ፌደራል ‎ፖሊስ "ከ50 በላይ ሴቶች እንዲደፈሩ" እና "ከ100 በላይ ለሞት ዳርጓል" ያለውን ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪን ያዘ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

‎የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ "ከ50 በላይ ሴቶች እንዲደፈሩ" እና "ከ100 በላይ ሰዎችን" ለሞት የዳረገ ነው ያለውን ሕገወጥ አዘዋዋሪ ትግራይ ክልል ሽሬ ከተማ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

ፖሊስ ሰኞ ዕለት መጋቢት 28/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከሦስት ሺህ በላይ ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ በማዘዋወር የተጠረጠረውን ይትባረክ ዳዊት ወይንም ክብሮም የተባለውን ግለሰብ ከዘጠኝ ግብረ አበሮቹ ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።

ሕገ ወጥ አዘዋዋሪ ቡድኑ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ወጣቶችን ከኢትዮጵያ፣ ከሱዳን፣ ከኤርትራ፣ ከጂቡቲ፣ ከኬንያ እና ከሶማሊያ በመመልመል ወደ ሊቢያ ይወስድ እንደነበር ፖሊስ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ሊቢያ ውስጥ ተጎጂዎችን አግተው የሚያሰቃዩባቸው "አምስት መጋዘን" እንዳላቸው እና በዚህ አደገኛ ወንጀል "ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ" ሲያንቀሳቀሱ እንደነበረ ፖሊስ አስታውቋል።

ይህ የሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ቡድን ሊቢያ ውስጥ ባዘጋጀው መጋዘን ስደተኞችን በማገት "የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ ከቤተሰቦቻቸው በማስላክ፤ ገንዘብ ያልከፈሉትን በቀን አንድ ጊዜ ብቻ በትንሹ እንዲመገቡ በማድረግ" እንደሚያሰቃይ ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ገንዘብ መክፈል ያልቻሉትን "በጎማ፣ በዱላ እና በኤሌክትሪክ ገመድ በሰንሰለት እጅ እና እግራቸውን አስረው በመግረፍና በማስገረፍ፣ የውሃ ማሸጊያ ፕላስቲክ አቃጥለው ሰውነታቸው ላይ በማንጠባጠብ ከፍተኛ ስቃይ" ያደርሱ ነበር ብሏል።

በዚህ የቡድኑ ድርጊት የበርካታ ስደተኞች "ሕይወት ማለፉን"፣ "የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው"፣ "ሴቶች እንዲደፈሩ እና ከፍተኛ አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት እንዲደርስባቸው" ማድረጉን ፖሊስ በምርመራው ማረጋገጡ ተጠቅሷል።

የፌደራል ፖሊስ በመግለጫው ላይ "ከ100 በላይ ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸውን" በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ የምስክርነት ቃል የመቀበል ሥራ መሥራቱንም ጨምሮ ገልጿል፡፡

ሊቢያ፣ ሱዳን፣ ቤልጂየም፣ እንግሊዝ፣ ካናዳ፣ ኖርዌይ፣ ኔዘርላንድስ፣ ሉግዘንበርግ እና ስዊትዘርላንድ ከሚገኙ አስራ ስድስት ተጎጂዎች ላይ ቃል መቀበሉንም የፌደራል ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል፡፡

በትግራይ ክልል ሽሬ ከተማ በቁጥጥር ስር የዋለው ክብሮም በተለያዩ አገራት የሚጠቀምባቸው ከአራት በላይ ስሞች እንደነበሩ ፖሊስ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የጠረጠራቸውን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሮክ (ROCK) ከተባለ በምሥራቅ አፍሪካ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከሚሠራ ድርጅት ጋር የመረጃ ልውውጥ ማድረጉንም ገልጿል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፈለግ ነበር የተባለው ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ይትባረክ ዳዊት አለሙ ከዚህ ቀደም ወላጆቹ ባወጡለት ስም ጳውሎስ ዳዊት ወልዳይ ይታወቅ እንደነበር ፖሊስ ጠቅሷል።

የፌደራል ፖሊስ በመግለጫው ላይ "ወንጀል መሥራት ሲጀምር የሚታወቅባቸው ስሞች" በማለት ግለሰቡ "ሱዳን አገር የሚታወቅበት ስም አህመድ፤ ሱማሊያ፣ ጅቡቲ እና ኬንያ የሚጠቀምበት ስም ሙኒር" መሆኑን ግለጿል።

ክብሮም ደግሞ በስዊድን እና በሌሎች የአውሮፓ አገራት የሚጠቀምባቸው ሐሰተኛ ስሞች መሆናቸውን ፖሊስ በምርመራ ማረጋገጡን በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

ፖሊስ እነዚህን ስሞች በመጠቀም ምርመራ እና ክትትል ማድረጉን አመልክቶ "ከ70 በላይ በአገር ውስጥ እና በተለያዩ አገራት የሚገኙ ዋና ዋና የሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎችን" መለየቱን አስታውቋል።

ከዚያ በኋላ ፖሊስ ዋና ተጠርጣሪ ነው ያለውን ክብሮምን ጨምሮ በአጠቃላይ 10 ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል።

"ፖሊስ የተያዙትንም ሆነ ያልተያዙትን ተጠርጣሪዎች በወንጀሉ ያፈሩትን ሀብት በጥናት በመለየት ሌሎች ሀብቶቻቸውንና በባንክ የሚገኝ ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ" በፍርድ ቤት ማሳገዱን ፖሊስ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተሻለ ኑሮን ፍለጋ በርካታ ወጣት ሴቶች እና ወንዶች ያላቸው ለሕገወጥ አዘዋዋሪዎች በመክፈል በአደገኛ ሁኔታ የአገራትን ድንበር እና ባሕሮችን በማቋረጥ ሞትን ጨምሮ ለተለያዩ አደጋዎች ይዳረጋሉ።

ፍልሰተኞቹ በጉዞቿ ው ውስጥ ከሚያጋጥሟቸው እንግልቶች እና ለሕይወት አደገኛ ከሆኑ ክስተቶች በተጨማሪ በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እጅ ለብዝበዛ፣ ለመደፈር፣ ለስቃይ፣ ለአካል ጉዳት እና ለሞት ይዳረጋሉ።