ቀጥታ, ኢራን 'እውነተኛውን ስምምነት' ሙሉ በሙሉ እስክታከብር ድረስ የአሜሪካ ኃይሎች በቀጣናው እንደሚቆዩ ትራምፕ ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በግል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ኢራን “ትክክለኛውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ የማታከበር ከሆነ “ማንም ካየው በላይ ጠንካራ የሆነ ጥቃት” እንደሚፈጸም በመግለጽ አስጠነቀቁ። ፕሬዚዳንቱ በትሩዝ ሶሻል ላይ ባጋሩት ጽሑፍ “ተኩስ ከሚጀመረው ግዙፍ እና የተሻለ እንዲሁም ማንም ካየው በላይ ጠንካራ ሆኖ ነው” በማለት አስጠንቅቀዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የአሜሪካ-ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት ‘አጠራጣሪ’ ቢሆንም የኢራን ተደራዳሪዎች ወደ ፓኪስታን አቀኑ

    የኢራን ተደራዳሪዎች ልዑክ ከአሜሪካ ጋር ጦርነቱን ለማቆም ወደ ፓኪስታን ማምራቱን በፓኪስታን የኢራን አምባሳደር አረጋግጠዋል።

    ልዑኩ ቅዳሜ ከአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዴ ቫንስ ጋር ይገናኛል።

    በፓኪስታን የኢራን አምባሳደር ሬዛ አሚሪ ሞግሃደም በኤክስ ገፃቸው ድርድሩ “ኢራን ባቀረበችው ባለ 10 ነጥብ ምክረ ሐሳብ” ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

    ድርድሩ በየትኛው አገር ባቀረበው ነጥብ ላይ ነው የሚለው አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኗል።

    አምባሳደሩ ንግግሩ የእስራኤል አገዛዝ የዲፕሎማቲክ ጥረቶችን ለማሰናከል በተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ ኢራናውያን ጥርጣሬ ባደረባቸው ሰዓት እንደሚካሄድም ጠቅሰዋል።

  2. ትራምፕ ኢራን “ትክክለኛውን ስምምነት” እስክታከብር ድረስ ሲሉ ምን ማለታቸው ነው?

    አሜሪካ እና ኢራን ያወጁት ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት እርስ በእርሱ የሚጣረስ ነው።

    አለመግባባቱ የመጣው ባለ አስር ነጥብ ዕቅድ በሚል እየተዘዋወረ ካለው ሰነድ ጋር ተያይዞ ነው።

    ትራምፕ “በዩናይትድ ስቴትስ ተቀባይነት ያለው እና አንድ ትርጉም ያለው” ስምምነት ብቻ መኖሩን ተናግረዋል።

    ይህንንም ትክክለኛ ስምምነት በሚል በመጥራት “የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች እንደማይኖር እንዲሁም የሆርሙዝ ወሽመጥ ይከፈታል፤ ደህንነቱም የይጠባቃል” የሚል መሆኑን ጠቅሰዋል።

    በኢራን ወገን ግን የተለያዩ የስምምነት ሰነዶች ይገኛሉ።

    የኢራን ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን በኢራን፣ ኢራቅ፣ የመን እና ሊባኖስ የሚካሄደውንው ውግያ የሚያስቆም እንዲሁም የሆርሙዝ ወሽመጥን ዳግም መክፈት እና አሜሪካ ማዕቀቦችን ለማንሳት ሙሉ ቁርጠኝነት እንዳላት የሚግለጽ ሰነድን አቅርቧል።

    በኋላ ላይ ደግሞ የኢራን ጠቅላይ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ይፋ ያደረገው ባለ አስር ነጥብ ዕቅድ ዩራኒየም ማበልጸግ እና ቴህራን የሆርሙዝ ወሽመጥን እንደምትቆጣጠር የሚሉ ሃሳቦችን ይዞ መጥቷል።

    በደህንነት ምክር ቤቱ መግለጫ ውስጥ በእንግሊዘኛ የቀረበው መግለጫ ላይ ዩራኒየም ማበልጸግ የሚለው ሃሳብ በኋለ ላይ እነዲወጣ ተደርጓል።

    ትራምፕ የማኅበራዊ ሚዲያ ልጥፋቸው ላይ በተኩስ አቁሙ ሊባኖስ ስለመካተቷ ያሉት ነገር የለም። ነገር ገን በተኩስ አቁሙ ዙሪያ ላለመግባባት ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ ግን የሊባኖስ አለመካተት ነው።

  3. የአሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት ጥርጣሬ ማሳደሩን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ጨመረ

    አሜሪካ ኢራንን ለሁለት ሳምንት ላለማጥቃት ከተስማማች በኋላ የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ አሳይቶ የነበረ ቢሆንም ሐሙስ ጠዋት ግን ዳግም ጨምሯል።

    በዓለም አቀፍ ገበያ ብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ በበርሚል 2.2 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 96.70 ዶላር ገብቷል። በአሜሪካ ገበያ ደግሞ ከዚህም ከፍ በማለት በ2.8 በመቶ በመጨመር 96.90 ዶላር ገብቷል።

    እስራኤል በሊባኖስ ላይ ተከታታይ ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ ቀዳዳዎች እንዲታዩ አድርጓል።

    የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስምምነቱን ካበሰሩ በኋላ ረቡዕ ዕለት ብሬንት ነዳጅ በ15 በመቶ በመቀነስ አንድ በርሜል 92 ዶላር ገብቶ ነበር። በኋላ ላይ ግን የነዳጅ ዋጋ ከዚህ ትንሽ ከፍ ብሏል።

    የነዳጅ ዋጋ ጦርነቱ የካቲት 21/ 2018 ዓ.ም. ከመጀመሩ በፊት ከነበረበት ዋጋ በጣም ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

  4. የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር የአሜሪካ-ኢራንን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማፅናት በርካታ ሥራዎች ገና ይቀራሉ አሉ

    የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ለሁለት ሳምንታት የታወጀውን የአሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማፅናት እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመክፈት “በርካታ ሥራዎች መሰራት” አለባቸው ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ረቡዕ ዕለት ስምምነቱን ለመደገፍ እና ለማፅናት የዲፕሎማሲያዊ ጥረት ለማድረግ የባሕረ ሰላጤው አገራት ጉብኝት አካል በሆነው ጉዟቸው ሳዑዲ አረቢያ ገብተዋል።

    ሰር ኪር ስታርመር ስምምነቱን ተከትሎ “እፎይታ” ስሜት እንዳለ ጠቅሰው ጊዜው ገና መሆኑን ግን ተናግረዋል።

    የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት የተሰማው የኢራን መገናኛ ብዙኃን እስራኤል ሊባኖስ ላይ ጥቃት መፈፀሟን ተከትሎ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በሆርሙዝ ማለፍ ማቆማቸውን ከዘገቡ በኋላ ነው።

    በተኩስ አቁም ድርድሩ አሸማጋይ ሆና ያገለገለችው ፓኪስታን እና ኢራን ስምምነቱ ሊባኖስንም እንደሚያካትት ቢናገሩም፤ እስራኤል ግን ስምምነቱ ሊባኖስን አይጨምርም ብላለች።

    ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን በሆርሙዝ ሰርጥ ማሳለፍ የአሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት ቁልፍ አካል ነው።

    የዩናይትድ ኪንገደም እና የሳዑዲ ወታደሮችን ያነጋገሩት ስታርመር “እንደምታውቁት በርካታ መሰራት ያለባቸው ሥታዎች አሉ፤ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ቋሚ እንዲሆን እና ሁላችንም ማየት የምንፈልገውን ሰላም ለማምጣት በርካታ ሥራዎች መሰራት አለባቸው” ብለዋል።

    ስታርመር ወደ ጂዳ ተጉዘው የሳዑዲውን አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማንን አግኝተዋል።

    ይህን ንግግር ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ሁለቱ መሪዎች የሆርሙዝ ወሽመጥ መርከቦች ያለስጋት እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ የዩኬ በአጋሮች ዘንድ ስምምነት እንዲኖር በምታደርገው ጥረት ላይ እንደተነጋገሩ ገልፀዋል።

  5. ኢራን የተኩስ አቁሙ ሦስት አንቀጾች “በግልጽ እና በይፋ ተጥሰዋል” አለች

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ መሐመድ ባገር ጋሊባፍ ትናንት ምሽት በኤክስ ገጻቸው ላይ በጻፉት ጽሑፍ ኢራን ካቀረበችው ባለ 10 ነጥብ ምክረ ሀሳብ መካከል ሦስት አንቀጾች “በግልጽ እና በይፋ ተጥሰዋል” አሉ።

    አፈ ጉባዔው በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ የሁለትዮሽ የተኩስ አቁም ስምምነት ወይም ድርድር “ምክንያታዊ አይሆንም” ብለዋል።

    ጋሊባፍ ሊባኖስ በዚህ ምክረ ሀሳብ ውስጥ ተካትታ እንደነበር የጠቀሱ ሲሆን ዋይት ሐውስ ግን ይህንን አስቀድሞ ውድቅ አድርጓል።

    በተጨማሪም አንድ ሰው አልባ አውሮፕላን ወደ ኢራን ደቡባዊ ፋርስ ግዛት መግባቱን አፈ ጉባዔው ጠቅሰዋል።

    የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊት እንዲህ አይነት ክስተት ስለመፈጠሩ "እንደማያውቅ" ለቢቢሲ ተናግሯል።

    አፈ ጉባዔው በሦስተኛው አንቀጽ ላይ ኢራን ዩራኒየም የማበልጸግ መብት የሚል ተካትቷል ያሉ ሲሆን ይህም የኢራን ጠቅላይ ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት በፋርስ ቋንቋ በሰጠው እና በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን በተነበበው መግለጫ ውስጥ ተካትቷል።

    የአሜሪካ እና የእስራኤል በኢራን ጦርነት የተጀመረው የካቲት 21 2018 ዓ.ም. ሲሆን ይህም በኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ የተደረገው ድርድር ያለውጤት ከተጠናቀቀ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።

    አንዳንድ ያልተረጋገጡ ሪፖርቶች የትራምፕ አስተዳደር አፈ ጉባኤ ጋሊባፍን የወደፊቷ ኢራን መሪ ለማድረግ እያጤነ መሆኑን ጠቁመዋል።

  6. ትራምፕ ኢራን “ለትክክለኛው ስምምነት” ሙሉ በሙሉ እስክትገዛ ድረስ ጦሩ በተጠንቀቅ እንዲቆይ አዘዙ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በግል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ኢራን “ትክክለኛውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ የማታከበር ከሆነ ማንም ካየው በላይ ጠንካራ የሆነ ጥቃት” እንደሚፈጸም በመግለጽ አስጠነቀቁ።

    ፕሬዚዳንቱ በትሩዝ ሶሻል ላይ ባጋሩት ጽሑፍ “ተኩስ የሚጀመረው ግዙፍ እና የተሻለ እንዲሁም ማንም ካየው በላይ ጠንካራ ሆኖ ነው” በማለት አስጠንቅቀዋል።

    አክለውም ሁሉም የአሜሪካ ጦር መርከቦች፣ አውሮፕላኖች እና ወታደሮች እንዲሁም ተጨማሪ ጦር መሣሪያዎች ዝግጁ እንዲሆኑ አዝዘዋል።

    ረቡዕ ዕለት አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ቢቆሙም እስራኤል ግን በሊባኖስ ላይ ጠንካራ እና ገዙፍ ድብደባዎችን መፈጸሟን አስታውቃለች።

    በዚህም የተነሳ የሄዝቦላህ አዛዠን ጨምሮ ከ180 በላይ ሰዎች መሞታቸው ተሰምቷል።

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመው ጥቃት በአስቸኳይ ካልቆመ “ጸጸት የሚያስከትል ምላሽ” እንደሚሰጥ ዝቷለ።

    የትራምፕ ማስጠንቀቂያ የተሰማው የአብዮታዊ ዘቡ ማስጠንቀቂያን ተከትሎ ነው።

    “ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ደረጃ አቅሙ የተዳከመውን ጠላት ለመምታት እና ለማጥፋት ተገቢ እና አስፈላጊ የሆነ ማንኛውም ነገር ትክክለኛው ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እስኪሆን ድረስ በኢራን እና በዙሪያው አካባቢ ይቆያል” ብለዋል ፕሬዝዳንት ትራምፕ።

    ትራምፕ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰው “ትክክለኛ ስምምነት” የማይከበር ከሆነ ግን “ሊሆን የሚችል አይመስለኝም” በማለት “ተኩስ የሚጀመረው ግዙፍ እና የተሻለ ሆኖ እንዲሁም ማንም አይቶት ከሚያውቀው በላይ ጠንካራ ሆኖ ነው” ብለዋል።

    ቀደም ብሎ “ምንም እንኳ ሐሰተኛ መረጃዎች ስለ አገሪቱ ቢኖሩም” ምንም ዓይነት የኒውከክሌር ጦር መሣሪያ እንደማይኖር እና የሆርሙዝ ወሽመጥ ደህንነቱ ተጠብቆ እንደሚከፈት ከስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር” ብለዋል።

    ይህ በእንዲህ አንዳለ “ታላቁ ጦራችን መሣሪያውን እየጫነ እና እያረፈ ቀጣዩን ድል ይጠብቃል፤ አሜሪካ ተመልሳለች” ብለዋል።

  7. የኢራን አብዮታዊ ዘብ በሊባኖስ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ከቀጠለ “ጸጸት የሚያስከትል ምላሽ” እሰጣለሁ ሲል አስጠነቀቀ

    የኢራን አብዮታዊ ዘብ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመው ጥቃት በአስቸኳይ ካልቆመ “ጸጸት የሚያስከትል ምላሽ” እንደሚሰጥ መዛቱን የኢራን መንግሥት የዜና ወኪል ዘገበ።

    አብዮታዊ ዘቡ በቴሌግራም ገጹ ላይ ባስተላለፈው መልዕክት “ቃሏን ላጠፈችው ዩናይትድ ስቴትስ እና ጽዮናዊት አጋሯ ከባድ ማስጠንቀቂያ አለን” ብሏል።

    “በውዷ ሊባኖስ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አሁኑኑ ካልቆመ የገባነውን ቃል በመፈጸም ጸጸት የሚያስከትል ጥቃት በቀጣናው ረባሽ ላይ እንሰነዝራለን” ሲል ዝቷል።

    የአገሪቱ ብሔራዊ የዜና ወኪል ኢርና የአብዮታዊ ዘቡ ባለሥልጣናትን በመጥቀስ “በኩሩው ሄዝቦላህ ላይ የሚፈጸም ጥቃት ኢራን ላይ እንደተፈጸመ ነው። ጦሩ ከባድ ምላሽ በጨካኙ ወንጀለኛ አገዛዝ [እስራኤል] ላይ ለመውሰድ እየተዘጋጀ ነው” ማለታቸውን ዘግቧል።

  8. እስራኤል በሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ድብደባ 89 ሰዎችን ሲገደሉ ከ700 በላይ ቆሰሉ

    እስራኤል በመላው ሊባኖስ ዛሬ ረቡዕ በፈጸመችው ጥቃት 89 ሰዎች ሲገደሉ ከ700 በላይ መጎዳታቸውን የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለሮይተርስ ተናገሩ።

    ቃል አቀባዩ ጨምረው አንደተናገሩት በደቡባዊ ሊባኖስ ከሞቱት መካከል 12 የሕክምና ባለሙያዎች ይገኙበታል።

    የእስራኤል ሠራዊት በዛሬው ዕለት ባለፈው ወር በሊባኖስ የእግረኛ ወታደሮችን ካሰማራ ወዲህ “ግዙፍ የአየር ድብደባ” መፈጸሙን አስታውቋል።

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል በቴሌግራም ገጹ ላይ “ከጥቂት ሰዓታት በፊት” በቤይሩት የሄዝቦላህ አዛዥን መግደሉን አስታውቋል።

    ጦሩ ዝርዝር መረጃ እንደሚሰጥ አስታውቋል።

    የሊባኖስ ብሔራዊ የዜና ወኪል በቤይሩት እና ደቡባዊ ሊባኖስ ጥቃቶች መቀጠላቸውን ዘግቧል።

  9. ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ማለፍ ማቆማቸው ተዘገበ

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን እስራኤል የእግረኛ ጦሯ ወደ ሊባኖስ ከገባ ወዲህ ግዙፍ ያለችወን ድብደባ መፈጸሟን ተከትሎ በሆርሙዝ ወሽመጥ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ማለፍ ማቆማቸውን ዘገቡ።

    ኢራን እና አሜሪካ በደረሱት የተኩስ አቁም ላይ በባሕር ወሽመጡ በኩል ነዳጅ ጫኝ መርከቦች እንዲያልፉ ማድረግ ቁልፍ የስምምነቱ አካል ነው።

    ነገር ግን ከኢራን እስላማዊ አብዮት ዘብ ጋር ግንኙነት ያለው ፋርስ ዜና ወኪል ዛሬ ማለዳ ከቴህራን ፈቃድ አግኝተው ሁለት ነዳጅ የጫኑ መርከቦች ማለፍ ችለው የነበረ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ግን መርከቦች እንዳያልፉ ተደርገዋል።

    ዘ እስላሚክ ሪፐብሊክ የዜና ወኪል በበኩሉ እስራኤል በሊባኖስ ላይ የምትፈጽመውን የአየር ድብደባ በመቀጠሏ የመርከቦች ጉዞ መቋረጡን ዘግቧል።

  10. ምዕራባውያን ሁሉም ወገኖች በሊባኖስ ጭምር የተኩስ አቁሙን እንዲያከብሩ ጥሪ አቀረቡ

    የምዕራባውያን አገራት በኢራን "ፈጣን እና ዘላቂ ሰላም" እንዲመጣ እንዲሁም "ሁሉም ወገኖች" በሊባኖስ ጭምር የሁለት ሳምንቱን የተኩስ አቁም እንዲያከብሩ ጥሪ አቀረቡ።

    መግለጫው በዩናይትድ ኪንግደም፣ በፈረንሳይ፣ በጣሊያን፣ በጀርመን፣ በካናዳ፣ በዴንማርክ፣ በኔዘርላንድስ፣ በስፔን፣ በአውሮፓ ኮሚሽን እና በአውሮፓ ምክር ቤት መሪዎች ተፈርሟል።

    ፓኪስታንን እና ሌሎች አደራዳሪዎችን “ስምምነቱን ስላመቻቹ” በማመስገን ለሁለት ሳምንት የሚቆየው የተኩስ አቁም “መልካም” መሆኑን ገልጸዋል።

    መግለጫው "ቀጣዩ ግብ በመጪዎቹ ቀናት ጦርነቱ በፍጥነት እና በዘላቂነት በሚያበቃበት ሁኔታ ላይ ድርድር የሚደረግበት መሆን አለበት። ይህ ሊገኝ የሚችለው በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብቻ ነው። በፍጥነት በድርድር ላይ ወደ ተደረሰ ተጨባጭ ስምምነት እንዲመጣ አጥብቀን እናበረታታለን" ይላል።

    የምዕራቡ አገራት መሪዎች በመግለጫቸው ስምምነቱ "የኢራንን ሕዝብ ለመጠበቅ በጣም አስፈላጊ ነው" ብለዋል።

    “ሁሉም ወገኖች የተኩስ አቁሙን በሊባኖስ ጭምር ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን።”

  11. የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የእስራኤል ድብደባን እንዲያስቆም ጠየቁ

    የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሳላም ከፍተኛ የአየር ድብደባ ከተፈጸመ በኋላ "የሊባኖስ ወዳጆች በሙሉ" የእስራኤልን ወታደራዊ እርምጃ "በሚችሉት መንገድ ሁሉ" እንዲያስቆሙ ተማጸኑ።

    ናዋፍ ሳላም በኤክስ ገጻቸው ላይ "እስራኤል በሊባኖስ በተለይም በዋና ከተማዋ ቤይሩት ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ያልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ በሕዝብ በተጨናነቁ የመኖሪያ ሰፈሮች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸሟን ቀጥላለች" ብለዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ ያቀረቡት የእስራኤል ሠራዊት በሄዝቦላህ ላይ ዘመቻ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተለየ በመላው ሊባኖስ ዛሬ “መጠነ ሰፊ ድብደባ” መፈጸሙን ካስታወቀ በኋላ ነው።

    ሳላም እንደሚሉት የእስራኤል ጦር ጥቃቶች ለዓለም አቀፍ ሕግ "ፍፁም ቸልተኝነት" አሳይተዋል።

    አክለውም "ሁሉም የሊባኖስ ወዳጆች እነዚህን ጥቃቶች በሁሉም መንገዶች ለማስቆም እንዲረዱን ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል።

    ሊባኖን 24 የተባለ የአረብኛ ዜና ወኪል በበኩሉ በኤክስ ገጹ ላይ በሊባኖስ የሚገኙ ሆስፒታሎች በተጎጂዎች መጨናነቃቸውን አጋርቷል።

    የሊባኖስ ጤና ሚኒስትር በበኩሉ ዜጎች አውራ መንገዶችን ለአምቡላንሶች እንዲለቅቁ ጠይቋል።

    የሄዝቦላህ ደጋፊ የሆነው አል ማናር ቴሌቪዥን ጣቢያ ደግሞ እስራኤል በደቡባዊ ቤይሩት በፈጸመችው ጥቃት በርካቶች መሞታቸውን እና መጎዳታቸውን በቴሌግራም ገጹ ላይ ጽፏል።

    ኤልቢሲአይ የተባለ የሊባኖስ መገናኛ ብዙኃን በኤክስ ገጹ ላይ የአገሪቱን ጤና ሚኒስቴር ጠቅሶ በእስራኤል ጥቃት መቶዎች መሞታቸውን እና መጎዳታቸውን አጋርቷል።

    በመንግሥት የሚመራው የአገሪቱ የዜና ወኪል በበኩሉ በደቡባዊ ሊባኖስ አድሉን ከተማ በአንድ ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሦስት ሴቶች መገደላቸውን ዘግቧል።

    አሜሪካ እና ኢራን ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሲደርሱ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ይህ “ሊባኖስን አያካትትም” ብለዋል።

  12. የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ኢራን ከአሁን በኋላ ስጋት አትሆንም አሉ

    የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ፒት ሄግሴት ኢራን ላለፉት 47 ዓመታት ስጋት ሆና ቆይታ የነበረ ቢሆንም “ከአሁን በኋላ ግን አትሆንም” አሉ።

    ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ለሁለት ሳምንት የሚቆይ የተኩስ አቁም ከተደረሰ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

    ፒት ሄግሴት ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት ከፔንታጎን የጋራ ወታደራዊ አዛዦች ሊቀ መንበር የሆኑት ጄነራል ዳን ኬን ጋር በመሆን ነው።

    ፒት ሄግሴት "ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህንን ቅጽበት ፈጥረዋል፤ ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ለምናለች፤ ይህንንም ሁላችንም እናውቀዋለን" ሲሉ ተናግረዋል።

    ሄግሰት ኦፕሬሽን ኤፒክ ፉሪ “ታሪካዊ እና እጅግ አስደናቂ ነበር” ያሉ ሲሆን የአሜሪካ ጦር “የኢራንን ጦር አውድሟል” ብለዋል።

    ሄግሴት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም የተደረሰበትን ዕለት “ለዓለም ሰላም ትልቅ ቀን” ሲሉ አሞካሽተዋል።

    አክለውም “በዓለም ግንባር ቀደም አሸባሪነትን የሚደግፍ መንግሥት ራሱን፣ ሕዝቡን ወይም ግዛቱን መከላከል ሙሉ በሙሉ አቅሙ የለውም” ሲሉ ተናግረዋል።

    ሄግሴት ዩኤስ የኢራንን ባሕር ኃይል እና አየር ኃይል ጠራርጎ ለማጥፋት የያዘችውን ወታደራዊ ዓላማ አሳክታለች - አሜሪካ "ሰማያቸውን” ትቆጣጠራለች ብለዋል።

    ኢራን የተኩስ አቁሙን የተቀበለችው “በከፍተኛ ጫና” መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቅሰው ቴህራን የዋሺንግተንን ቅድመ ሁኔታዎች ባለትቀበል ኖሮ “ቀጥሎ ዒላማ የሚሆኑት ድልድዮቿ፣ የኃይል ማመንጫዎቿ፣ የነዳጅ እና ኢነርጂ መሠረተ ልማቶቿ ነበሩ” ሲሉ የፕሬዚዳንት ዛቻ ጠቅሰዋል።

    ኢራን መልሶ ለመገንባት አስርታት ዓመታትን ይወስድባት ነበር በማለት የግዛቲቱ መሪዎች ይህንን በመገንዘባቸው ከስምምነት ላይ መድረስን መርጠዋል ብለዋል።

    “ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኢራንን ምጣኔ ኃብት በደቂቃዎች ውስጥ ማሽመድመድ አቅም ነበራቸው ነገር ግን ርህራሄን መርጠዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

    ሚኒስትሩ የተኩስ አቁሙ “ለእውነተኛ ሰላም እና ለእውነተኛ ስምምነትን” ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመው መስሪያቤታቸው “ለአሁኑ” የበኩሉን አድርጓል ፣ ግን ኢራን እያንዳንዱን ስምምነት ማክበሯን ለማረጋገጥ ዝግጁ ይሆናል” ብለዋል ።

    ሄግሴት እስራኤልን “ደፋር፣ ፈቃደኛ እና አቅም ያላትአጋር” በማለት ጠርተዋታል። የተቀረው ዓለም እና ሌሎች "የአሜሪካ አጋሮች ነን የሚሉ" አንዳንድ ማስታወሻዎችን መውሰድ አለባቸው ብለዋል።

    የፔንታጎን የጋራ ወታደራዊ አዛዦች ሊቀ መንበር የሆኑት ጄነራል ዳን ኬን በበኩላቸው የአሜሪካ ጦር “ከታዘዘ ወይም ጥቃት ዘመቻውን እንዲቀጥል ጥሪ ከቀረበለት ዝግጁ ሆኖ ይጠብቃል ብለዋል።

    “የአሜሪካ ወታደሮች ባለፉት 38 ቀናት እንዳሳየነው ፍጥነት እና ቆራጥነት የጥቃት ዘመቻውን እንድንቀጥል ከታዘዝን ወይም ከተጠራን ዝግጁ ሆነን እንጠብቃለን እና ያ እንደማይሆን ተስፋ እናደርጋለን።”

  13. መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ መንቀሳቀስ መጀመራቸው ተሰማ

    የባሕር ላይ ትራንስፖርትን የሚከታተለው ማሪንትራፊክ የተሰኘ ድርጅት በኢራን ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ በነበረው የሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ “የመርከቦች እንቅስቃሴ ምልክት” መታየቱን አስታወቀ።

    በወሽመጡ አንድ በግሪክ ባለቤትነት የተያዘች እና ሌላ ደግሞ በላይቤሪያ የተመዘገበች መርከብ ማለፋቸውን ጠቅሷል።

    ቢቢሲ የመረጃውን ትክክለኛነት ከገለልተኛ ወገን አላጣራም።

    ባለፉት 40 ቀናት በወሽመጡ ላይ የሚደረግ የመርከብ እንቅስቃሴ የአለመግባባት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።

    ምንም እንኳ የረዥም ጊዜ ዕቅድ ምን እንደሆነ ባይታወቅም በአሜሪካ እና በኢራን መካከል የተደረሰው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነትን ተከትሎ ወሽመጡ ክፍት ሆኗል።

    የተወሰኑ አገራት ቀደም ብሎ ከኢራን ጋር መርከቦቻቸው በወሽመጡ በኩል ያለምንም ችግር ማለፍ እንዲችሉ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

    ከእነዚህ አገራት መካከል ፊሊፒንስ፣ ፓኪስታን እና ሕንድ ይገኙበታል።

    ቀሪው የዓለም አገራት መርከቦች ግን በወሽመጡ በኩል ለማለፍ ሲሞክሩ ተደጋጋሚ ጥቃትን ከኢራን በኩል አስተናግደዋል።

    የሆርሙዝ ወሽመጥ ተዘግቶ በቆየባቸው ሳምንታት ውስጥ የነዳጅ ዘይት፣ የተፈጥሮ ጋዝ ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሶ ነበር። ይህም የአፈር ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስፈልገው ግብዓት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫና ፈጥሮ ቆይቷል።

    የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራጋቺ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ውስጥ በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ከኢራን ጦር ጋር በመተባበር እና “የቴክኒክ ቀርነቶችን ከግንዛቤ በማስገባት” ያለምንም ችግር ማለፍ ይቻላል ብለዋል።

  14. ለኢራን የጦር መሣሪያ ሲያቀርቡ የነበሩ አገራት ታሪፍ እንደሚጣልባቸው ትራምፕ ተናገሩ

    የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኢራን የጦር መሣሪያ ሲያቀርብ የነበረ አገር “አሁኑኑ ታሪፍ ይጣልበታል” አሉ።

    ትራምፕ በግል የማኅበራዊ ድረ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ለኢራን የጦር መሣሪያ ሲያቀርብ የነበረ አገር ለአሜሪካ የሚሸጠው ማንኛውም ዕቃ ላይ "ከአሁን ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን” 50 በመቶ ታሪፍ እንደሚጣልበት ተናግረዋል።

    ትራምፕ በዚሁ የማኅበራዊ ልጥፋቸው ላይ “ምንም የሚተው ወይንም የሚቀር ነገር የለም” ሲሉ ሙሉ በሙሉ ታሪፉ ተፈጻሚ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

    ትራምፕ ለኢራን መሣሪያ ሲያቀርብ ነበር ያሉትን አገር በስም አልጠቀሱም።

    ትራምፕ በዚሁ ልጥፋቸው ላይ ከኢራን ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    ዩናይትድ ስቴትስ ከኢራን ጋር ትሰራለች ያሉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ “እኛ የወሰንነው በጣም ውጤታማ የሆነ የስርዓት ለውጥ ነው የተካሄደው!” ብለዋል።

    ትራምፕ ኢራን ዩራኒየም አታበለጽግም ያሉ ሲሆን አሜሪካ ከቴህራን ጋር በመሆን “ በጥልቅ የተቀበሩትን የኒውክሌር ብናኞች በመቆፈር ታስወግዳለች” ብለዋል።

    “አሁን በሳተላይት ቅኝት የት ስፍራ ላይ በትክክል እንደሚገኝ እየለየን ነው።”

    አክለውም “ጥቃት ከተፈጸመበት ዕለት ጀምሮ ምንም የተነካ ነገር የለም። ከኢራን ጋር ስለ ታሪፍ እና የማዕቀብ እፎይታ ተነጋግረናል፤ እየተነጋገርንም ነው። አብዛኞቹ 15 ነጥቦች ቀድሞውንም ከስምምነት ላይ ተደርሰዋል” ብለዋል።

  15. የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የተኩስ አቁም ስምምነቱ “በቀላሉ ሊጣስ” ይችላል አሉ

    የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት አገራቸው ከቴህራን ጋር የገባችው የተኩስ አቁም ስምምነት “በቀላሉ ሊጣስ የሚችል ነው” በማለት ኢራን “በቀና ልቦና” ዘላቂ ለሆነ ስምምነት መደራደር አለባት አሉ።

    የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን የምርጫ ቅስቀሳን ለመደገፍ በዋና ከተማዋ ቡዳፔስት የሚገኙት ቫንስ “ኢራናውያን ከእኛ ጋር በቀና ልቦና ለመሥራት ፈቃደኞች ከሆኑ” ስምምነት ላይ ሊደረስ ይችላል ሲሉ ተናግረዋል።

    ነገር ግን “የደረስንበትን ደካማ የሆነ ስምምነት እንኳ እንዳይሳካ የሚያደርጉ ከሆነ ደስተኛ ሊሆኑ አይችሉም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    ኢራንን ከአሜሪkኣ ጋር በማደራደር ውስጥ ሚና የነበራቸው የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህባዝ ሻሪፍ በሁለቱ አገራት መካከል “ሁሉንም አለመግባባቶች ለመፍታት የሚያስችል መደምደሚያ ላይ ለመድረስ የሚያስችል ድርድር" ለማድረግ የሚደረገውን ውይይት ኢዝላማባድ አርብ ዕለት እንደምታስተናግድ ተናግረዋል።

    የኢራን መገናኛ ብዙኃን ቫንስ የአሜሪካ ተደራዳሪ ልዑካን ቡድንን እንደሚመሩ የዘገቡ ሲሆን፣ ዋሺንግተን ግን ይህንን አላረጋገጠችም።

  16. ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከኔቶ ዋና አዛዥ ጋር ተገናኙ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና አዛዥ ማርክ ሩተ ጋር በዋይት ሐውስ መገናኘታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    ፕሬዝዳንቱ እና ዋና አዛዡ የተገናኙት በኢራን ጦርነት ምክንያት አሜሪካ ከሌሎቹ የጥምረቱ አባል አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ከሻከረ በኋላ ነው።

    የኔቶ አባል አገራት አሜሪካ በኢራን የከፈተችውን ጦርነት መቀላቀል እንደማይፈልጉ ከገለጹ በኋላ ፕሬዝዳንት ትራምፕ አገራቸውን 32 አባላት ካሉት ወታደራዊ ጥምረት እንደሚያስወጡ ተናግረዋል። ትራምፕን ከኔቶ ጋር ያቃቃረው የኢራን ጦርነትን የሚያስቆም የሁለት ሳምንት የተኩስ አቁም መደረጉ ይፋ ሆኗል።

    የኔቶ ዋና አዛዥ የሆኑት ሩተ ከትራምፕ ጋር ውጥረት ውስጥ የገቡባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ከፕሬዝዳንቱ ጋር ጥሩ ግንኙነት አዳብረዋል። የጂኦፖለቲካል ሁኔታው ቀውስ ውስጥ በገባበት በዚህ ጊዜ ከትራምፕ ጋር የሚደረገው ንግግር የኔቶው አዛዥ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ፈተና ላይ እንደሚያስቀምጠው ተነግሯል።

  17. ተቋሞቻቸውን ከአሜሪካ ጥቃት ለመጠበቅ አደባባይ ወጥተው የነበሩት ኢራናውያን

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ማክሰኞ ሌሊት ያስቀመጡት ቀነ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት ስምምነት ላይ ካልተደረሰ የኢራን መሠረተ ልማቶችን ለማውደም መዛታቸውን ተከትሎ የኢራን ባለሥልጣናት የአገሪቱ ዜጎች ዒላማ ወደሚሆኑት ተቋማት በመሄድ በዙሪያቸው ተሰባስበው እንዲከላከሏቸው ጥሪ አቅርበው ነበር።

    ሕዝቡም የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ አደባባይ ወጥቶ ታይቷል። በመጨረሻው ሰዓት አሜሪካ እና ኢራን ተኩስ ለማቆም ከስምምነት በመድረሳቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ እንደዛቱት ጥቃቱ ሳይፈጸም ቀርቷል።

  18. የአውሮፓ አገራት ስለ አሜሪካ እና ኢራን ተኩስ አቁም ምን አሉ?

    አብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገራት መሪዎች ትናንት ሌሊት ይፋ የተደረገውን የአሜሪካ እና ኢራን ተኩስ አቁም ስምምነት በበጎ ተቀብለውታል። መሪዎቹ ተኩስ አቁም ለመደረሱ ማን እውቅና ሊሰጠው ይገባል ስለሚለው እና በቀጣይ ምን መሆን አለበት ስለሚለው የተናገሩት እንዲህ ተጠናቅሯል።

    • የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር፤ የተኩስ አቁሙ “ለቀጣናው እና ለዓለም የእፎይታ ጊዜ ያመጣል” ብለዋል። ስምምነቱ እንዲዘልቅ “ማድረግ የምንችለውን እናከናውን” ሲሉ ለአጋሮች ጥሪ አቅርበዋል።
    • የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በበኩላቸው “ተኩስ አቁሞች ሁሉም ጥሩ ዜናዎች ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል። ነገር ግን መንግሥታቸው “ዓለምን በእሳት ካነደዱ በኋላ በባልዲ ውሃ ይዘው ስለመጡ ብቻ ጭብጨባ" እንደማይቸር ገልጸዋል።
    • የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ በበኩላቸው አሜሪካ “ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ መውሰዳቸው ጠቃሚ” መሆኑን ገልጸዋል። በድኅረ ጦርነት በሚኖረው የዓለም ሁኔታ ውስጥም “የሁሉንም አገር” ጥቅም ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ጠይቀዋል።
    • የአውስትሪያ ቻንስለር ክርስቲያን ስቶከር ደግሞ “የተሳካ የአደራዳሪነት ጥረት” አድርጋለች ላሏት ፓኪስታን ምስጋናቸውን ችረዋል። በተኩስ አቁም ስምምነት አማካኝነት የዲፕሎማሲ መስኮት “ከነበረው ጥቂት ከፍ ብሎ” ተከፍቷል። ብለዋል።
  19. የእስራኤል ጦር ኢራንን ማጥቃት ማቆሙን፣ የሊባኖስ ዘመቻውን ግን እንደሚቀጥል ገለጸ

    የእስራኤል ጦር ዛሬ ጠዋት ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ ተከታታይ የአየር ጥቃቶችን ፈጸመ። ይህ ጥቃት እስራኤል በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ሊባኖስ ውስጥ ተግባራዊ እንደማታደርግ የሚጠቁም ሆኗል።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት፤ ኢራን ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ማቆሙን፤ ሊባኖስ ውስጥ የሚያካሂደውን ዘመቻ ግን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

    በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኙ ትይሬ እና ናባቲህ አካባቢዎች ረቡዕ ጠዋት ጥቃት የተፈጸመባቸው የተኩስ አቁም ስምምነቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ነው።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ፤ የተኩስ አቁሙ በኢራን ከሚደገፈው የሊባኖሱ ታጣቂ ቡድን ሄዝቦላህ ጋር የሚካሄደውን ግጭትም ያካትታል መባሉን ውድቅ አድርገዋል።

    የሊባኖስ መንግሥት እና ሄዝቦላህ እስካሁን በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጡም። ስምምነቱን ያሸማገለችው ፓኪስታን በበኩሏ ተኩስ አቁሙ ሊባኖስንም እንደሚያካትት ገልጻለች።

    ባለፉት ቀናት ኢራን በምታደርገው ድርድር ውስጥ በሊባኖስ የሚደረገውን ግጭትም እንድታካትት ሄዝቦላህ መጠየቁ ተዘግቦ ነበር።

    የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ “ኢራን ውስጥ የሚፈጽመውን ተከታታይ ጥቃት ማጠናቀቁን” ገልጿል። ከፖለቲካዊ አመራሩ “በደረው መመሪያ መሠረት” ኢራንን ማጥቃቱን እንዳቆመም አክሏል።

    እስራኤል ላይ ለሚፈጸም “ማንኛውንም ጥሰት ለመከላከል ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉን” ጠቅሷል።

    ሊባኖስ እና ሄዝቦላህን በተመለከተ ግን “የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ዒላማ ያለውን የምድር ዘመቻ ማከናወኑን ይቀጥላል” ብሏል።

    እስራኤል በበኩሏ የሊባኖስ ግዛትን ተቆጣጥራ የመቆየት እንዲሁም ድንበሩ ውስጥ የደኅንነት ዞን የማቋቋም ዕቅድ እንዳላት ገልጻለች።

    የእስራኤል ወታደሮች ሊባኖስን የወረሩ ሲሆን ይህ እርምጃቸው የአገሪቱን ክፍሎች ተወርረው እንደተያዙ እንዲቀሩ ያደርጋል የሚል ስጋት ተፈጥሯል። እስራኤል ወርራ በምትቆየው የሊባኖስ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ቤቶችን እንደምታፈርስ እና ነዋሪዎችን ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ እንደማትፈቅድ አስታውቃለች።

  20. የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በጦርነቱ “ድል ማድረጓን” ገለጸች

    ዋሽንግተን እና ቴህራን የተኩስ አቁም ማድረጋቸውን ተከትሎ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት አማካሪ ከጦርነቱ መጀመር አንስቶ በተከታታይ የኢራን ጥቃቶችን ያስተናገደችው አገራቸው “ድል ማድረጓን” ተናገሩ።

    አማካሪው አንዋር ጋርጋሽ "ሉዓላዊነትን እና ክብርን እንዲሁም ክህደት በተሞላበት ጥቃት ፊት ስኬቶቻችን ባስጠበቀ ድንቅ ብሔራዊ መከላከያ ድል አድርገናል” ብለዋል።

    ኤምሬቶች ዛሬ ላይ “የገዘፈ ተጽዕኖ የማሳደር አቅም፣ የሰላ ዕይታ እንዲሁም በወደፊቱ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር እና ለመቅረጽ የሚያስችል ይበልጥ ጠንካራ አቅም” እንዳላት አማካሪው ጠቅሰናል። ይህንንም ተጠቅመን “ውስብስብ የሆነውን ቀጣናዊ ሁኔታ ለመምራት ወደፊት እንጓዛለን" ብለዋል።

    የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ጦርነቱ ከተጀመረ አንስቶ ያከሸፋቸውን የኢራን ጥቃቶችን በተመለከተ በየጊዜው መደበኛው መረጃ ሲያወጣ ቆይቷል።

    ማክሰኞ ዕለት የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው እስካሁን ድረስ 2,221 ድሮን፣ 26 የክሩዝ ሚሳዔል እና 520 ባሊስቲክ ሚሳዔል ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ተተኩሷል።

    የኦማን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም አሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ላይ መድረሳቸውን በበጎ ተቀብሎታል።

    ፓኪስታን ለማሸማገል ላከናወነችውን ሥራ ዕውቅና የሰጠው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ፤ ወደ ቋሚ ተኩስ አቁም ለመድረስ ወደፊት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ "ጥረቶችን ማጠናከር" አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥቷል።