እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ጀምሮ ከ1500 በላይ ሕንጻዎችን አውድማለች

እስራኤል ከሐማስ ጋር የተኩስ አቁም እንደ አውሮፓውያኑ ጥቅምት 10 2025 ከደረሰች በኋላ በቁጥጥሯ ሥር ባሉት የጋዛ አካባቢዎች ከ1,500 በላይ ሕንፃዎችን ማውደሟን ቢቢሲ ቬሪፋይ ከተመለከታቸው የሳተላይት ምስሎች መረዳት ችሏል።
እንደ አውሮፓውያኑ እስከ ሕዳር 8 ድረስ የተወሰዱት የቅርብ ጊዜ ምስሎች የእስራኤል መከላከያ ኃይል በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች በሙሉ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አፈራርሷቸዋል።
ቢቢሲ ቬሪፋይ ባደረገው ግምገማ በአካባቢው የተወሰኑ ምስሎችን ማግኘት አዳጋች በመሆኑ እስራኤል ያፈራረሰቻቸው ሕንጻዎች ቁጥር ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል መገመት ይቻላል።
አንዳንድ ባለሙያዎች ፍርስራሹ በአሜሪካ፣ በግብፅ፣ በኳታር እና በቱርክ አደራዳሪነት ከስምምነት የተደረሰውን የተኩስ አቁም ሊጥስ ይችላል ብለዋል።
ነገር ግን የእስራኤል መከላከያ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ቬሪፋይ እየተንቀሳቀሱ ያሉት "የተኩስ አቁም ማዕቀፉን ተከትሎ" መሆኑን ተናግረዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለጋዛ የነደፉት ባለ 20 ነጥብ የሰላም ዕቅድ "የአየር እና የመድፍ ድብደባዎችን ጨምሮ ሁሉም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ይቆማሉ" ይላል።
ፕሬዚዳንቱ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ "ጦርነቱ አብቅቷል" ሲሉም በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
የቢቢሲ ቬሪፋይ የተመለከታቸው የሳተላይት ምስሎች የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ እያደረሱት ያለው ውድመት በከፍተኛ ደረጃ መቀጠሉን አረጋግጧል።
ቢቢሲ ቬሪፋይ ከተኩስ አቁም በፊቱ የተነሱ እንዲሁም ከስምምነቱ በኋላ የተወሰዱትን የሳተላይት ምስሎችን በመመልከት እና የደረሱ ውድመቶችን ለማመልከት በተናጠል ቆጠራ አካሄዷል።
በዚህም በሰሜን፣ ደቡብ እና ምሥራቅ ጋዛ ወሰን በመሆን እያገለገለ በሚገኘው ቢጫ መስመር ጀርባ የወደሙ ሕንጻዎችን መመልከት ተችሏል።
በጥቅምት ወር በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት እስራኤል ጦሯን በካርታዎች ላይ በቢጫ መስመር ወደተመልከቱት አካባቢዎች ለማስወጣት ተስማምታለች።
ቤቶች፣ እርሻዎች እና ዕጽዋት ወድመዋል
በምሥራቅ ካን ዮኒስ እና በአባሳን አል ካቢር አካባቢ የነበሩ ብዙዎቹ የፈራረሱ ሕንፃዎች ከመውደማቸው በፊት ጉዳት የደረሰባቸው አይመስሉም።
ከላይ በተነሳ የሳተላይት ምስል ብቻ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ ነው፤ ነገር ግን እነዚህ ሕንጻዎች በአወቃቀራቸው ላይ የሚታይ የደረሰ ጉዳት አልነበራቸውም፤ ወይም በአቅራቢያቸው እንዳሉ ፍርስራሾች ወይም የጉዳት ለውጦችን የሚናገሩ ምልክቶች አልነበሩም።
የአትክልት ስፍራዎች፣ ዛፎች እና አንዳንድ ትናንሽ የአትክልት ስፍራዎች ያሉባቸው ቤቶች ነበሩ።
መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ጦርነቱ ሲጀምር የተነሱትንከተኩስ አቁም በኋላ ከተነሱ የሳተላይት ምስሎች ጋር ሲነጻጸር በብዙ ሕንፃዎች ላይ ለውጥ ያሳያል።
ላና ካህሊል ወደ አልማዋሲ ከመፈናቀሏ በፊት በአብሳን አል ካቢራ ትኖር ነበር።
ቤቷን ስትገልጸው "ዓለም ነበር" እንዲሁም "በአፀዶች እና አትክልቶች የተሞላ ነበር" በማለት ነው።
አሁን ግን ልክ በጋዛ አንዳሉት ሌሎች አካባቢዎች ሁሉ አካባቢው በፍርስራሾች ተሞልቷል።
"የእስራኤል ጦር ምንም ነገር አላስቀረልንም። ሁሉንም ነገር ነው እያፈራረሱ ያሉት" ትላለች።
ካህሊል አክላም "በአል ማዋሲ በሚገኘው ድንኳናችን ሆነን" ሲያፈራርሱት ይሰማናል ብላለች።
አክላም "ልባችን ተሰብሯል" ስትል ሐዘኗን ገልጻለች።
በራፋህ ምሥራቃዊ አካባቢ አል ባዩክ በሚባል አካባቢ የተገኙ ሳተላይት ምሥሎች እንዲሁ ተመሳሳይ ታሪክ ይናገራሉ።
ከተኩስ አቁሙ በፊት ቆመው የነበሩ ሕንጻዎች ከስምምነቱ በኋላ ወድመዋል።
በሕዳር ወር ከአየር ላይ የተቀረፁ ምስሎች በአካባቢው ትልቅ አቧራ ሲነሳ አሳይተው ነበር።
በጋዛ ከተማ፣ በሼጃኢያ እንዲሁም ኢንዶኔዢያ ሆስፒታል ጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ አቅራቢያም የሚደርሱ ውድመቶች እና ማፈራረሶች እንደቀጠሉ ናቸው።
በእስራኤል ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ውስጥ የብሔራዊ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ኢታን ሻሚር የእስራኤል ጦር ድርጊት የተኩስ አቁም ጥሰት ላይሆን ይችላል ይላሉ። ስምምነቱ ከቢጫው መስመር ወዲያ ማዶ ባሉ አአካባቢዎች ተግባራዊ አይሆንም ሲሉም ይከራከራሉ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ እና ትክክለኛነታቸው የተረጋገጡ ቪዲዮዎች ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በኋላ ከቢጫው መስመር ጀርባ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ማፈራረሶችን፣ ዶዘሮች ሕንጻዎችን ሲመነጋግሉ ያሳያሉ።
ማፈራረስ "የተኩስ አቁም ጥሰት"
የእስራኤል ጦር የድርጊቱን ትክክለኛነት የገለፀ ሲሆን ቃል አቀባዩ "በስምምነቱ መሠረት፣ ሁሉም የአሸባሪዎች መሠረተ ልማቶች፣ ዋሻዎችን ጨምሮ በመላው ጋዛ ይወድማሉ፤ እስራኤል ምላሽ እየሰጠች ያለችው ባለባት ስጋት የተነሳ፣ ለጥሰቶች እና ለአሸባሪ መሠረተ ልማቶች ነው" ብለዋል።
ጥቅምት 18 የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር በኤክስ ገጻቸው ላይ "ጋዛን ከወታደራዊ አንቅስቃሴ ነጻ ማድረግ እና ሁሉንም የሽብር መሠረተ ልማቶችን" ማፈራረስ "ግልጽ" የእስራኤል ደህንነት ፖሊሲ ነው።
ዋይት ሐውስ ይፋ ያደረገው የትራምፕ የሰላም ዕቅድ 13ኛው ነጥብ "ወታደራዊ፣ ሽብር እና ለጥቃት የሚውሉ መሠረተ ልማቶች ዋሻዎችን እና የጦር መሣሪያ ማምረቻ ተቋማት ይወድማሉ፤ እንዲሁም ዳግም አይገነቡም" ይላል።
ነገር ግን ጋዛን ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ የማውጣት ሂደት "በገለልተኛ ተቆጣጣሪዎች ቁጥጥር ሥር" እንደሚሆንም ይገልጻል።
የሩሲ (RUSI) ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሃ ሄየር "ይህ በእርግጠኝነት የተኩስ አቁም ጥሰት ነው" ይላሉ። "ነገር ግን (ዋሺንግተን) ዲሲ እንደዚያ ለመረዳት ፈቃደኛ አይደለችም፣ ይህም የተኩስ አቁም ስምምነት በትክክል ባይፀናም እንኳ ፀንቷል ማለት ብቻ ፈቅደዋል።"
ነገር ግን ሻሚር የመከላከያ ሠራዊት የተኩስ አቁም ስምምነቱን እየጣሰ መሆኑን አስተባብለዋል። ለቢቢሲ ቬሪፋይ እንደተናገሩት በእስራኤል ጦር ውስጥ ያሉት ምንጮቻቸውን በመጥቀስ "ሐማስ በሚቆጣጠረው ክልል የፈለገውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል፤ እስራኤልም በምትቆጣጠረው ክልል የፈለገችውን እንድታደርግ ተፈቅዷል" የሚል አመለካከት አለ።
የመከላከያ ኃይሉ ሐማስ ሁለተኛውን ዙር የተኩስ አቁም ስምምነት ሊቀበል አይችልም የሚል አመለካከት መኖሩን እነዚሁኑ ምንጮቻቸውን ጠቅሰው ተናግረዋል።
"ስለዚህ ወታደሮቻችን ላይ የደፈጣ ጥቃት እንዳይደርስ ለውጊያው ቀጣይነት ቦታው መዘጋጀት አለበት።"
በተጨማሪም ሐማስ ከቢጫ መስመሩ አልፎ ሰርጎ ለመግባት ተደጋጋሚ ሙከራዎች በማድረጉ እና አሁንም ሊፈተሹ የሚገባቸው ረዥም የዋሻ ክፍሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
እንደ ሩትገርስ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሰር አዲል ሃክ ያሉ አንዳንድ ተንታኞች ግን እስራኤል ወረራ የፈጸመ ኃይል የሰላማዊ ዜጎችን ንብረት ማውደም የሚከለክለውን የጦርነት ሕግን እየጣሰች ነው ይላሉ።
"ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ማለትም ከጦርነት ወይም ለጦርነት ቀጥተኛ ዝግጅቶች" ሳይኖር የተኩስ አቁም በሚደረግበት ወቅት "ይህን የመሰለ ጉልህ የሆነ የሰላማዊ ዜጎች ንብረት ማውደም የግድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ምክንያታዊ አይደለም" ሲሉ አብራርተዋል።
በአውሮፓ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት ከፍተኛ የፖሊሲ ባልደረባ የሆኑት ሂዩ ሎቫት ሕንጻዎችን ማፈራረሱ የሰላም ዕቅዱን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል ብለዋል።
"እስራኤል ከቢጫ መስመር ጀርባ ባለው ቀጠና በቆየች ቁጥር ማፈራረሱ እየጨመረ ይሄዳል። በመጨረሻም እስራኤል መውጣትዋን ትታ በዌስት ባንክ እንዳደረገችው በመሬት ላይ አዳዲስ ቋሚ እውነታዎችን ለመፍጠር እየሞከረች ነው የሚለው ስሜት የተኩስ አቁምን ማስጠበቅ ላይ የበለጠ ስጋት ይሆናል።"















