በመንትያ ቄሶች እና በመንትዮች ታጅበው የተዳሩት መንትዮች

ሁለት መንትያ ሙሽሮች፣ ከመንትያ ካህናት እና መንትያ አጃቢዎች ኣገር

የፎቶው ባለመብት, Family Handout

የምስሉ መግለጫ, ይህ ብዙዎችን ያስደመመ ሰርግ ለዓመታት በጥንቃቄ የታቀደ ነበር
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

አራት መንትዮችን የሚያሳየው ፎቶ በደቡባዊ ሕንድ በሰፊው መነጋገሪያ ሆኗል።

ምሥሉ ሁለት መንትያ ወንድማማቾች መንትያ እህትማማቾችን ማግባታቸውን ያሳያል። መንትዮቹን ያጋቡት ደግሞ መንታ ካህናት ሲሆኑ ያጀቧቸውንም መንትያ ታዳጊዎች ናቸው።

ይህ ለየት ያለ እና ብዙዎችን ያስደመመ የሰርግ ሥነ ሥርዓት በከፍተኛ ሁኔታ የታሰበበት እና የታቀደ ነበር።

ከሙሽሮቹ አንዱ የሆነው አክሂል ቶማስ "ሁለት ጥንድ መንትያ ሙሽሮችን በአንድ ሰርግ ላይ ማግኘት አጋጣሚ ሊሆን አይችልም" ብሏል።

ኒክሂል ቶማስ እና ማሪያ ማሪ (በስተግራ) ማጊ ማሪ እና አክሂል ቶማስ (በስተቀኝ) በቤተ ክርስትያን ውስጥ ከእንግዶች ጋር ተቀምጠው

የፎቶው ባለመብት, Family Handout

የምስሉ መግለጫ, ኒክሂል (በስተግራ) እና አክሂል (በስተቀኝ) መንትያ እህቶችን አግኝተው ለማግባት ለረዥም ጊዜ ተስፋ ያደርጉ ነበር

የአክሂል መንትያ ወንድም የሆነው ሙሽራው ኒክሂል ቶማስ "መንትዮችን ለማግባት ቆርጠን ነበር። ቤተሰባችን ለእኛ ተስማሚ የሆኑ ሙሽሮችን ለመፈለግ ሦስት ዓመታት ፈጅቶበታል" ይላል።

32 ዓመት የሆናቸው ወንድማማቾች በአካባቢው ባሕል መሠረት ትዳር ለመመሥረት ዘግይተዋል።

"በሠላሳዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ስለሆንን፣ ዘመዶቻችን መንትዮችን እንዳንጠብቅ አጥብቀው ይጠይቁን ነበር" ያለው አክሂል "ሌሎች [መንትያ ያልሆኑ] ሴቶችን ካላገባን ጨርሶ ላናገባ እንደምንችል አስጠንቅቀውናል" ሲል የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል።

ሁለቱ ሙሽሮች አበባ ይዘው በካህናት፣ አጃቢዎቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ጋር ሆነው

የፎቶው ባለመብት, Family Handout

የምስሉ መግለጫ, ሠርጉ የተካሄደው እአአ ሐምሌ 30 በደቡባዊ ሕንድ በሚገኝ የሜትሮፖሊታን ቤተክርስቲያን ውስጥ ነበር።

ቤተሰቦቻቸው ለልጆቻቸው ተስማሚ የሆኑ ሙሽሮችን ለማግኘት ተስፋ በማድረግ፣ በተለይ ለመንትዮች የሚሆን የሰርግ ሥነ ሥርዓት አዘጋጅተዋል።

አክሂል ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከማጂ እና ከማሪያ ሜሪ ጋር ከመተዋወቃቸው በፊት እስከ 40 የሚደርሱ መንትያ እህቶችን እንዳገኙ ይናገራል። ዕጣ ፈንታ ሆኖ የ31 ዓመቶቹ እህትማማቾችም መንትያ ለማግባት ይፈልጉ ነበር።

"ከልጅነታችን ጀምሮ የምናገባ ከሆነ መንትዮች መሆን እንዳለባቸው ወስነን ነበር" ትላለች ማጂ።

"አክሂልን እና ኒክሂልን ስናገኛቸው ወዲያውኑ ወደድናቸው" ያለችው ማሪያ "የሕይወት አጋሮቻችን እንደሆኑ ወሰንን" ስትል ወዲያውኑ መስማማታቸውን ትናገራለች።

ከዚያም እህትማማቾቹ የሰርጋቸውን ሥነ ሥርዓት መንትያ ካህናት እንዲያከናውኑላቸው እንደሚፈልጉ ገለጹ።

ይህ ሀሳብ የመጣው ማጂ እና ማሪያ ባለፈው ዓመት በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ መንትያ የሆኑትን ዲያቆናት፣ ጄሮን እና ጆሃን ጄምስን ካዩ በኋላ ነው።

ጋብቻው ከታቀደ በኋላ ወንድማማቾቹን አግኝተው በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዲሳተፉ ጋበዟቸው።

ሁለቱ ሙሽሮች ቤተክርስትያን ሲደርሱ

የፎቶው ባለመብት, Family Handout

የምስሉ መግለጫ, ሁለቱም ቤተሰቦች ጥንዶችን ለማግባት ለረዥም ዓመት ሲፈልጉ ቆይተዋል

የአክሂል እናት ከጥቂት ወራት በፊት በቤተ ክርስቲያን የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ መንትያ ካህናትን አይተው ስለነበር አጆ ፔሩምካትቲልን ሰርጉን እንዲያከናውኑላት አናጋገረቻቸው።

"ካህናቱን አግኝቼ ዝርዝሮቹን ስነግራቸው በጣም ተደሰቱ" ይላል አክሂል።

የሰርጉ ፎቶዎች በስፋት ከተጋሩ ጊዜ ጀምሮ መንትዮቹ ካህናት በጣም ደስተኞች ናቸው።

አጆ "ለእኛ፣ በእውነቱ የማይረሳ ሰርግ ሆኗል" ብለዋል።

ፎቶዎቹ በበይነ መረብ ላይ መዘዋወር ከጀመሩ ወዲህ ሁለት ሌሎች ቤተሰቦች የመንትያ ልጆቻቸውን ሰርግ እንዲያስፈጽሙላቸው ለካህናቱ ጥያቄ አቅርበዋል።

በቤተክርስቲያኒቱ የተካሄደውን ሠርግ የመሩት መንትያ ወንድማማቾች አንቶ እና አጆ ፔሩምካትቲል

የፎቶው ባለመብት, Family Handout

የምስሉ መግለጫ, መንትዩች ካህናቶቹ ከሠርጉ ዕለት ጀምሮ ትኩረት ስበዋል

"የእኛ በፍቅር ተሳስበን የተገናኘን አይደለንም፤ በወላጆቻችን የታቀደ እና የተዘጋጀ ጋብቻ ነው" ይላል ኒክሂል ቶማስ።

ይህ ትዳር ወላጆች እና ዘመድ አዝማድ ተስማሚ የትዳር አጋርን ለመምረጥ በሚያግዙበት ባሕላዊ የሕንድ የጋብቻ ሥርዓት ነው።

የሰርጉ ፎቶዎች በስፋት ከተሠራጩ ወዲህ፣ ጥንዶቹ በበይነ መረብ ላይ ብዙ ምርቃትን ተቀብለዋል።

ሁለቱ አዲስ ተጋቢዎች

የፎቶው ባለመብት, Family Handout

የምስሉ መግለጫ, አዲሶቹ ተጋቢዎች የሠርጋቸው ፎቶግራፍ በበርካቶች ዘንድ መወደዱ እንደተገረሙ ተናግረዋል

ብዙ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እንኳን ደስ አላችሁ ሲሏቸው፣ ሌሎች ደግሞ ለመንትዮች ድንቅ የሆነ ሰርግ ሲሉ ገልጸውታል።

"የሰርጋችን ፎቶዎች እንዲህ ተወዳጅ ይሆናሉ ብዬ አልጠበቅኩም ነበር" ትላለች ማሪያ።

"ይህንን ያደረግነው ዝና ለማግኘት ወይም የማኅበራዊ ሚዲያ ትኩረትን ለመሳብ አይደለም። ይህ የምናልመው ጋብቻ ነበር እና በድንገት ሰፊው ማኅበረሰብ ጋር ደርሷል" ትላለች።