስምምነት ማደረግ ይፈልጋሉ። ከዚህ በላይ ስለዚህ መናገር አልችልም" ብለዋል።

ሁኔታዎች በተጧጧፉበት በዚህ ወቅት የፕሬዝዳንቱ አርቆ አሳቢነት የሚታይ ይሆናል። "እያንዳንዱ ነገር በእኛ ታስቦበታል" ሲሉ እቅድ እንዳላቸው የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ሠኞ ዕለት እቅዳቸውን ይፋ አላደርግም ብለዋል።

ይህም ከመጋረጃው ጀርባ ድርድሮች ለሕዝብ ይፋ ከተደረገው በላይ ስር እየሰደዱ ለመሆኑ አመላካች ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ የውሸት እና የምኞት ጥምረት ሊሆን ይችላል።

"እስከ ነገ ድረስ አላቸው" ብለዋል ትራምፕ። "ምን እንደሚፈጠር እናያለን። በጥሩ ልቦና ይደራደራሉ ብዬ አምናለሁ። የምናየው ይሆናል"